ሚልክያስ 2:1-17

  • ካህናቱ ሕዝቡን ሳያስተምሩ ቀሩ (1-9)

    • ካህኑ “በከንፈሮቹ ላይ እውቀት ሊኖረው ይገባል” (7)

  • ሚስቶቻቸውን በመፍታት በደል ፈጸሙ (10-17)

    • “እኔ ፍቺን እጠላለሁ” ይላል ይሖዋ (16)

2  “አሁንም ካህናት ሆይ፣ ይህ ትእዛዝ ለእናንተ ነው።+  ለመስማት አሻፈረኝ ብትሉና ለስሜ ክብር ትሰጡ ዘንድ በልባችሁ ባታኖሩት” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ “በእናንተ ላይ እርግማን እሰዳለሁ፤+ በረከታችሁንም ወደ እርግማን እለውጣለሁ።+ አዎ፣ በልባችሁ ስላላኖራችሁት እያንዳንዱን በረከት ወደ እርግማን ለውጫለሁ።”  “እነሆ፣ በእናንተ የተነሳ የዘራችሁትን ዘር አጠፋለሁ፤*+ ፈርሱንም ይኸውም በበዓሎቻችሁ ላይ የምትሠዉአቸውን እንስሳት ፈርስ ፊታችሁ ላይ እበትናለሁ፤ እናንተንም ወደዚያ* ወስደው ይጥሏችኋል።  ይህን ትእዛዝ የሰጠኋችሁ ከሌዊ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን ጸንቶ እንዲኖር መሆኑን ታውቃላችሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።  “ከእሱ ጋር የገባሁት ቃል ኪዳን የሕይወትና የሰላም ቃል ኪዳን ነው፤ እነዚህን በረከቶች በማግኘቱ እኔን ለመፍራት* ተነሳሳ። አዎ፣ ለስሜ ታላቅ አክብሮት አሳየ።  የእውነት ሕግ* በአፉ ውስጥ ነበር፤+ በከንፈሮቹም ክፋት አልተገኘም። ከእኔ ጋር በሰላምና በቅንነት ሄደ፤+ ብዙዎቹንም ከስህተት ጎዳና መለሰ።  ካህኑ ምንጊዜም በከንፈሮቹ ላይ እውቀት ሊኖረው ይገባል፤ ሰዎችም ሕጉን* ከአፉ ሊሹ ይገባል፤+ ምክንያቱም እሱ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ መልእክተኛ ነው።  “እናንተ ግን ከመንገዱ ፈቀቅ ብላችኋል። ብዙዎች ከሕጉ ጋር በተያያዘ* እንዲሰናከሉ አድርጋችኋል።+ የሌዊን ቃል ኪዳን አርክሳችኋል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።  “ስለዚህ በሰዎች ሁሉ ፊት የተናቃችሁና የተዋረዳችሁ እንድትሆኑ አደርጋለሁ፤ ምክንያቱም መንገዶቼን አልጠበቃችሁም፤ ከዚህ ይልቅ ሕጉን ተግባራዊ ስታደርጉ አድልዎ ፈጽማችኋል።”+ 10  “የሁላችንም አባት አንድ አይደለም?+ የፈጠረንስ አምላክ አንድ አይደለም? ታዲያ የአባቶቻችንን ቃል ኪዳን በማርከስ አንዳችን በሌላው ላይ ክህደት የምንፈጽመው ለምንድን ነው?+ 11  ይሁዳ ክህደት ፈጽሟል፤ በእስራኤልና በኢየሩሳሌምም አስጸያፊ ነገር ተፈጽሟል፤ ይሁዳ፣ ይሖዋ የሚወደውን ቅድስናውን* አርክሷልና፤+ ደግሞም የባዕድ አምላክ ሴት ልጅን አግብቷል።+ 12  ይህን የሚያደርግ ማንኛውም ሰው ለሠራዊት ጌታ ለይሖዋ ስጦታ አድርጎ መባ ቢያቀርብም እንኳ ይሖዋ ከያዕቆብ ድንኳኖች ያስወግደዋል።”+ 13  “ሌላም የምታደርጉት ነገር አለ፤ ይህም የይሖዋ መሠዊያ በእንባ፣ በለቅሶና በሐዘን እንዲሞላ ምክንያት ሆኗል፤ በመሆኑም ስጦታ አድርጋችሁ የምታቀርቧቸውን መባዎች ከእንግዲህ አይቀበልም፤ የምታቀርቡትንም ነገር ሁሉ በሞገስ ዓይን አይመለከትም።+ 14  እናንተም ‘ይህ የሆነው ለምንድን ነው?’ ብላችኋል። ይህ የሆነው ይሖዋ በአንተ ላይ ስለመሠከረብህ ነው፤ ምክንያቱም እሷ አጋርህና የቃል ኪዳን ሚስትህ* ሆና ሳለ በወጣትነት ሚስትህ ላይ ክህደት ፈጽመሃል።+ 15  ሆኖም እንዲህ ያላደረገ አለ፤ እሱ በተወሰነ መጠን የአምላክ መንፈስ ነበረው። ፍላጎቱስ ምን ነበር? የአምላክ ዘር ነበር። በመሆኑም መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ በወጣትነት ሚስታችሁም ላይ ክህደት አትፈጽሙ። 16  እኔ ፍቺን እጠላለሁና”*+ ይላል የእስራኤል አምላክ ይሖዋ፤ “ልብሱን በግፍ ድርጊት የሚሸፍነውንም* እጠላለሁ” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “መንፈሳችሁን ጠብቁ፤ ክህደትም አትፈጽሙ።+ 17  “ይሖዋን በቃላችሁ አታክታችሁታል።+ እናንተ ግን ‘ያታከትነው እንዴት ነው?’ ትላላችሁ። ‘ክፉ ድርጊት የሚፈጽም ሁሉ በይሖዋ ዓይን ጥሩ ነው፤ እሱ እንዲህ ባለ ሰው ደስ ይሰኛል’+ ወይም ‘የፍትሕ አምላክ የት አለ?’ በማለታችሁ ነው።”

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “እገሥጻለሁ።”
የመሥዋዕቶቹ ፈርስ የተጣለበትን ቦታ የሚያመለክት ነው።
ወይም “ለማክበር፤ ለእኔ አምልኮታዊ ክብር ለመስጠት።”
ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”
ወይም “መመሪያውን፤ ትምህርቱን።”
“በመመሪያችሁ፤ በትምህርታችሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
“መቅደሱን” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ሕጋዊ ሚስትህ።”
ቃል በቃል “እሱ ፍቺን ይጠላልና።”
ወይም “ግፍ የሚፈጽመውንም።”