መዝሙር 92:1-15

  • ይሖዋ ለዘላለም ከፍ ከፍ ብሏል

    • ሥራው ታላቅ፣ ሐሳቡም ጥልቅ ነው (5)

    • ‘ጻድቅ እንደ ዛፍ ይለመልማል’ (12)

    • አረጋውያን ማበባቸውን ይቀጥላሉ (14)

በሰንበት ቀን የሚዘመር መዝሙር። ማህሌት። 92  ለይሖዋ ምስጋና ማቅረብ ጥሩ ነው፤+ልዑሉ አምላክ ሆይ፣ ለስምህም የውዳሴ መዝሙር መዘመር መልካም ነው፤   ታማኝ ፍቅርህን በማለዳ፣ታማኝነትህንም በሌሊት ማሳወቅ+ መልካም ነው፤   አሥር አውታር ባለው መሣሪያና በክራር፣ደስ በሚል የበገና ድምፅ+ ታጅቦ ማሳወቅ ጥሩ ነው።   ይሖዋ ሆይ፣ ባከናወንካቸው ነገሮች እንድደሰት አድርገኸኛልና፤ከእጅህ ሥራዎች የተነሳ እልል እላለሁ።   ይሖዋ ሆይ፣ ሥራህ ምንኛ ታላቅ ነው!+ ሐሳብህም እንዴት ጥልቅ ነው!+   ማመዛዘን የጎደለው ሰው ይህን ሊያውቅ አይችልም፤ሞኝ የሆነም ሰው ይህን ሊረዳ አይችልም፦+   ክፉዎች እንደ አረም* ቢበቅሉ፣ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ቢያብቡ እንኳ፣ለዘላለም መጥፋታቸው የማይቀር ነው።+   ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን ለዘላለም ከሁሉ በላይ ነህ።   ይሖዋ ሆይ፣ ጠላቶችህን በድል አድራጊነት ስሜት ተመልከት፤ጠላቶችህ እንዴት እንደሚጠፉ እይ፤ክፉ አድራጊዎች በሙሉ ይበተናሉ።+ 10  አንተ ግን ኃይሌን* እንደ ዱር በሬ ኃይል ታደርጋለህ፤እኔም ገላዬን ጥሩ ዘይት እቀባለሁ።+ 11  ዓይኔ ጠላቶቼን በድል አድራጊነት ስሜት ያያል፤+ጆሮዬም የሚያጠቁኝን ክፉ ሰዎች ውድቀት ይሰማል። 12  ጻድቅ ግን እንደ ዘንባባ ዛፍ ይለመልማል፤እንደ አርዘ ሊባኖስም ትልቅ ይሆናል።+ 13  በይሖዋ ቤት ተተክለዋል፤በአምላካችን ቅጥር ግቢዎች ያብባሉ።+ 14  ባረጁ* ጊዜም እንኳ ማበባቸውን ይቀጥላሉ፤+እንደበረቱና* እንደጠነከሩ ይኖራሉ፤+ 15  ይሖዋ ትክክለኛ እንደሆነ እያወጁ ይኖራሉ። እሱ ዓለቴ ነው፤+ በእሱም ዘንድ ክፋት የለም።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ሣር።”
ቃል በቃል “ቀንዴን።”
ወይም “በሸበቱ።”
ቃል በቃል “እንደሰቡና።”