ምሳሌ 10:1-32
10 የሰለሞን ምሳሌዎች።+
ጥበበኛ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል፤+ሞኝ ልጅ ግን እናቱን ያሳዝናል።
2 በክፋት የተገኘ ሀብት ምንም ፋይዳ የለውም፤ጽድቅ ግን ከሞት ይታደጋል።+
3 ይሖዋ ጻድቅ ሰው እንዲራብ* አያደርግም፤+የክፉዎችን ምኞት ግን ያጨናግፋል።
4 ሥራ የፈቱ እጆች ያደኸያሉ፤+ትጉ እጆች ግን ብልጽግና ያስገኛሉ።+
5 ጥልቅ ማስተዋል ያለው ልጅ እህሉን በበጋ ይሰበስባል፤አሳፋሪ ልጅ ግን በመከር ወቅት ለጥ ብሎ ይተኛል።+
6 በረከት በጻድቅ ራስ ላይ ነው፤+የክፉዎች አፍ ግን የዓመፅ ዕቅዳቸውን ይሰውራል።
7 የጻድቅ መታሰቢያ* በረከት ያስገኛል፤+የክፉዎች ስም ግን ይጠፋል።*+
8 ጥበበኛ ልብ ያለው ሰው መመሪያዎችን* ይቀበላል፤+በሞኝነት የሚናገር ሰው ግን ጥፋት ይደርስበታል።+
9 ንጹሕ አቋሙን* ጠብቆ የሚሄድ ያለስጋት ይመላለሳል፤+መንገዱን ጠማማ የሚያደርግ ግን ይጋለጣል።+
10 በተንኮል የሚጣቀስ ሐዘን ያመጣል፤+በሞኝነት የሚናገር ሰውም ጥፋት ይደርስበታል።+
11 የጻድቅ አፍ የሕይወት ምንጭ ነው፤+የክፉዎች አፍ ግን የዓመፅ ዕቅዳቸውን ይሰውራል።+
12 ጥላቻ ጭቅጭቅ ያስነሳል፤ፍቅር ግን በደልን ሁሉ ይሸፍናል።+
13 አስተዋይ በሆነ ሰው ከንፈር ጥበብ ትገኛለች፤+በትር ግን ማስተዋል* ለጎደለው ሰው ጀርባ ነው።+
14 ጥበበኞች እውቀትን እንደ ውድ ሀብት ያከማቻሉ፤+የሞኝ ሰው አፍ ግን ጥፋት ይጋብዛል።+
15 የባለጸጋ ሀብት* የተመሸገ ከተማው ነው።
ድሆችን የሚያጠፋቸው ድህነታቸው ነው።+
16 የጻድቅ ሰው ሥራ ወደ ሕይወት ይመራል፤የክፉ ሰው ፍሬ ግን ወደ ኃጢአት ይመራል።+
17 ተግሣጽን የሚቀበል ለሌሎች የሕይወት መንገድ ይሆናል፤*ወቀሳን ችላ የሚል ግን ሌሎች መንገድ እንዲስቱ ያደርጋል።
18 ጥላቻውን የሚሸፋፍን ሰው ሐሰት ይናገራል፤+ተንኮል ያዘለ ወሬ* የሚያስፋፋ ሰውም ሞኝ ነው።
19 ከቃላት ብዛት ስህተት አይታጣም፤+ከንፈሩን የሚገታ ግን ልባም ሰው ነው።+
20 የጻድቅ አንደበት ጥራት ያለው ብር ነው፤+የክፉ ሰው ልብ ግን እርባና የለውም።
21 የጻድቅ ከንፈሮች ብዙዎችን ይመግባሉ፤*+ሞኞች ግን ማስተዋል ስለሚጎድላቸው ይሞታሉ።+
22 የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤+እሱም ከበረከቱ ጋር ሥቃይን* አይጨምርም።
23 አሳፋሪ ምግባር መፈጸም ለሞኝ ሰው እንደ ጨዋታ ነው፤ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰው ግን ጥበበኛ ነው።+
24 ክፉ ሰው የፈራው ነገር ይደርስበታል፤ጻድቅ ግን የተመኘውን ያገኛል።+
25 አውሎ ነፋስ ሲያልፍ ክፉ ሰው ተጠርጎ ይወሰዳል፤+ጻድቅ ግን ለዘላለም እንደሚኖር መሠረት ነው።+
26 ኮምጣጤ ጥርስን፣ ጭስም ዓይንን እንደሚጎዳ፣ሰነፍም ለሚልከው ሰው* እንዲሁ ነው።
27 ይሖዋን መፍራት ዕድሜን ያስረዝማል፤+የክፉዎች ዕድሜ ግን በአጭሩ ይቀጫል።+
28 የጻድቃን ተስፋ ደስታ ያስገኛል፤+የክፉዎች ተስፋ ግን መና ይቀራል።+
29 የይሖዋ መንገድ፣ ያለነቀፋ ለሚመላለስ ሰው መሸሸጊያ ነው፤+ለክፉ አድራጊዎች ግን መጥፊያቸው ነው።+
30 ጻድቅ ሰው ምንም ነገር አይጥለውም፤+ክፉዎች ግን በምድር ላይ መኖራቸውን አይቀጥሉም።+
31 የጻድቅ አፍ ጥበብን ያፈልቃል፤*ጠማማ ምላስ ግን ትቆረጣለች።
32 የጻድቅ ሰው ከንፈሮች ደስ የሚያሰኘው ነገር ምን እንደሆነ ያውቃሉ፤የክፉዎች አፍ ግን ጠማማ ነው።