መዝሙር 69:1-36

  • ጥበቃ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት

    • “ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት በልቶኛል” (9)

    • “በፍጥነት መልስልኝ” (17)

    • “ኮምጣጤ እንድጠጣ ሰጡኝ” (21)

ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ፤ “በአበቦች” የሚዘመር። የዳዊት መዝሙር። 69  አምላክ ሆይ፣ ውኃ ሕይወቴን አደጋ ላይ ስለጣላት* አድነኝ።+   መቆሚያ ስፍራ በሌለበት ጥልቅ ማጥ ውስጥ ሰምጫለሁ።+ ጥልቅ ውኃዎች ውስጥ ገባሁ፤ኃይለኛ ጅረትም ጠርጎ ወሰደኝ።+   ከመጮኼ ብዛት የተነሳ ደከምኩ፤+ድምፄም ጎረነነ። አምላኬን በመጠባበቅ ዓይኖቼ ፈዘዙ።+   ያለምክንያት የሚጠሉኝ+ከራሴ ፀጉር ይልቅ በዙ። ሊያጠፉኝ የሚፈልጉ፣ተንኮለኛ የሆኑ ጠላቶቼ እጅግ በዝተዋል። ያልሰረቅኩትን ነገር እንድመልስ ተገደድኩ።   አምላክ ሆይ፣ ሞኝነቴን ታውቃለህ፤ጥፋቴም ከአንተ የተሰወረ አይደለም።   ሉዓላዊ ጌታ የሆንከው የሠራዊት አምላክ ይሖዋ ሆይ፣አንተን ተስፋ የሚያደርጉ በእኔ የተነሳ አይፈሩ። የእስራኤል አምላክ ሆይ፣አንተን የሚሹ በእኔ የተነሳ አይዋረዱ።   በአንተ የተነሳ ነቀፋ ይደርስብኛል፤+ኀፍረት ፊቴን ይሸፍነዋል።+   ለወንድሞቼ እንደ እንግዳ፣ለእናቴ ልጆች እንደ ባዕድ አገር ሰው ሆንኩ።+   ለቤትህ ያለኝ ቅንዓት በልቶኛል፤+ሰዎች አንተን ይነቅፉበት የነበረው ነቀፋም በእኔ ላይ ደረሰ።+ 10  በጾም ራሴን* ባዋረድኩ ጊዜ፣*ነቀፋ ደረሰብኝ። 11  ማቅ በለበስኩ ጊዜ፣መቀለጃ* አደረጉኝ። 12  በከተማዋ መግቢያ የሚቀመጡት የመወያያ ርዕስ አደረጉኝ፤ሰካራሞችም ስለ እኔ ይዘፍናሉ። 13  ይሁንና ይሖዋ ሆይ፣ ጸሎቴ ተሰሚነት ሊያገኝ በሚችልበት ጊዜወደ አንተ ይድረስ።+ አምላክ ሆይ፣ በታማኝ ፍቅርህ ብዛት፣አስተማማኝ በሆነው የማዳን ሥራህም መልስልኝ።+ 14  ከማጡ አውጣኝ፤እንድሰምጥ አትፍቀድ። ከሚጠሉኝ ሰዎችናከጥልቁ ውኃ ታደገኝ።+ 15  ደራሽ ውኃ ጠርጎ እንዲወስደኝ አትፍቀድ፤+ጥልቁም አይዋጠኝ፤የጉድጓዱም አፍ በእኔ ላይ አይዘጋ።+ 16  ይሖዋ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርህ ጥሩ ስለሆነ መልስልኝ።+ እንደ ምሕረትህ ብዛት ወደ እኔ ተመልከት፤+ 17  ፊትህንም ከአገልጋይህ አትሰውር።+ ጭንቅ ውስጥ ነኝና በፍጥነት መልስልኝ።+ 18  ወደ እኔ ቀርበህ ታደገኝ፤*ከጠላቶቼ የተነሳ ዋጀኝ። 