መዝሙር 26:1-12

  • ንጹሕ አቋም ይዞ መመላለስ

    • “ይሖዋ ሆይ፣ መርምረኝ” (2)

    • ከመጥፎ ጓደኞች መራቅ (4, 5)

    • ‘የአምላክን መሠዊያ እዞራለሁ’ (6)

የዳዊት መዝሙር። 26  ይሖዋ ሆይ፣ በንጹሕ አቋም* ተመላልሻለሁና ፍረድልኝ፤+ያለምንም ማወላወል በይሖዋ ታምኛለሁ።+   ይሖዋ ሆይ፣ መርምረኝ፤ ፈትነኝም፤በውስጤ ያለውን ሐሳብና* ልቤን አጥራልኝ።+   ታማኝ ፍቅርህ ምንጊዜም በፊቴ ነውና፤በእውነትህም እመላለሳለሁ።+   አታላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር አልቀራረብም፤*+ማንነታቸውን ከሚደብቁም እርቃለሁ።*   ከክፉ ሰዎች ጋር መሆን እጠላለሁ፤+ከክፉዎችም ጋር መቀራረብ* አልፈልግም።+   ንጹሕ መሆኔን ለማሳየት እጆቼን እታጠባለሁ፤ይሖዋ ሆይ፣ መሠዊያህን እዞራለሁ፤   ይህም የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፣+ድንቅ ሥራዎችህንም ሁሉ አውጅ ዘንድ ነው።   ይሖዋ ሆይ፣ የምትኖርበትን ቤት፣+የክብርህንም ማደሪያ ቦታ እወዳለሁ።+   ከኃጢአተኞች ጋር አታጥፋኝ፤*+ሕይወቴንም ከዓመፀኞች* ጋር አታስወግድ፤ 10  እጆቻቸው አሳፋሪ ድርጊት ይፈጽማሉ፤ቀኝ እጃቸውም በጉቦ የተሞላ ነው። 11  እኔ ግን ንጹሕ አቋሜን ጠብቄ እመላለሳለሁ። ታደገኝ፤* ሞገስም አሳየኝ። 12  እግሬ በደልዳላ ስፍራ ቆሟል፤+በታላቅ ጉባኤ መካከል* ይሖዋን አወድሳለሁ።+

የግርጌ ማስታወሻ

መዝ 7:8 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “ጥልቅ ስሜቴንና።” ቃል በቃል “ኩላሊቴንና።”
ቃል በቃል “(አታላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር) አልቀመጥም።”
ወይም “ከግብዞችም ጋር አልቀላቀልም።”
ቃል በቃል “መቀመጥ።”
ወይም “ነፍሴን አታጥፋ።”
ወይም “ደም ከሚያፈሱ ሰዎች።”
ቃል በቃል “ዋጀኝ።”
ቃል በቃል “በሸንጎዎች መካከል።”