የማቴዎስ ወንጌል 11:1-30

  • መጥምቁ ዮሐንስ ተወደሰ (1-15)

  • ዓመፀኛው ትውልድ ተወገዘ (16-24)

  • ‘ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለልጆች ገለጥክላቸው’ (25-27)

  • የኢየሱስ ቀንበር እረፍት ይሰጣል (28-30)

11  ኢየሱስ ለ12 ደቀ መዛሙርቱ መመሪያ ሰጥቶ ከጨረሰ በኋላ በሌሎች ከተሞች ለማስተማርና ለመስበክ ሄደ።+  ዮሐንስ በእስር ቤት ሆኖ+ ክርስቶስ ስላከናወናቸው ሥራዎች ሲሰማ ደቀ መዛሙርቱን በመላክ+  “ይመጣል የተባልከው አንተ ነህ ወይስ ሌላ እንጠብቅ?” ሲል ጠየቀው።+  ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ሄዳችሁ የምትሰሙትንና የምታዩትን ነገር ለዮሐንስ ንገሩት፤+  ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤+ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤+ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤ ሙታን እየተነሱ ነው፤ ድሆችም ምሥራቹ እየተነገራቸው ነው።+  በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው።”+  መልእክተኞቹ ከሄዱ በኋላ ኢየሱስ ስለ ዮሐንስ እንዲህ ሲል ለሕዝቡ ይናገር ጀመር፦ “ወደ ምድረ በዳ የሄዳችሁት ምን ለማየት ነበር?+ ነፋስ የሚያወዛውዘውን ሸምበቆ?+  ታዲያ ምን ለማየት ነበር የሄዳችሁት? ምርጥ ልብስ* የለበሰ ሰው ለማየት? ምርጥ ልብስ የለበሱማ የሚገኙት በነገሥታት ቤት ነው።  ታዲያ ለምን ሄዳችሁ? ነቢይ ለማየት? አዎ፣ እላችኋለሁ፣ ከነቢይም የሚበልጥ ነው።+ 10  ‘እነሆ፣ ከፊትህ እየሄደ መንገድህን እንዲያዘጋጅ መልእክተኛዬን ከአንተ አስቀድሜ እልካለሁ!’+ ተብሎ የተጻፈው ስለ እሱ ነው። 11  እውነት እላችኋለሁ፣ ከሴት ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሳም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ዝቅተኛ የሆነው እንኳ ይበልጠዋል።+ 12  መንግሥተ ሰማያት ከመጥምቁ ዮሐንስ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሰዎች የሚጋደሉለት ግብ ሆኗል፤ በተጋድሏቸው የሚጸኑም ያገኙታል።+ 13  ነቢያትና ሕጉ በሙሉ እስከ ዮሐንስ ዘመን ድረስ ተንብየዋልና፤+ 14  እንግዲህ ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆናችሁ ‘ይመጣል የተባለው ኤልያስ’ እሱ ነው።+ 15  ጆሮ ያለው ይስማ። 16  “ይህን ትውልድ ከማን ጋር ላመሳስለው?+ በገበያ ስፍራ ተቀምጠው ጓደኞቻቸውን እየተጣሩ እንዲህ ከሚሉ ልጆች ጋር ይመሳሰላል፦ 17  ‘ዋሽንት ነፋንላችሁ፤ እናንተ ግን አልጨፈራችሁም፤ ሙሾ አወረድንላችሁ፤ እናንተ ግን በሐዘን ደረታችሁን አልደቃችሁም።’ 18  በተመሳሳይም ዮሐንስ ሳይበላና ሳይጠጣ መጣ፤ ሰዎች ግን ‘ጋኔን አለበት’ አሉ። 19  የሰው ልጅ እየበላና እየጠጣ መጣ፤+ ሰዎች ግን ‘እዩ፣ ይህን ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ’ አሉ።+ የሆነ ሆኖ፣ ጥበብ ጻድቅ መሆኗ* በሥራዋ* ተረጋግጧል።”+ 20  ከዚያም ብዙ ተአምራት የፈጸመባቸውን ከተሞች ንስሐ ባለመግባታቸው የተነሳ እንዲህ ሲል ይነቅፋቸው ጀመር፦ 21  “ወዮልሽ ኮራዚን! ወዮልሽ ቤተሳይዳ! በእናንተ ውስጥ የተደረጉት ተአምራት በጢሮስና በሲዶና* ተደርገው ቢሆን ኖሮ ገና ድሮ ማቅ ለብሰውና አመድ ላይ ተቀምጠው ንስሐ በገቡ ነበር።+ 22  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።+ 23  አንቺም ቅፍርናሆም+ ወደ ሰማይ ከፍ የምትዪ ይመስልሻል? በፍጹም! ወደ መቃብር* ትወርጃለሽ፤+ ምክንያቱም በአንቺ ውስጥ የተደረጉት ተአምራት በሰዶም ተደርገው ቢሆን ኖሮ እስከ ዛሬ በኖረች ነበር። 24  እኔ ግን እላችኋለሁ፣ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም ምድር ይቀልላታል።”+ 25  በዚያን ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፣ እነዚህን ነገሮች ከጥበበኞችና ከአዋቂዎች ሰውረህ ለትናንሽ ልጆች ስለገለጥክላቸው በይፋ አወድስሃለሁ።+ 26  አዎ፣ አባት ሆይ፣ ይህ የአንተ ፈቃድ ነውና። 27  አባቴ ሁሉንም ነገር ለእኔ ሰጥቶኛል፤+ ከአብ በስተቀር ወልድን በሚገባ የሚያውቅ የለም፤+ ከወልድና ወልድ ሊገልጥለት ከሚፈቅድ በስተቀር አብን በሚገባ የሚያውቅ ማንም የለም።+ 28  እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። 29  ቀንበሬን ተሸከሙ፤* ከእኔም ተማሩ፤* እኔ ገርና* በልቤ ትሑት ነኝ፤+ ለራሳችሁም* እረፍት ታገኛላችሁ። 30  ቀንበሬ ልዝብ፣* ሸክሜም ቀላል ነውና።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ለስላሳ ልብስ።”
ወይም “በውጤቷ።”
ወይም “ትክክል መሆኗ።”
እነዚህ የአይሁዳውያን ከተሞች አልነበሩም።
ወይም “ሐዲስ።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ቀንበሬን አብራችሁኝ ተሸከሙ።”
ወይም “ደቀ መዛሙርቴም ሁኑ።”
“ልዝብ፤ ለስላሳ፤ ሻካራ ያልሆነ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “ለነፍሳችሁም።”
ወይም “ለመሸከም የማያስቸግር።”