ሚልክያስ 3:1-18

  • እውነተኛው ጌታ ቤተ መቅደሱን ለማንጻት ይመጣል (1-5)

    • የቃል ኪዳኑ መልእክተኛ (1)

  • ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ማበረታታት (6-12)

    • ይሖዋ አይለወጥም (6)

    • “ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ” (7)

    • ‘አሥራቱን ሁሉ አስገቡ፤ ይሖዋም የተትረፈረፈ በረከት ያፈስላችኋል’ (10)

  • ጻድቁ ሰውና ክፉው ሰው (13-18)

    • በአምላክ ፊት የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ (16)

    • በጻድቁና በክፉው መካከል ያለው ልዩነት (18)

3  “እነሆ፣ መልእክተኛዬን እልካለሁ፤ እሱም በፊቴ መንገድ ይጠርጋል።*+ እናንተ የምትፈልጉት እውነተኛው ጌታ* በድንገት ወደ ቤተ መቅደሱ ይመጣል፤+ ደስ የምትሰኙበት የቃል ኪዳኑ መልእክተኛም ይመጣል። እነሆ፣ እሱ በእርግጥ ይመጣል” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።  “ይሁንና እሱ የሚመጣበትን ቀን ሊቋቋም የሚችል ማን ነው? እሱ በሚገለጥበት ጊዜስ ማን ሊቆም ይችላል? እሱ እንደ አንጥረኛ እሳት፣ እንደ ልብስ አጣቢም እንዶድ* ይሆናልና።+  ደግሞም ብርን እንደሚያነጥርና እንደሚያነጻ ሰው ይቀመጣል፤+ የሌዊንም ልጆች ያነጻል፤* እንደ ወርቅና እንደ ብርም ያጠራቸዋል፤ ይሖዋም በጽድቅ መባ የሚያቀርብ ሕዝብ ይኖረዋል።  ይሁዳና ኢየሩሳሌም ስጦታ አድርገው የሚያቀርቡት መባ በቀድሞው ጊዜና በጥንት ዘመን እንደነበረው ይሖዋን ደስ ያሰኘዋል።*+  “ለመፍረድ ወደ እናንተ እቀርባለሁ፤ በመተተኞቹ፣+ በአመንዝሮቹ፣ በሐሰት በሚምሉት ሰዎች+ እንዲሁም ቅጥር ሠራተኛውን፣+ መበለቲቱንና አባት የሌለውን ልጅ* በሚያጭበረብሩትና+ ከባዕድ አገር የመጣውን ሰው ለመርዳት ፈቃደኛ በማይሆኑት* ላይ ወዲያውኑ እመሠክርባቸዋለሁ።+ እነዚህ ሰዎች እኔን አልፈሩም” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።  “እኔ ይሖዋ ነኝና፤ አልለወጥም።*+ እናንተም የያዕቆብ ልጆች ናችሁ፤ ገና አልጠፋችሁም።  ከአባቶቻችሁ ዘመን አንስቶ ከሥርዓቴ ፈቀቅ ብላችኋል፤ ደግሞም ሥርዓቴን አልጠበቃችሁም።+ ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። እናንተ ግን “የምንመለሰው እንዴት ነው?” ትላላችሁ።  “በውኑ ተራ ሰው አምላክን ይሰርቃል? እናንተ ግን እኔን ትሰርቁኛላችሁ።” እናንተም “የሰረቅንህ እንዴት ነው?” ትላላችሁ። “በምትሰጡት አሥራትና* መዋጮ ነው።  እናንተ በእርግጥ የተረገማችሁ ናችሁ፤* ትሰርቁኛላችሁና፤ አዎ፣ መላው ብሔር እንዲህ ያደርጋል። 10  በቤቴ ውስጥ እህል እንዲኖር አሥራቱን* ሁሉ ወደ ጎተራው አስገቡ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፤ “የሰማያትን መስኮቶች ከፍቼ+ ማስቀመጫ እስክታጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት ባላፈስላችሁ፣*+ እስቲ በዚህ ፈትኑኝ።” 11  “ለእናንተም ስል፣ በላተኛውን* እገሥጻለሁ፤ የምድራችሁንም ፍሬ አያጠፋም፤ በእርሻችሁ ላይ ያለው የወይን ተክልም ፍሬ አልባ አይሆንም”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 12  “እናንተ የደስታ ምድር ስለምትሆኑ ብሔራት ሁሉ ደስተኞች ብለው ይጠሯችኋል”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 13  “በእኔ ላይ ኃይለ ቃል ተናግራችኋል” ይላል ይሖዋ። እናንተም “በአንተ ላይ የተናገርነው እንዴት ነው?” ትላላችሁ።+ 14  “እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘አምላክን ማገልገል ዋጋ የለውም።+ ለእሱ ያለብንን ግዴታ በመጠበቃችንና በኃጢአታችን የተነሳ ማዘናችንን በሠራዊት ጌታ በይሖዋ ፊት በማሳየታችን ምን ተጠቀምን? 15  አሁን እብሪተኛ የሆኑ ሰዎችን ደስተኞች እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን። ደግሞም ክፉ አድራጊዎች ስኬታማ ሆነዋል።+ እነሱ በድፍረት አምላክን ይፈታተናሉ፤ ከቅጣትም ያመልጣሉ።’” 16  በዚያ ጊዜ ይሖዋን የሚፈሩ ሰዎች እርስ በርሳቸው፣ ከባልንጀሮቻቸው ጋር ተነጋገሩ፤ ይሖዋም በትኩረት አዳመጠ፤ ደግሞም ሰማ። ይሖዋንም ለሚፈሩና በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ*+ በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።+ 17  “የእኔ ልዩ ንብረት*+ በማደርጋቸውም ቀን እነሱ የእኔ ይሆናሉ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “አባት ለሚታዘዝለት ልጁ እንደሚራራ እኔም እራራላቸዋለሁ።+ 18  እናንተም በጻድቁና በክፉው እንዲሁም አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት ዳግመኛ ታያላችሁ።”+

የግርጌ ማስታወሻ

የሠራዊት ጌታ ይሖዋን ያመለክታል።
ወይም “ያዘጋጃል።”
ወይም “ሳሙና።”
ወይም “ያነጥራል።”
ወይም “ለይሖዋ እርካታ ያስገኝለታል።”
ወይም “የባዕዱን መብት በሚነፍጉት።”
ወይም “ወላጅ አልባ የሆነውን ልጅ።”
ወይም “አልተለወጥኩም።”
ወይም “አንድ አሥረኛና።”
“በእርግማን ትረግሙኛላችሁ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “አንድ አሥረኛውን።”
ቃል በቃል “ባልገለብጥላችሁ።”
ተባይ የሚያስከትለውን መቅሰፍት የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
ወይም “ስሙን ለሚያስቡ።” “ስሙን ከፍ አድርገው ለሚመለከቱ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ውድ ንብረት።”