የማቴዎስ ወንጌል 21:1-46

  • ኢየሱስ እንደ ድል አድራጊ ሆኖ ገባ (1-11)

  • ኢየሱስ ነጋዴዎችን ከቤተ መቅደሱ አባረረ (12-17)

  • የበለስ ዛፏ ተረገመች (18-22)

  • የኢየሱስን ሥልጣን ተገዳደሩ (23-27)

  • የሁለቱ ልጆች ምሳሌ (28-32)

  • ነፍሰ ገዳይ የሆኑት ገበሬዎች ምሳሌ (33-46)

    • የማዕዘን ራስ ድንጋይ ተናቀ (42)

21  ወደ ኢየሩሳሌም በተቃረቡና በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወደምትገኘው ወደ ቤተፋጌ በደረሱ ጊዜ ኢየሱስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ላከ፤+  እንዲህም አላቸው፦ “ወደዚያ ወደምታዩት መንደር ሂዱ፤ እዚያ እንደደረሳችሁም አንዲት የታሰረች አህያ ከነውርንጭላዋ ታገኛላችሁ። ፈታችሁ ወደ እኔ አምጧቸው።  ማንም ሰው ቢጠይቃችሁ ‘ጌታ ይፈልጋቸዋል’ በሉት። በዚህ ጊዜ ወዲያውኑ ይልካቸዋል።”  ይህም የሆነው ነቢዩ እንዲህ ብሎ የተናገረው ይፈጸም ዘንድ ነው፦  “ለጽዮን ልጅ እንዲህ በሏት፦ ‘እነሆ ንጉሥሽ+ ገር+ ሆኖ በአህያ፣ አዎ በአህያይቱ ግልገል በውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ይመጣል።’”+  ስለዚህ ደቀ መዛሙርቱ ሄደው ኢየሱስ እንዳዘዛቸው አደረጉ።+  አህያይቱንና ውርንጭላዋን አምጥተው መደረቢያዎቻቸውን በላያቸው ላይ አደረጉ፤ እሱም ተቀመጠባቸው።*+  ከሕዝቡ መካከል አብዛኞቹ መደረቢያቸውን በመንገዱ ላይ አነጠፉ፤+ ሌሎች ደግሞ ከዛፎች ላይ ቅርንጫፎች እየቆረጡ በመንገዱ ላይ ያነጥፉ ነበር።  በተጨማሪም ከፊት ከፊቱ የሚሄደውና ከኋላው የሚከተለው ሕዝብ “የዳዊትን ልጅ እንድታድነው እንለምንሃለን!*+ በይሖዋ* ስም የሚመጣ የተባረከ ነው!+ በሰማይ የምትኖረው ሆይ፣ እንድታድነው እንለምንሃለን!”+ ብሎ ይጮኽ ነበር። 10  ወደ ኢየሩሳሌም በገባ ጊዜም “ይህ ሰው ማን ነው?” በማለት መላዋ ከተማ ታወከች። 11  ሕዝቡም “ይህ በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት የመጣው ነቢዩ ኢየሱስ ነው!”+ ይል ነበር። 12  ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ገብቶ በቤተ መቅደሱ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አስወጣ፤ የገንዘብ መንዛሪዎችን ጠረጴዛዎችና የርግብ ሻጮችን መቀመጫዎችም ገለባበጠ።+ 13  እንዲህም አላቸው፦ “‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይባላል’ ተብሎ ተጽፏል፤+ እናንተ ግን የዘራፊዎች ዋሻ አድርጋችሁታል።”+ 14  ቤተ መቅደሱ ውስጥ እንዳለም ዓይነ ስውሮችና አንካሶች ወደ እሱ መጡ፤ እሱም ፈወሳቸው። 15  የካህናት አለቆችና ጸሐፍት ያደረጋቸውን አስደናቂ ነገሮች እንዲሁም በቤተ መቅደሱ ውስጥ “የዳዊትን ልጅ እንድታድነው እንለምንሃለን!”