መዝሙር 18:1-50

  • ዳዊት፣ አምላክ ስላዳነው ያቀረበው ውዳሴ

    • “ይሖዋ ቋጥኜ” ነው (2)

    • ይሖዋ ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ነው (25)

    • የአምላክ መንገድ ፍጹም ነው (30)

    • ‘ትሕትናህ ታላቅ ያደርገኛል’ (35)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የይሖዋ አገልጋይ የሆነው ዳዊት፣ ይሖዋ ከጠላቶቹ ሁሉ እጅና ከሳኦል እጅ ባዳነው ቀን ለይሖዋ የዘመረው መዝሙር፦+ 18  ብርታቴ ይሖዋ ሆይ፣+ እወድሃለሁ።   ይሖዋ ቋጥኜ፣ ምሽጌና ታዳጊዬ ነው።+ አምላኬ የምሸሸግበት ዓለቴ ነው፤+ጋሻዬ፣ የመዳኔ ቀንድና* አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው።+   ውዳሴ የሚገባውን ይሖዋን እጠራለሁ፤ከጠላቶቼም እድናለሁ።+   የሞት ገመዶች ተተበተቡብኝ፤+የማይረቡ ሰዎች የለቀቁት ድንገተኛ ጎርፍ አሸበረኝ።+   የመቃብር* ገመድ ተጠመጠመብኝ፤የሞት ወጥመድ ተጋረጠብኝ።+   በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤እርዳታ ለማግኘት አምላኬን አጥብቄ ተማጸንኩት። በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፤+እርዳታ ለማግኘት የማሰማውም ጩኸት ወደ ጆሮው ደረሰ።+   ምድርም ትንቀጠቀጥና ትናወጥ ጀመር፤+የተራሮች መሠረቶች ተንቀጠቀጡ፤እሱ ስለተቆጣም ራዱ።+   ከአፍንጫው ጭስ ወጣ፤የሚባላም እሳት ከአፉ ወጣ፤+ፍምም ከእሱ ፈለቀ።   ወደ ታች ሲወርድ ሰማያት እንዲያጎነብሱ አደረገ፤+ከእግሮቹም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበር።+ 10  በኪሩብ ላይ ተቀምጦ እየበረረ መጣ።+ በመንፈስ* ክንፎች በፍጥነት ወረደ።+ 11  ከዚያም በጨለማ ራሱን ሸፈነ፤+ጥቁር ውኃና ጥቅጥቅ ያለ ደመና+እንደ መጠለያ በዙሪያው ነበር። 12  በፊቱ ካለው ብርሃን፣ከደመናቱ መካከል በረዶና ፍም ወጣ። 13  ከዚያም ይሖዋ በሰማያት ያንጎደጉድ ጀመር፤+ልዑሉ አምላክ ድምፁን አሰማ፤+ደግሞም በረዶና ፍም ነበር። 14  ፍላጻዎቹን አስፈንጥሮ በታተናቸው፤+መብረቁን አዥጎድጉዶ ግራ አጋባቸው።+ 15  ይሖዋ ሆይ፣ ከተግሣጽህ፣ ከአፍንጫህም ከሚወጣው ኃይለኛ እስትንፋስ የተነሳ+የጅረቶች ወለል ታየ፤*+የምድር መሠረቶችም ተገለጡ። 16  ከላይ ሆኖ እጁን ሰደደ፤ከጥልቅ ውኃ ውስጥም አወጣኝ።+ 17  ከብርቱ ጠላቴ አዳነኝ፤+ከእኔ ይበልጥ ብርቱዎች ከሆኑት፣ ከሚጠሉኝ ሰዎች ታደገኝ።+ 18  ችግር ላይ በወደቅኩበት ቀን ተነሱብኝ፤+ይሖዋ ግን ድጋፍ ሆነልኝ። 19  ከዚያም ደህንነት ወደማገኝበት ስፍራ* አመጣኝ፤በእኔ ስለተደሰተ ታደገኝ።+ 20  ይሖዋ እንደ ጽድቄ ወሮታ ይከፍለኛል፤+እንደ እጄ ንጽሕና ብድራት ይመልስልኛል።+ 21  የይሖዋን መንገድ ጠብቄአለሁና፤አምላኬን በመተው ክፉ ድርጊት አልፈጸምኩም። 22  ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነው፤ደንቦቹን ቸል አልልም። 23  በፊቱ እንከን የለሽ ሆኜ እኖራለሁ፤+ራሴንም ከስህተት እጠብቃለሁ።+ 24  ይሖዋ እንደ ጽድቄ፣+በፊቱ ንጹሕ እንደሆኑት እጆቼ ብድራት ይመልስልኝ።+ 25  ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ፤+እንከን የለሽ ለሆነ ሰው እንከን የለሽ ትሆናለህ፤+ 26  ከንጹሕ ሰው ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤+ጠማማ ለሆነ ሰው ግን ብልህ መሆንህን ታሳያለህ።+ 27  ችግረኞችን* ታድናለህና፤+ትዕቢተኛውን* ግን ታዋርዳለህ።+ 28  ይሖዋ ሆይ፣ መብራቴን የምታበራው አንተ ነህና፤አምላኬ ሆይ፣ ጨለማዬን ብርሃን የምታደርገው አንተ ነህ።