መዝሙር 90:1-17

  • የአምላክ ዘላለማዊነትና የሰው አጭር ዕድሜ

    • ሺህ ዓመት እንደ ትናንት ቀን ነው (4)

    • የሰው ዕድሜ ከ70-80 ዓመት ነው (10)

    • “ዕድሜያችንን እንዴት መቁጠር እንዳለብን አስተምረን” (12)

የእውነተኛው አምላክ ሰው የሙሴ ጸሎት።+ 90  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ከትውልድ እስከ ትውልድ መኖሪያችን* ሆነሃል።+   ተራሮች ሳይወለዱ፣ምድርንና ዓለምን ከመፍጠርህ*+ በፊት፣ከዘላለም እስከ ዘላለም አንተ አምላክ ነህ።+   ሟች የሆነ ሰው ወደ አፈር እንዲመለስ ታደርጋለህ፤“የሰው ልጆች ሆይ፣ ወደ አፈር ተመለሱ”+ ትላለህ።   በአንተ ዘንድ ሺህ ዓመት፣ እንዳለፈችው እንደ ትናንት ቀን፣+እንደ አንድ ክፍለ ሌሊትም* ነው።   ጠራርገህ ታስወግዳቸዋለህ፤+ እንደ ሕልም ይጠፋሉ፤በማለዳ ሲታዩ እንደሚለመልም ሣር ናቸው።+   ጠዋት ላይ ሣሩ ያቆጠቁጣል፤ ደግሞም ይለመልማል፤ምሽት ላይ ግን ጠውልጎ ይደርቃል።+   በቁጣህ አልቀናልና፤+ከታላቅ ቁጣህም የተነሳ ተሸብረናል።   በደላችንን በፊትህ ታኖራለህ፤*+የደበቅናቸው ነገሮች በፊትህ ብርሃን ተጋልጠዋል።+   ከኃይለኛ ቁጣህ የተነሳ ዘመናችን* ይመናመናል፤ዕድሜያችንም ሽው ብሎ ያልፋል።* 10  የዕድሜያችን ርዝማኔ 70 ዓመት ነው፤ለየት ያለ ጥንካሬ ካለን* ደግሞ 80+ ዓመት ቢሆን ነው። ይህም በችግርና በሐዘን የተሞላ ነው፤ፈጥኖ ይነጉዳል፤ እኛም እናልፋለን።+ 11  የቁጣህን ኃይል መረዳት የሚችል ማን ነው? ቁጣህ፣ አንተ መፈራት የሚገባህን ያህል ታላቅ ነው።+ 12  ጥበበኛ ልብ ማግኘት እንችል ዘንድ፣ዕድሜያችንን እንዴት መቁጠር እንዳለብን አስተምረን።+ 13  ይሖዋ ሆይ፣ ተመለስ!+ ይህ ሁኔታ የሚቀጥለው እስከ መቼ ነው?+ ለአገልጋዮችህ ራራላቸው።+ 14  በሕይወት ዘመናችን ሁሉ እልል እንድንልና ሐሴት እንድናደርግ፣+በማለዳ ታማኝ ፍቅርህን አጥግበን።+ 15  ባጎሳቆልከን ዘመን ልክ፣መከራም ባየንባቸው ዓመታት መጠን+ ሐሴት እንዲሰማን አድርገን።+ 16  አገልጋዮችህ ሥራህን ይዩ፤ልጆቻቸውም ግርማህን ይመልከቱ።+ 17  የአምላካችን የይሖዋ ሞገስ በእኛ ላይ ይሁን፤የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ አድርግልን።* አዎ፣ የእጆቻችንን ሥራ ፍሬያማ አድርግልን።+

የግርጌ ማስታወሻ

“መጠጊያችን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “አምጠህ ከመውለድህ።”
ክፍለ ሌሊት ፀሐይ ከጠለቀችበት አንስቶ እስከምትወጣበት ድረስ ካለው ጊዜ ውስጥ አንድ ሦስተኛውን ይሸፍናል። በመሆኑም እንደ ወቅቱ ሁኔታ፣ አንድ ክፍለ ሌሊት የአራት ሰዓት ገደማ ርዝማኔ ሊኖረው ይችላል።
ወይም “በደላችንን ታውቃለህ።”
ወይም “ሕይወታችን።”
ወይም “እንደ እስትንፋስ ወዲያው ያከትማል።”
ወይም “ልዩ ብርታት ቢኖረን።”
ወይም “አጽናልን።”