የማቴዎስ ወንጌል 20:1-34

  • የወይን እርሻ ሠራተኞችና የተቀበሉት ክፍያ (1-16)

  • ኢየሱስ እንደሚሞት በድጋሚ ተናገረ (17-19)

  • በአምላክ መንግሥት ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው ጠየቁ (20-28)

    • ኢየሱስ የመጣው ለብዙዎች ቤዛ ሊሆን ነው (28)

  • ሁለት ዓይነ ስውሮች ተፈወሱ (29-34)

20  “መንግሥተ ሰማያት በወይን እርሻው ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን ለመቅጠር ማልዶ ከወጣ የእርሻ ባለቤት ጋር ይመሳሰላል።+  በቀን አንድ ዲናር* ሊከፍላቸው ከተዋዋለ በኋላ ሠራተኞቹን ወደ ወይን እርሻው ላካቸው።  በሦስት ሰዓት ገደማም ወጥቶ በገበያ ቦታ ሥራ ፈተው የቆሙ ሌሎች ሰዎች አየ፤  እነዚህንም ሰዎች ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሂዱ፤ ተገቢውንም ክፍያ እከፍላችኋለሁ’ አላቸው።  እነሱም ሄዱ። ዳግመኛም በስድስት ሰዓትና በዘጠኝ ሰዓት ገደማ ወጥቶ እንዲሁ አደረገ።  በመጨረሻም በ11 ሰዓት ገደማ ወጥቶ ቆመው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አገኘና ‘ቀኑን ሙሉ ሥራ ፈታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው?’ አላቸው።  እነሱም ‘የሚቀጥረን ሰው ስላጣን ነው’ ሲሉ መለሱለት። እሱም ‘እናንተም ወደ ወይኑ እርሻ ሄዳችሁ ሥሩ’ አላቸው።  “በመሸም ጊዜ የወይኑ እርሻ ባለቤት የሠራተኞቹን ተቆጣጣሪ ‘ሠራተኞቹን ጠርተህ በመጨረሻ ከተቀጠሩት አንስቶ በመጀመሪያ እስከተቀጠሩት ድረስ ደሞዛቸውን ክፈላቸው’+ አለው።  በ11 ሰዓት የተቀጠሩት ሰዎች መጥተው እያንዳንዳቸው አንድ ዲናር* ተቀበሉ። 10  በመሆኑም በመጀመሪያ የተቀጠሩት ሲመጡ እነሱ የበለጠ የሚከፈላቸው መስሏቸው ነበር፤ ነገር ግን እነሱም የተከፈላቸው አንድ አንድ ዲናር* ነበር። 11  ክፍያውን ሲቀበሉ በእርሻው ባለቤት ላይ ማጉረምረም ጀመሩ፤ 12  እንዲህም አሉት፦ ‘እነዚህ በመጨረሻ የተቀጠሩት ሰዎች አንድ ሰዓት ብቻ ነው የሠሩት፤ ያም ሆኖ አንተ ቀኑን ሙሉ ስንደክምና በፀሐይ ስንቃጠል ከዋልነው ከእኛ ጋር እኩል አደረግካቸው!’ 13  እሱ ግን ከመካከላቸው ለአንዱ እንዲህ አለው፦ ‘የኔ ወንድም፣ ምንም የበደልኩህ ነገር የለም። የተስማማነው አንድ ዲናር* እንድከፍልህ ነው፣ አይደለም እንዴ?+ 14  ስለዚህ ድርሻህን ይዘህ ሂድ። በመጨረሻ ለተቀጠሩት ለእነዚህ ሰዎችም ለአንተ የሰጠሁትን ያህል መስጠት ፈለግኩ። 15  በገዛ ገንዘቤ የፈለግኩትን የማድረግ መብት የለኝም? ወይስ እኔ ደግ* በመሆኔ ዓይንህ ተመቀኘ?’*+ 16  ስለሆነም ኋለኞች ፊተኞች፣ ፊተኞች ደግሞ ኋለኞች ይሆናሉ።”