19  የደረሰብኝን ነቀፋ፣ ኀፍረትና ውርደት ታውቃለህ።+ ጠላቶቼን በሙሉ ታያለህ። 20  የተሰነዘረብኝ ነቀፋ ልቤን ሰብሮታል፤ ቁስሉም የሚድን ዓይነት አይደለም።* የሚያዝንልኝ ሰው ለማግኘት ተመኝቼ ነበር፤ ሆኖም አንድም ሰው አልነበረም፤+የሚያጽናናኝ ሰውም ለማግኘት ስጠባበቅ ነበር፤ ሆኖም አንድም ሰው አላገኘሁም።+ 21  ይልቁንም መርዝ* እንድበላ ሰጡኝ፤+በጠማኝ ጊዜም ኮምጣጤ እንድጠጣ ሰጡኝ።+ 22  ማዕዳቸው ወጥመድ፣ብልጽግናቸውም አሽክላ* ይሁንባቸው።+ 23  ዓይኖቻቸው ማየት እንዳይችሉ ይጨልሙ፤ሰውነታቸውም* ምንጊዜም እንዲንቀጠቀጥ አድርግ። 24  ቁጣህን አውርድባቸው፤የሚነደው ቁጣህም ድንገት ይምጣባቸው።+ 25  ሰፈራቸው* ወና ይሁን፤በድንኳኖቻቸው የሚኖር ሰው አይገኝ።+ 26  አንተ የመታኸውን አሳደዋልና፤ደግሞም አንተ ያቆሰልካቸውን ሰዎች ሥቃይ ሁልጊዜ ያወራሉ። 27  በበደላቸው ላይ በደል ጨምርባቸው፤ከአንተም ጽድቅ ምንም ድርሻ አይኑራቸው። 28  ከሕያዋን መጽሐፍ* ይደምሰሱ፤+በጻድቃንም መካከል አይመዝገቡ።+ 29  እኔ ግን በጭንቅና በሥቃይ ላይ ነኝ።+ አምላክ ሆይ፣ የማዳን ኃይልህ ይጠብቀኝ። 30  ለአምላክ ስም የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ፤እሱንም በምስጋና ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ። 31  ይህ ከበሬ ይበልጥ ይሖዋን ያስደስተዋል፤ቀንድና ሰኮና ካለው ወይፈን ይበልጥ ደስ ያሰኘዋል።+ 32  የዋሆች ይህን ያያሉ፤ ሐሴትም ያደርጋሉ። እናንተ አምላክን የምትፈልጉ፣ ልባችሁ ይነቃቃ። 33  ይሖዋ ድሆችን ይሰማልና፤+በምርኮ ላይ ያለውን ሕዝቡንም አይንቅም።+ 34  ሰማይና ምድር፣ባሕርና በውስጡ የሚንቀሳቀሱ ሁሉ ያወድሱት።+ 35  አምላክ ጽዮንን ያድናታልና፤+የይሁዳንም ከተሞች መልሶ ይገነባል፤እነሱም በዚያ ይኖራሉ፤ ደግሞም ይወርሷታል።* 36  የአገልጋዮቹ ዘሮች ይወርሷታል፤+ስሙን የሚወዱም+ በእሷ ላይ ይኖራሉ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነፍሴን ሊያሰምጣት ስለደረሰ።”
ወይም “ነፍሴን።”
“ባለቀስኩና በጾምኩ ጊዜ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “መተረቻ።”
ወይም “ወደ ነፍሴ ቀርበህ ተቤዣት።”
ወይም “ተስፋዬም ተሟጠጠ።”
ወይም “መርዛማ ተክል።”
ወይም “ወጥመድ።”
ቃል በቃል “ዳሌያቸውም።”
ወይም “በግንብ የታጠረው ሰፈራቸው።”
ወይም “ከሕይወት መጽሐፍ።”
ይህ ቃል ምድሪቱን እንደሚወርሱ ያሳያል።