+ 29  በአንተ እርዳታ ወራሪውን ቡድን መጋፈጥ እችላለሁ፤+በአምላክ ኃይል ቅጥር መውጣት እችላለሁ።+ 30  የእውነተኛው አምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤+የይሖዋ ቃል የነጠረ ነው።+ እሱ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።+ 31  ደግሞስ ከይሖዋ ሌላ አምላክ ማን ነው?+ ከአምላካችንስ ሌላ ዓለት ማን ነው?+ 32  ብርታትን የሚያስታጥቀኝ እውነተኛው አምላክ ነው፤+መንገዴንም ፍጹም ያደርግልኛል።+ 33  እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች ያደርጋል፤በከፍታ ቦታዎች ላይ ያቆመኛል።+ 34  እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤ክንዶቼ የመዳብ ደጋን ማጠፍ ይችላሉ። 35  የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤+ቀኝ እጅህ ይደግፈኛል፤ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል።+ 36  ለእርምጃዬ መንገዱን ታሰፋልኛለህ፤እግሮቼ* አያዳልጣቸውም።+ 37  ጠላቶቼን አሳድጄ እደርስባቸዋለሁ፤ተጠራርገው እስኪጠፉ ድረስ ወደ ኋላ አልመለስም። 38  እንዳያንሰራሩ አድርጌ አደቃቸዋለሁ፤+እግሬ ሥር ይወድቃሉ። 39  ለውጊያው ብርታት ታስታጥቀኛለህ፤ጠላቶቼ ሥሬ እንዲወድቁ ታደርጋለህ።+ 40  ጠላቶቼ ከእኔ እንዲሸሹ ታደርጋለህ፤*እኔም የሚጠሉኝን አጠፋቸዋለሁ።*+ 41  እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ፤ ሆኖም የሚያድናቸው የለም፤ወደ ይሖዋም ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም። 42  በነፋስ ፊት እንዳለ አቧራ ፈጽሜ አደቃቸዋለሁ፤በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ አውጥቼ እጥላቸዋለሁ። 43  ስህተት ከሚለቃቅሙ ሰዎች ታድነኛለህ።+ የብሔራት መሪ አድርገህ ትሾመኛለህ።+ የማላውቀው ሕዝብ ያገለግለኛል።+ 44  ስለ እኔ በሰሙት ነገር ብቻ ይታዘዙኛል፤የባዕድ አገር ሰዎችም አንገታቸውን ደፍተው ወደ ፊቴ ይቀርባሉ።+ 45  የባዕድ አገር ሰዎች ወኔ ይከዳቸዋል፤*ከምሽጎቻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ። 46  ይሖዋ ሕያው ነው! ዓለቴ+ ይወደስ! የመዳኔ አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።+ 47  እውነተኛው አምላክ ይበቀልልኛል፤+ሕዝቦችንም ከበታቼ ያስገዛልኛል። 48  በቁጣ ከተሞሉ ጠላቶቼ ይታደገኛል፤ከሚያጠቁኝ ሰዎች በላይ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤+ከዓመፀኛ ሰው ታድነኛለህ። 49  ይሖዋ ሆይ፣ በብሔራት መካከል የማከብርህ ለዚህ ነው፤+ለስምህም የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ።+ 50  እሱ ለንጉሡ ታላላቅ የማዳን ሥራዎች ያከናውናል፤*+ለቀባውም ታማኝ ፍቅር ያሳያል፤+ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይህን ያደርጋል።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ኃያል አዳኜና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “የሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “በነፋስ።”
ወይም “የውኃ መውረጃ ቦዮች ታዩ።”
ወይም “ሰፊ ወደሆነ ስፍራ።”
ወይም “የተጎሳቆሉትን ሰዎች።”
ቃል በቃል “ትዕቢተኛውን ዓይን።”
ወይም “ቁርጭምጭሚቶቼ።”
ወይም “የጠላቶቼን ጀርባ ትሰጠኛለህ።”
ቃል በቃል “ጸጥ አሰኛቸዋለሁ።”
ወይም “ይጠወልጋሉ።”
ወይም “ታላላቅ ድሎችን ያጎናጽፋል።”