የማርቆስ ወንጌል 11:1-33

  • ኢየሱስ እንደ ድል አድራጊ ሆኖ ገባ (1-11)

  • የበለስ ዛፏ ተረገመች (12-14)

  • ኢየሱስ ነጋዴዎችን ከቤተ መቅደሱ አባረረ (15-18)

  • ከደረቀችው የበለስ ዛፍ የሚገኝ ትምህርት (19-26)

  • የኢየሱስን ሥልጣን ተገዳደሩ (27-33)

11  ወደ ኢየሩሳሌም፣ በደብረ ዘይት ተራራ ወዳሉት ወደ ቤተፋጌ እና ወደ ቢታንያ+ በተቃረቡ ጊዜ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ሁለቱን ላካቸው፤+  እንዲህም አላቸው፦ “ወደዚያ ወደምታዩት መንደር ሂዱ፤ ወደ መንደሩም እንደገባችሁ ሰው ተቀምጦበት የማያውቅ ውርንጭላ ታስሮ ታገኛላችሁ። ፈታችሁ ወደዚህ አምጡት።  ማንም ሰው ‘ምን ማድረጋችሁ ነው?’ ቢላችሁ ‘ጌታ ይፈልገዋል፤ ደግሞም ወዲያውኑ ወደዚህ ይመልሰዋል’ በሉት።”  እነሱም ሄዱ፤ ውርንጭላውንም በአንድ ጠባብ መንገድ ዳር፣ ደጃፍ ላይ ታስሮ አገኙት።+  በዚያ ከቆሙት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ “ውርንጭላውን የምትፈቱት ለምንድን ነው?” አሏቸው።  እነሱም ኢየሱስ ያለውን ነገሯቸው፤ ከዚያም ፈቀዱላቸው።  ውርንጭላውንም+ ወደ ኢየሱስ አመጡት፤ መደረቢያቸውንም በውርንጭላው ጀርባ ላይ አደረጉ፤ እሱም ተቀመጠበት።+  ብዙዎችም መደረቢያቸውን በመንገዱ ላይ አነጠፉ፤ ሌሎች ደግሞ በመንገድ ዳር ካሉት ዛፎች ቅርንጫፎች እየቆረጡ አነጠፉ።+  ከፊቱ የሚሄዱትና ከኋላው የሚከተሉት እንዲህ እያሉ ይጮኹ ነበር፦ “እንድታድነው እንለምንሃለን!*+ በይሖዋ* ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!+ 10  የሚመጣው የአባታችን የዳዊት መንግሥት የተባረከ ነው!+ በሰማይ የምትኖረው ሆይ፣ እንድታድነው እንለምንሃለን!” 11  ኢየሱስም ኢየሩሳሌም ደረሰ፤ ከዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገባ፤ በዙሪያውም ያለውን ነገር ሁሉ ተመለከተ፤ ሆኖም ሰዓቱ ገፍቶ ስለነበር ከአሥራ ሁለቱ ጋር ወደ ቢታንያ ሄደ።+ 12  በማግስቱ ከቢታንያ እየወጡ ሳለ ተራበ።+ 13  ቅጠሏ የለመለመ አንዲት የበለስ ዛፍ ከሩቅ አየና ምናልባት ፍሬ ይገኝባት እንደሆነ ለማየት ሄደ። ወደ እሷ በቀረበ ጊዜ ግን በለስ የሚያፈራበት ወቅት ስላልነበረ ከቅጠል በቀር ምንም አላገኘባትም። 14  ስለዚህ ኢየሱስ ዛፏን “ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ” አላት።+ ይህን ሲናገርም ደቀ መዛሙርቱ ይሰሙት ነበር። 15  ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። በዚያም ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያስወጣ ጀመር፤ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም ገለባበጠ፤+ 16  ማንም ሰው ዕቃ ተሸክሞ በቤተ መቅደሱ አቋርጦ እንዳያልፍም ከለከለ። 17  ሰዎቹንም ያስተምር ነበር፤ ደግሞም “‘ቤቴ ለሕዝቦች ሁሉ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ አልተጻፈም?+ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አደረጋችሁት” አላቸው።+ 18  የካህናት አለቆችና ጸሐፍትም ያደረገውን በሰሙ ጊዜ እሱን የሚገድሉበትን መንገድ ይፈልጉ ጀመር፤+ ምክንያቱም ሕዝቡ ሁሉ በትምህርቱ ስለሚገረም ኢየሱስን ይፈሩት ነበር።+ 19  አመሻሽ ላይ ከከተማዋ ወጡ። 20  ማለዳም ላይ በመንገድ ሲያልፉ የበለስ ዛፏ ከነሥሯ ደርቃ አዩ።+ 21  ጴጥሮስም ትዝ አለውና “ረቢ፣ ተመልከት! የረገምካት የበለስ ዛፍ ደርቃለች” አለው።+ 22  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “በአምላክ ላይ እምነት ይኑራችሁ። 23  እውነት እላችኋለሁ፣ ማንም ሰው ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ቢለውና በልቡ ሳይጠራጠር የተናገረው ነገር እንደሚፈጸም ቢያምን ይሆንለታል።+ 24  ስለዚህ እላችኋለሁ፣ በጸሎት የምትጠይቁትንና የምትለምኑትን ነገር ሁሉ እንዳገኛችሁት አድርጋችሁ እመኑ፤ ደግሞም ታገኙታላችሁ።+ 25  በሰማያት ያለው አባታችሁ በደላችሁን ይቅር እንዲላችሁ እናንተም ለመጸለይ በምትቆሙበት ጊዜ በማንም ሰው ላይ ያላችሁን ቅሬታ ሁሉ ይቅር በሉ።”+ 26  *—— 27  እንደገናም ወደ ኢየሩሳሌም መጡ። በቤተ መቅደሱም ሲዘዋወር የካህናት አለቆች፣ ጸሐፍትና ሽማግሌዎች መጥተው 28  “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? እነዚህን ነገሮች እንድታደርግስ ሥልጣን የሰጠህ ማን ነው?” አሉት።+ 29  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “አንድ ጥያቄ እጠይቃችኋለሁ። እናንተም መልሱልኝ፤ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ። 30  ዮሐንስ የማጥመቅ ሥልጣን+ ያገኘው ከአምላክ* ነው ወይስ ከሰው? መልሱልኝ።”+ 31  እነሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ይባባሉ ጀመር፦ “‘ከአምላክ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤ 32  ደፍረን ‘ከሰው ነው’ ብንልስ?” ሰዎቹ ሁሉ ዮሐንስን እንደ ነቢይ ያዩት ስለነበር ሕዝቡን ፈሩ።+ 33  ስለዚህ ለኢየሱስ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። ኢየሱስም “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም” አላቸው።

የግርጌ ማስታወሻ

ግሪክኛ፣ ሆሳዕና።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ3ን ተመልከት።
ቃል በቃል “ከሰማይ።”