ምሳሌ 11:1-31

  • ‘ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ጥበብ ትገኛለች’ (2)

  • ከሃዲ ሰው ሌሎችን ለጥፋት ይዳርጋል (9)

  • ‘ብዙ አማካሪዎች ባሉበት ስኬት ይገኛል’ (14)

  • “ለጋስ ሰው ይበለጽጋል” (25)

  • “በሀብቱ የሚታመን ሰው ይወድቃል” (28)

11  አባይ* ሚዛን በይሖዋ ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ትክክለኛ መለኪያ* ግን ደስ ያሰኘዋል።+   እብሪት ከመጣ ውርደት ይከተላል፤+ልካቸውን በሚያውቁ ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።+   ቅኖችን ንጹሕ አቋማቸው* ይመራቸዋል፤+ከዳተኞችን ግን ተንኮላቸው ያጠፋቸዋል።+   በቁጣ ቀን ሀብት ፋይዳ አይኖረውም፤*+ጽድቅ ግን ከሞት ይታደጋል።+   ነቀፋ የሌለበት ሰው የሚሠራው ጽድቅ መንገዱን ቀና ያደርግለታል፤ክፉ ሰው ግን በገዛ ክፋቱ ይወድቃል።+   ቅኖችን ጽድቃቸው ያድናቸዋል፤+ከዳተኞች ግን በገዛ ምኞታቸው ይጠመዳሉ።+   ክፉ ሰው ሲሞት ተስፋው መና ይቀራል፤በኃይሉ ተመክቶ ተስፋ የሚያደርገው ነገርም ይጠፋል።+   ጻድቅ ከመከራ ይድናል፤ክፉ ሰው ደግሞ በእሱ ቦታ ይተካል።+   ከሃዲ ሰው* በአፉ ባልንጀራውን ያጠፋል፤ጻድቃን ግን በእውቀት ይድናሉ።+ 10  በጻድቃን ጥሩነት ከተማ ሐሴት ታደርጋለች፤ክፉዎች ሲጠፉም እልልታ ይሆናል።+ 11  በቅኖች በረከት ከተማ ከፍ ከፍ ትላለች፤+የክፉዎች አፍ ግን ያፈራርሳታል።+ 12  ማስተዋል* የጎደለው ሰው ባልንጀራውን ይንቃል፤*ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰው ግን ዝም ይላል።+ 13  ስም የሚያጠፋ ሰው እየዞረ የሌሎችን ሚስጥር ይገልጣል፤+እምነት የሚጣልበት ሰው* ግን ሚስጥር ይጠብቃል።* 14  ጥበብ ያለበት አመራር ሲጓደል ሕዝብ ይጎዳል፤ብዙ አማካሪዎች ባሉበት ግን ስኬት* ይገኛል።+ 15  የማያውቀው ሰው ለወሰደው ብድር ዋስ የሚሆን* ጉዳት ላይ መውደቁ አይቀርም፤+እጅ በመምታት* ቃል ከመግባት የሚቆጠብ* ግን ምንም አይደርስበትም። 16  ሞገስ ያላት* ሴት ክብር ታገኛለች፤+ጨካኞች ግን ሀብት ያካብታሉ። 17  ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል፤*+ጨካኝ ሰው ግን በራሱ ላይ መከራ* ያመጣል።+ 18  ክፉ ሰው የሚያገኘው ደሞዝ እርባና የለውም፤+ጽድቅን የሚዘራ ግን እውነተኛ ብድራት ያገኛል።+ 19  ለጽድቅ ጽኑ አቋም ያለው ሰው ሕይወት የማግኘት ተስፋ አለው፤+ክፋትን የሚያሳድድ ግን ለሞት መዳረጉ አይቀርም። 20  ይሖዋ ጠማማ ልብ ያላቸውን ሰዎች ይጸየፋል፤+ነቀፋ በሌለበት ጎዳና የሚመላለሱ ግን ደስ ያሰኙታል።+ 21  ይህን አትጠራጠር፦ ክፉ ሰው ከቅጣት አያመልጥም፤+የጻድቃን ልጆች ግን ይድናሉ። 22  ማስተዋልን የምትንቅ ቆንጆ ሴት፣በአሳማ አፍንጫ ላይ እንዳለ የወርቅ ቀለበት ናት። 23  የጻድቅ ምኞት መልካም ነገር ያስገኛል፤+የክፉ ሰው ተስፋ ግን ወደ ቁጣ ይመራል። 24  አንዱ በልግስና ይሰጣል፤* ሆኖም ተጨማሪ ያገኛል፤+ሌላው ደግሞ ለመስጠት ይሰስታል፤ ነገር ግን ለድህነት ይዳረጋል።+ 25  ለጋስ ሰው* ይበለጽጋል፤*+ሌሎችን የሚያረካም* እሱ ራሱ ይረካል።+ 26  እህል ለመሸጥ ፈቃደኛ ያልሆነውን ሕዝቡ ይረግመዋል፤የሚሸጠውን ግን ይባርከዋል። 27  መልካም ነገር ለማድረግ የሚተጋ ሞገስ ለማግኘት ይጥራል፤+መጥፎ ነገር ለማድረግ የሚፈልግ ግን ክፋቱ በራሱ ላይ እንደሚመጣ የተረጋገጠ ነው።+ 28  በሀብቱ የሚታመን ሰው ይወድቃል፤+ጻድቅ ግን እንዳማረ ቅጠል ይለመልማል።+ 29  ቤተሰቡ ላይ ችግር* የሚያመጣ ሰው ሁሉ ነፋስን ይወርሳል፤+ሞኝ ሰውም ጥበበኛ ልብ ላለው ሰው አገልጋይ ይሆናል። 30  የጻድቅ ፍሬ የሕይወት ዛፍ ነው፤+ነፍሳትንም* የሚማርክ ጥበበኛ ነው።+ 31  በእርግጥ ጻድቅ በምድር ላይ የሚገባውን ብድራት የሚቀበል ከሆነክፉውና ኃጢአተኛው የሚቀበሉት ብድራትማ ምንኛ የከፋ ይሆን!+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የተሟላ የድንጋይ መለኪያ።”
ወይም “የማታለያ።”
ምሳሌ 2:7 ላይ የሚገኘውን የግርጌ ማስታወሻ ተመልከት።
ወይም “ውድ ነገሮች ፋይዳ አይኖራቸውም።”
ወይም “አምላክ የለሽ ሰው።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ወይም “ባልንጀራውን ያቃልላል።”
ቃል በቃል “በመንፈሱ የታመነ ሰው።”
ቃል በቃል “ነገርን ይሰውራል።”
ወይም “መዳን።”
ቃል በቃል “(ቃል መግባት) የሚጠላ።”
ወይም “በመጨበጥ።”
ወይም “ተያዥ የሚሆን።”
ወይም “የምትወደድ።”
ወይም “ታማኝ ፍቅር የሚያሳይ ሰው ነፍሱን ይጠቅማል።”
ወይም “ውርደት።”
ቃል በቃል “አንዱ ይበትናል።”
ወይም “ለጋስ ነፍስ።”
ቃል በቃል “ይሰባል።”
ቃል በቃል “እንደ ልብ የሚያጠጣም።”
ወይም “ውርደት።”