የማቴዎስ ወንጌል 15:1-39
15 ከዚያም ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት+ ወደ ኢየሱስ ቀርበው እንዲህ አሉት፦
2 “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ የሚጥሱት ለምንድን ነው? ለምሳሌ፣ ሊበሉ ሲሉ እጃቸውን አይታጠቡም።”*+
3 እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተ ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ትእዛዝ የምትጥሱት ለምንድን ነው?+
4 ለምሳሌ አምላክ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’+ እንዲሁም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ* ይገደል’ ብሏል።+
5 እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘ማንኛውም ሰው አባቱን ወይም እናቱን “እናንተን መጦር የምችልበት፣ ያለኝ ነገር ሁሉ ለአምላክ የተወሰነ ስጦታ ነው”+ ካለ
6 አባቱን የማክበር ግዴታ የለበትም።’ በመሆኑም ለወጋችሁ ስትሉ የአምላክን ቃል ሽራችኋል።+
7 እናንተ ግብዞች፣ ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፦+
8 ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው።
9 የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’”+
10 ከዚያም ሕዝቡን ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ስሙ፤ ደግሞም ይህን ቃል አስተውሉ፦+
11 ሰውን የሚያረክሰው ወደ አፉ የሚገባው አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የሚያረክሰው ከአፉ የሚወጣው ነው።”+
12 ከዚያም ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው “ፈሪሳውያን በተናገርከው ነገር ቅር እንደተሰኙ አውቀሃል?” አሉት።+
13 እሱም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል።
14 ተዉአቸው፤ እነሱ ዕውር መሪዎች ናቸው። ስለዚህ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።”+
15 ጴጥሮስም መልሶ “ምሳሌውን አብራራልን” አለው።
16 በዚህ ጊዜ እንዲህ አላቸው፦ “እናንተም እስካሁን ማስተዋል ተስኗችኋል?+
17 ወደ አፍ የሚገባ ሁሉ ወደ ሆድ እንደሚዘልቅና ከዚያም ወጥቶ ወደ ጉድጓድ እንደሚገባ አታውቁም?
18 ይሁን እንጂ ከአፍ የሚወጣ ሁሉ ከልብ ይወጣል፤ ሰውንም የሚያረክሰው ይህ ነው።+
19 ለምሳሌ ከልብ ክፉ ሐሳብ ይወጣል፦+ ግድያ፣ ምንዝር፣ የፆታ ብልግና፣* ሌብነት፣ በሐሰት መመሥከርና ስድብ።
20 ሰውን የሚያረክሱት እነዚህ ነገሮች ናቸው፤ እጅን ሳይታጠቡ* መብላት ግን ሰውን አያረክስም።”
21 ኢየሱስ ከዚያ ወጥቶ ወደ ጢሮስና ሲዶና አካባቢ ሄደ።+
22 በዚያ ክልል የምትኖር አንዲት ፊንቄያዊት* ሴት መጥታ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልኝ። ልጄን ጋኔን ስለያዛት ክፉኛ እየተሠቃየች ነው” ብላ ጮኸች።+
23 እሱ ግን ምንም መልስ አልሰጣትም። ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው “ይህች ሴት ከኋላችን እየተከተለች ስለምትጮኽ እባክህ አሰናብታት” እያሉ ይለምኑት ጀመር።
24 እሱም መልሶ “እኔ የተላክሁት ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች እንጂ ለሌላ ለማንም አይደለም” አለ።+
25 ሴትየዋ ግን ቀርባ “ጌታ ሆይ፣ እርዳኝ!” እያለች ሰገደችለት።*
26 እሱም መልሶ “የልጆችን ዳቦ ወስዶ ለቡችሎች መጣል ተገቢ አይደለም” አለ።
27 እሷም “አዎ ጌታ ሆይ፣ ግን እኮ ቡችሎችም ከጌቶቻቸው ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለች።+
28 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ መልሶ “አንቺ ሴት፣ እምነትሽ ታላቅ ነው፤ በይ እንደ ፍላጎትሽ ይሁንልሽ” አላት። ልጇም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ተፈወሰች።
29 ኢየሱስ ከዚያ ተነስቶ ወደ ገሊላ ባሕር+ አቅራቢያ መጣ፤ ወደ ተራራ ወጥቶም ተቀመጠ።
30 በዚህ ጊዜ እጅግ ብዙ ሰዎች አንካሶችን፣ ሽባዎችን፣ ዓይነ ስውሮችን፣ ዱዳዎችንና ሌሎች በርካታ ሕመምተኞችን ይዘው ወደ እሱ በመምጣት እግሩ ሥር አስቀመጧቸው፤ እሱም ፈወሳቸው።+
31 ሕዝቡም ዱዳዎች ሲናገሩ፣ ሽባዎች ሲፈወሱ፣ አንካሶች ሲራመዱና ዓይነ ስውሮች ሲያዩ ተመልክተው እጅግ ተደነቁ፤ የእስራኤልንም አምላክ አከበሩ።+
32 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ እሱ ጠርቶ “እነዚህ ሰዎች ሦስት ቀን ሙሉ ከእኔ ጋር ስለቆዩና የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ።+ እንዲሁ ጦማቸውን ልሰዳቸው አልፈልግም፤ መንገድ ላይ ዝለው ሊወድቁ ይችላሉ” አላቸው።+
33 ደቀ መዛሙርቱ ግን “በዚህ ገለልተኛ ስፍራ ይህን ሁሉ ሕዝብ ሊያጠግብ የሚችል በቂ ዳቦ ከየት እናገኛለን?” አሉት።+
34 በዚህ ጊዜ ኢየሱስ “ስንት ዳቦ አላችሁ?” አላቸው። እነሱም “ሰባት ዳቦና ጥቂት ትናንሽ ዓሣዎች” አሉት።
35 እሱም ሕዝቡ መሬት ላይ እንዲቀመጥ ካዘዘ በኋላ
36 ሰባቱን ዳቦና ዓሣዎቹን ወሰደ፤ ካመሰገነ በኋላም ቆርሶ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው፤ ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ ለሕዝቡ ሰጡ።+
37 ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ ከዚያም የተረፈውን ቁርስራሽ ሰበሰቡ፤ ቁርስራሹም ሰባት ትላልቅ ቅርጫት ሙሉ ሆነ።+
38 የበሉትም ከሴቶችና ከትናንሽ ልጆች ሌላ 4,000 ወንዶች ነበሩ።
39 በመጨረሻም ሕዝቡን ካሰናበተ በኋላ ጀልባ ተሳፍሮ ወደ መጌዶን ክልል መጣ።+