የማርቆስ ወንጌል 15:1-47
15 ወዲያውኑ በማለዳ የካህናት አለቆች፣ ሽማግሌዎችና ጸሐፍት ማለትም መላው የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላት ተሰብስበው ተማከሩ፤ ኢየሱስንም አስረው በመውሰድ ለጲላጦስ አስረከቡት።+
2 ጲላጦስም “አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?” ሲል ጠየቀው።+ እሱም መልሶ “አንተው ራስህ ተናገርከው” አለው።+
3 የካህናት አለቆቹ ግን በእሱ ላይ በርካታ ክስ መደርደራቸውን ቀጠሉ።
4 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ “ምንም መልስ አትሰጥም?+ በስንት ነገር እየከሰሱህ እንዳሉ ተመልከት” ሲል እንደገና ጠየቀው።+
5 ሆኖም ኢየሱስ ምንም ተጨማሪ መልስ አልሰጠም፤ በመሆኑም ጲላጦስ ተገረመ።+
6 ጲላጦስ ሁልጊዜ በዚህ በዓል ወቅት፣ ሕዝቡ ይፈታልን ብለው የጠየቁትን አንድ እስረኛ የመፍታት ልማድ ነበረው።+
7 በወቅቱ፣ በመንግሥት ላይ ዓመፅ በማነሳሳት ሰው ገድለው ከታሰሩ ዓመፀኞች መካከል በርባን የሚባል ሰው ይገኝ ነበር።
8 ሕዝቡም መጥተው ጲላጦስ እንደ ልማዱ ያደርግላቸው ዘንድ ይጠይቁት ጀመር።
9 እሱም መልሶ “የአይሁዳውያንን ንጉሥ እንድፈታላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው።+
10 ጲላጦስ ይህን ያለው የካህናት አለቆች አሳልፈው የሰጡት በቅናት ተነሳስተው እንደሆነ ያውቅ ስለነበር ነው።+
11 ይሁንና የካህናት አለቆቹ በኢየሱስ ምትክ በርባንን ይፈታላቸው ዘንድ እንዲጠይቁ ሕዝቡን አነሳሱ።+
12 ጲላጦስም እንደገና መልሶ “እንግዲያው የአይሁዳውያን ንጉሥ የምትሉትን ምን ባደርገው ይሻላል?” አላቸው።+
13 እነሱም “ይሰቀል!”* ብለው እንደገና ጮኹ።+
14 ሆኖም ጲላጦስ “ለምን? ምን ያጠፋው ነገር አለ?” አላቸው። እነሱ ግን “ይሰቀል!”* እያሉ የባሰ ጮኹ።+
15 በዚህ ጊዜ ጲላጦስ ሕዝቡን ለማስደሰት ስለፈለገ በርባንን ፈታላቸው፤ ኢየሱስንም ካስገረፈው+ በኋላ በእንጨት ላይ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው።+
16 ወታደሮቹ ወደ ግቢው ይኸውም ወደ አገረ ገዢው መኖሪያ ቤት ወሰዱት፤ ሠራዊቱንም ሁሉ አንድ ላይ ሰበሰቡ።+
17 ሐምራዊ ልብስም አለበሱት፤ የእሾህ አክሊል ጎንጉነውም በራሱ ላይ ደፉበት፤
18 ደግሞም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው “የአይሁዳውያን ንጉሥ ሆይ፣ ሰላም ለአንተ ይሁን!” ይሉት ጀመር።+
19 ከዚህም ሌላ ራሱን በመቃ ይመቱትና ይተፉበት ነበር፤ ተንበርክከውም እጅ ነሱት።*
20 ሲያፌዙበት ከቆዩ በኋላም ሐምራዊውን ልብስ ገፈው የራሱን መደረቢያዎች አለበሱት። ከዚያም በእንጨት ላይ ሊቸነክሩት ይዘውት ሄዱ።+
21 ስምዖን የተባለ አንድ የቀሬና ሰው ከገጠር መጥቶ በዚያ ሲያልፍ አግኝተው ኢየሱስ የሚሰቀልበትን የመከራ እንጨት* እንዲሸከም አስገደዱት፤* ይህ ሰው የእስክንድርና የሩፎስ አባት ነበር።+
22 በኋላም ኢየሱስን ጎልጎታ ወደተባለ ቦታ አመጡት፤ ትርጉሙም “የራስ ቅል ቦታ” ማለት ነው።+
23 እዚያም ከርቤ* የተቀላቀለበት የወይን ጠጅ ሰጡት፤+ እሱ ግን አልተቀበለም።
24 ከዚያም እንጨት ላይ ቸነከሩት፤ ማን ምን እንደሚወስድ ለመወሰንም ዕጣ ተጣጥለው መደረቢያዎቹን ተከፋፈሉ።+
25 እንጨት ላይ ሲቸነክሩትም ጊዜው ሦስት ሰዓት ነበር።
26 የተከሰሰበትን ጉዳይ የሚገልጽ “የአይሁዳውያን ንጉሥ” የሚል ጽሑፍ ተጽፎ ነበር።+
27 ከእሱም ጋር ሁለት ዘራፊዎችን፣ አንዱን በቀኙ ሌላውን ደግሞ በግራው በእንጨት ላይ ሰቀሉ።+
28 *——
29 በዚያ የሚያልፉም ይሰድቡትና ራሳቸውን እየነቀነቁ+ እንዲህ ይሉት ነበር፦ “ቤተ መቅደሱን አፍርሼ በሦስት ቀን እሠራዋለሁ ባይ!+