+ 17  ወደ ኢየሩሳሌም እየወጡ ሳሉ ኢየሱስ 12ቱን ደቀ መዛሙርት ለብቻቸው ነጥሎ ወሰዳቸው፤ በመንገድ ላይ ሳሉም እንዲህ አላቸው፦+ 18  “እነሆ፣ ወደ ኢየሩሳሌም እየወጣን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል። እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤+ 19  እንዲሁም እንዲያፌዙበት፣ እንዲገርፉትና በእንጨት ላይ እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል፤+ እሱም በሦስተኛው ቀን ይነሳል።”+ 20  ከዚያም የዘብዴዎስ+ ሚስት ከልጆቿ ጋር ወደ እሱ ቀርባ እየሰገደች* አንድ ነገር እንዲያደርግላት ለመነችው።+ 21  እሱም “ምንድን ነው የፈለግሽው?” አላት። እሷም መልሳ “በመንግሥትህ እነዚህን ሁለቱን ልጆቼን፣ አንዱን በቀኝህ አንዱን ደግሞ በግራህ አስቀምጥልኝ” አለችው።+ 22  ኢየሱስም መልሶ “የምትለምኑትን አታውቁም። እኔ በቅርቡ የምጠጣውን ጽዋ ልትጠጡ ትችላላችሁ?” አላቸው።+ እነሱም “እንችላለን” አሉት። 23  እሱም “በእርግጥ የእኔን ጽዋ ትጠጣላችሁ፤+ በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ ግን አባቴ ላዘጋጀላቸው የሚሰጥ እንጂ በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም” አላቸው።+ 24  የቀሩት አሥሩ ይህን ሲሰሙ በሁለቱ ወንድማማቾች ላይ ተቆጡ።+ 25  ሆኖም ኢየሱስ ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “የዚህ ዓለም ገዢዎች በሕዝባቸው ላይ ሥልጣናቸውን እንደሚያሳዩ፣ ታላላቅ ሰዎችም በኃይል እንደሚገዟቸው ታውቃላችሁ።+ 26  በእናንተ መካከል ግን እንዲህ መሆን የለበትም፤+ ከመካከላችሁ ታላቅ መሆን የሚፈልግ ሁሉ አገልጋያችሁ ሊሆን ይገባል፤+ 27  እንዲሁም ከመካከላችሁ ፊተኛ መሆን የሚፈልግ ሁሉ ባሪያችሁ ሊሆን ይገባል።+ 28  የሰው ልጅም የመጣው ለማገልገልና+ በብዙ ሰዎች ምትክ ሕይወቱን* ቤዛ አድርጎ ለመስጠት+ እንጂ እንዲገለገል አይደለም።” 29  ከኢያሪኮ ወጥተው እየሄዱ ሳሉ እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተለው። 30  በዚህ ጊዜ መንገድ ዳር የተቀመጡ ሁለት ዓይነ ስውሮች ኢየሱስ በዚያ እያለፈ መሆኑን ሲሰሙ “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ጮኹ።+ 31  ሆኖም ሕዝቡ ዝም እንዲሉ ገሠጿቸው፤ እነሱ ግን “ጌታ ሆይ፣ የዳዊት ልጅ፣ ምሕረት አድርግልን!” እያሉ ይበልጥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ጮኹ። 32  ኢየሱስም ቆም ብሎ ጠራቸውና “ምን እንዳደርግላችሁ ትፈልጋላችሁ?” አላቸው። 33  እነሱም “ጌታ ሆይ፣ ዓይናችንን አብራልን” አሉት። 34  ኢየሱስም በጣም አዘነላቸውና ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፤+ ወዲያውኑም ማየት ቻሉ፤ ከዚያም ተከተሉት።

የግርጌ ማስታወሻ

ለ14ን ተመልከት።
ለ14ን ተመልከት።
ለ14ን ተመልከት።
ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ለጋስ።”
ቃል በቃል “መጥፎ ሆነ፤ ክፉ ሆነ።”
ወይም “ወደ እሱ ቀርባ እጅ እየነሳች።”
ወይም “ነፍሱን።”