+ እያሉ የሚጮኹትን ልጆች ባዩ ጊዜ ተቆጥተው+ 16  “እነዚህ የሚሉትን ትሰማለህ?” አሉት። ኢየሱስም “አዎ እሰማለሁ። ‘ከልጆችና ከሕፃናት አፍ ምስጋና አዘጋጀህ’ የሚለውን ከቶ አላነበባችሁም?” አላቸው።+ 17  ከዚያም ትቷቸው ከከተማዋ ከወጣ በኋላ ወደ ቢታንያ ሄደ፤ እዚያም አደረ።+ 18  በማለዳም ወደ ከተማዋ እየተመለሰ ሳለ ተራበ።+ 19  በመንገድ ዳር አንድ የበለስ ዛፍ አየና ወደ እሷ ሄደ፤ ሆኖም ከቅጠል በቀር ምንም ስላላገኘባት+ “ከእንግዲህ ወዲህ ፍሬ አይገኝብሽ” አላት።+ የበለስ ዛፏም ወዲያውኑ ደረቀች። 20  ደቀ መዛሙርቱ ይህን ባዩ ጊዜ ተገርመው “የበለስ ዛፏ እንዲህ በአንዴ ልትደርቅ የቻለችው እንዴት ነው?” አሉ።+ 21  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ እምነት ካላችሁና ካልተጠራጠራችሁ እኔ በበለስ ዛፏ ላይ ያደረግኩትን ማድረግ ብቻ ሳይሆን ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነስተህ ወደ ባሕር ተወርወር’ ብትሉት እንኳ ይሆንላችኋል።+ 22  እምነት ካላችሁ በጸሎት የምትጠይቁትን ነገር ሁሉ ታገኛላችሁ።”+ 23  ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ እያስተማረ ሳለ የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ሽማግሌዎች ወደ እሱ መጥተው “እነዚህን ነገሮች የምታደርገው በምን ሥልጣን ነው? ይህን ሥልጣን የሰጠህስ ማን ነው?” አሉት።+ 24  ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “እኔም አንድ ነገር እጠይቃችኋለሁ። መልሱን ከነገራችሁኝ እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ እነግራችኋለሁ፦ 25  ዮሐንስ እንዲያጠምቅ ሥልጣን የሰጠው ማን ነው? አምላክ* ነው ወይስ ሰው?” እነሱ ግን እርስ በርሳቸው እንዲህ ይባባሉ ጀመር፦ “‘አምላክ’ ብንል ‘ታዲያ ለምን አላመናችሁትም?’ ይለናል፤+ 26  ‘ሰው’ ብንል ደግሞ ዮሐንስን ሁሉም እንደ ነቢይ ስለሚያየው ሕዝቡን እንፈራለን።” 27  ስለዚህ ለኢየሱስ “አናውቅም” ብለው መለሱለት። እሱ ደግሞ እንዲህ አላቸው፦ “እኔም እነዚህን ነገሮች በምን ሥልጣን እንደማደርግ አልነግራችሁም። 28  “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው ሁለት ልጆች ነበሩት። ወደ መጀመሪያው ልጁ ሄዶ ‘ልጄ ሆይ፣ ዛሬ ወደ ወይኑ እርሻ ሄደህ ሥራ’ አለው። 29  ልጁም መልሶ ‘አልሄድም’ አለው፤ በኋላ ግን ጸጸተውና ሄደ። 30  ሁለተኛውንም ቀርቦ እንደዚሁ አለው። ልጁም መልሶ ‘እሺ አባዬ፣ እሄዳለሁ’ አለው፤ ግን አልሄደም። 31  ከሁለቱ የአባቱን ፈቃድ የፈጸመው የትኛው ነው?” እነሱም “የመጀመሪያው” አሉ። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እውነት እላችኋለሁ፣ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች ወደ አምላክ መንግሥት በመግባት ረገድ ይቀድሟችኋል። 32  ዮሐንስ የጽድቅን መንገድ ሊያሳያችሁ መጣ፤ እናንተ ግን አላመናችሁትም። ይሁን እንጂ ቀረጥ ሰብሳቢዎችና ዝሙት አዳሪዎች አመኑት፤+ እናንተ ይህን አይታችሁም እንኳ ጸጸት ተሰምቷችሁ እሱን ለማመን አልፈለጋችሁም። 33  “ሌላም ምሳሌ ስሙ፦ የወይን እርሻ+ ያለማ አንድ ባለ ርስት ነበር፤ ዙሪያውንም አጠረው፤ በዚያም የወይን መጭመቂያ ቆፈረ እንዲሁም ማማ ሠራ፤+ ከዚያም ለገበሬዎች አከራይቶ ወደ ሌላ አገር ሄደ።+ 34  ፍሬው የሚሰበሰብበት ወቅት ሲደርስ ድርሻውን እንዲያመጡለት ባሪያዎቹን ወደ ገበሬዎቹ ላከ። 35  ገበሬዎቹ ግን ባሪያዎቹን ይዘው አንዱን ደበደቡት፤ ሌላውን ገደሉት፤ ሌላውን ደግሞ በድንጋይ ወገሩት።+ 36  ከበፊቶቹ የሚበዙ ሌሎች ባሪያዎች በድጋሚ ላከ፤ ይሁንና በእነሱም ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ፈጸሙባቸው።+ 37  በመጨረሻም ‘መቼም ልጄን ያከብሩታል’ በማለት ልጁን ላከው። 38  ገበሬዎቹ ልጁን ሲያዩት እርስ በርሳቸው ‘ወራሹ ይሄ ነው።+ ኑ እንግደለው፤ ርስቱንም እንውረስ!’ ተባባሉ። 39  ስለዚህ ያዙትና ከወይን እርሻው ጎትተው በማውጣት ገደሉት።+ 40  እንግዲህ የወይኑ እርሻ ባለቤት ሲመጣ እነዚህን ገበሬዎች ምን የሚያደርጋቸው ይመስላችኋል?” 41  የካህናት አለቆቹና የሕዝቡ ሽማግሌዎችም “ክፉዎች ስለሆኑ ከባድ ጥፋት ያደርስባቸዋል፤ ከዚያም የወይን እርሻውን፣ ፍሬውን በወቅቱ ለሚያስረክቡት ለሌሎች ገበሬዎች ያከራያል” አሉት። 42  ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እንዲህ የሚለውን የቅዱሳን መጻሕፍት ቃል አላነበባችሁም? ‘ግንበኞች የናቁት ድንጋይ፣ የማዕዘን ራስ ድንጋይ* ሆነ።+ ይህ የይሖዋ* ሥራ ነው፤ ለዓይናችንም ድንቅ ነው።’+ 43  የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል የምላችሁ ለዚህ ነው። 44  በተጨማሪም በዚህ ድንጋይ ላይ የሚወድቅ ይሰባበራል።+ ድንጋዩ የሚወድቅበት ሰው ሁሉ ደግሞ ይደቅቃል።”+ 45  የካህናት አለቆቹና ፈሪሳውያኑ ምሳሌዎቹን በሰሙ ጊዜ ስለ እነሱ እንደተናገረ ገባቸው።+ 46  ሊይዙት* ይፈልጉ የነበረ ቢሆንም ሕዝቡን ፈሩ፤ ምክንያቱም ሕዝቡ እንደ ነቢይ ያየው ነበር።+

የግርጌ ማስታወሻ

“ተቀመጠባቸው” የሚለው ቃል በመደረቢያዎቹ ላይ እንደተቀመጠ ያሳያል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ግሪክኛ፣ ሆሳዕና።
ቃል በቃል “ሰማይ።”
ቃል በቃል “የማዕዘኑ ራስ።” እዚህ ላይ የገባው ግሪክኛ ቃል ሁለት የሕንጻ ግድግዳዎች የሚገናኙበት ማዕዘን አናት ላይ የሚቀመጥ ድንጋይን ያመለክታል።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ሊያስሩት።”