30 እስቲ ከተሰቀልክበት እንጨት* ላይ ወርደህ ራስህን አድን።”
31 የካህናት አለቆችም እንደዚሁ ከጸሐፍት ጋር ሆነው እርስ በርሳቸው እንዲህ እያሉ ያፌዙበት ነበር፦ “ሌሎችን አዳነ፤ ራሱን ግን ማዳን አልቻለም!+
32 አይተን እናምን ዘንድ የእስራኤል ንጉሥ ክርስቶስ እስቲ አሁን ከተሰቀለበት እንጨት* ይውረድ።”+ ከእሱ ጋር በእንጨት ላይ የተሰቀሉትም እንኳ ሳይቀሩ ይነቅፉት ነበር።+
33 ስድስት ሰዓት በሆነ ጊዜም አገሩ በሙሉ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ በጨለማ ተሸፈነ።+
34 በዘጠነኛውም ሰዓት ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ “ኤሊ፣ ኤሊ፣ ላማ ሳባቅታኒ?” ብሎ ጮኸ፤ ትርጉሙም “አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?” ማለት ነው።+
35 በአቅራቢያው ቆመው ከነበሩት አንዳንዶቹ ይህን ሲሰሙ “አያችሁ! ኤልያስን እየተጣራ ነው” ይሉ ጀመር።
36 ከዚያም አንድ ሰው ሮጦ በመሄድ የኮመጠጠ የወይን ጠጅ ውስጥ ሰፍነግ* ከነከረ በኋላ በመቃ ላይ አድርጎ እንዲጠጣ ሰጠውና+ “ተዉት! እስቲ ኤልያስ መጥቶ ያወርደው እንደሆነ እንይ” አለ።
37 ሆኖም ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ጮኾ ሞተ።*+
38 የቤተ መቅደሱ መጋረጃም+ ከላይ እስከ ታች ለሁለት ተቀደደ።+
39 ከፊት ለፊቱ ቆሞ የነበረው መኮንንም በዚህ ሁኔታ መሞቱን ሲያይ “ይህ ሰው በእርግጥ የአምላክ ልጅ ነበር” አለ።+
40 በተጨማሪም ከሩቅ ሆነው የሚያዩ ሴቶች የነበሩ ሲሆን ከእነሱም መካከል መግደላዊቷ ማርያም እንዲሁም የትንሹ* ያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያምና ሰሎሜ ነበሩ፤+
41 እነዚህም በገሊላ ሳለ ይከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ ናቸው፤+ ከእሱ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም የመጡ ሌሎች በርካታ ሴቶችም ነበሩ።
42 ቀኑ በመገባደዱና የዝግጅት ቀን ማለትም የሰንበት ዋዜማ በመሆኑ
43 የተከበረ የሸንጎ* አባል የሆነውና የአምላክን መንግሥት ይጠባበቅ የነበረው የአርማትያሱ ዮሴፍ መጣ። ደፍሮም ወደ ጲላጦስ ገባና የኢየሱስ አስከሬን እንዲሰጠው ጠየቀ።+
44 ጲላጦስ ግን ኢየሱስ ሞቶ እንደሆነ ለማወቅ የመቶ አለቃውን ጠርቶ በእርግጥ ሞቶ እንደሆነ ጠየቀው።
45 መሞቱን ከመቶ አለቃው ካረጋገጠ በኋላም አስከሬኑን እንዲወስድ ለዮሴፍ ፈቀደለት።
46 እሱም በፍታ ገዝቶ አስከሬኑን ካወረደ በኋላ በበፍታው ገነዘው፤ ከዚያም ከዓለት ተፈልፍሎ በተሠራ መቃብር ውስጥ አኖረው፤+ ድንጋይ አንከባሎም የመቃብሩን ደጃፍ ዘጋው።+
47 በዚህ ጊዜ መግደላዊቷ ማርያምና የዮሳ እናት ማርያም አስከሬኑ የተቀመጠበትን ቦታ ይመለከቱ ነበር።+
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “እንጨት ላይ ይሰቀል!”
^ ወይም “እንጨት ላይ ይሰቀል!”
^ ወይም “ሰገዱለት።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “በመሸከም የግዳጅ አገልግሎት እንዲፈጽም አደረጉት።”
^ የሚያሰክር ንጥረ ነገር።
^ ስፖንጅ ተብሎ ከሚጠራ የባሕር እንስሳ የሚገኝ ውኃን መምጠጥና መያዝ የሚችል ነገር።
^ ወይም “እስትንፋሱ ቆመ።”
^ “ትንሹ” የሚለው ቃል ያዕቆብ፣ የዘብዴዎስ ልጅ ከሆነው ከሐዋርያው ያዕቆብ በዕድሜ ወይም በቁመት እንደሚያንስ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
^ ወይም “የሳንሄድሪን።”