ምሳሌ 12:1-28

  • ‘ወቀሳን የሚጠላ የማመዛዘን ችሎታ ይጎድለዋል’ (1)

  • “ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል” (18)

  • ‘ሰላምን የሚያራምዱ ደስታ አላቸው’ (20)

  • “ይሖዋ ውሸታም ከንፈሮችን ይጸየፋል” (22)

  • ጭንቀት ልብን ያዝላል (25)

12  ተግሣጽን የሚወድ እውቀትን ይወዳል፤+ወቀሳን የሚጠላ ግን የማመዛዘን ችሎታ* ይጎድለዋል።+   ጥሩ ሰው የይሖዋን ሞገስ ያገኛል፤ክፋት የሚያሴርን ሰው ግን እሱ ይፈርድበታል።+   በክፋት ጸንቶ መቆም የሚችል ሰው የለም፤+ጻድቅ ግን ፈጽሞ አይነቀልም።   ጥሩ ሚስት ለባሏ ዘውድ ናት፤+አሳፋሪ* ሚስት ግን አጥንቱ ውስጥ እንዳለ ንቅዘት ናት።+   የጻድቃን ሐሳብ ፍትሐዊ ነው፤የክፉዎች ምክር ግን አሳሳች ነው።   የክፉዎች ቃል ገዳይ ወጥመድ ነው፤*+የቅኖች አፍ ግን ይታደጋቸዋል።+   ክፉዎች ሲገለበጡ ደብዛቸው ይጠፋል፤የጻድቃን ቤት ግን ጸንቶ ይኖራል።+   ሰው አስተዋይ በሆነ አንደበቱ ይመሰገናል፤+ልቡ ጠማማ የሆነ ግን ይናቃል።+   የሚበላው* ሳይኖረው ራሱን ከፍ ከፍ ከሚያደርግ ሰው ይልቅአገልጋይ ኖሮት ራሱን ዝቅ አድርጎ የሚኖር ሰው ይሻላል።+ 10  ጻድቅ የቤት እንስሳቱን* ይንከባከባል፤+ክፉዎች ግን ርኅራኄያቸው እንኳ ጭካኔ ነው። 11  መሬቱን የሚያርስ ሰው የተትረፈረፈ ምግብ ያገኛል፤+ከንቱ ነገሮችን የሚያሳድድ ግን ማስተዋል* ይጎድለዋል። 12  ክፉ ሰው፣ ሌሎች መጥፎ ሰዎች ባጠመዱት ነገር ይቀናል፤የጻድቃን ሥር ግን ፍሬ ያፈራል። 13  መጥፎ ሰው በክፉ ንግግሩ ይጠመዳል፤+ጻድቅ ግን ከመከራ ያመልጣል። 14  ሰው ከአፉ ፍሬ መልካም ነገር ይጠግባል፤+የእጁ ሥራም ብድራት ይከፍለዋል። 15  የሞኝ መንገድ በራሱ ዓይን ትክክል ነው፤+ጥበበኛ ግን ምክር ይቀበላል።+ 16  ሞኝ ሰው ቁጣውን ወዲያውኑ* ይገልጻል፤+ብልህ ሰው ግን ስድብን ችላ ብሎ ያልፋል።* 17  ታማኝ ምሥክር እውነቱን* ይናገራል፤ውሸታም ምሥክር ግን ያታልላል። 18  ሳይታሰብበት የሚነገር ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤የጥበበኞች ምላስ ግን ፈውስ ነው።+ 19  እውነት የሚናገሩ ከንፈሮች ለዘላለም ጸንተው ይኖራሉ፤+ሐሰተኛ ምላስ ግን የሚቆየው ለቅጽበት ብቻ ነው።+ 20  ተንኮል በሚሸርቡ ሰዎች ልብ ውስጥ ማታለያ አለ፤ሰላምን የሚያራምዱ* ግን ደስተኞች ናቸው።+ 21  ጻድቅ ምንም ዓይነት ጉዳት አያገኘውም፤+የክፉዎች ሕይወት ግን በመከራ የተሞላ ይሆናል።+ 22  ይሖዋ ውሸታም ከንፈሮችን ይጸየፋል፤+በታማኝነት የሚመላለሱ ግን ደስ ያሰኙታል። 23  ብልህ ሰው እውቀቱን ይሰውራል፤የሞኝ ልብ ግን ሞኝነቱን ይዘከዝካል።+ 24  የትጉ ሰዎች እጅ ገዢ ትሆናለች፤+ሥራ ፈት እጆች ግን ለባርነት ይዳረጋሉ።+ 25  በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤*+መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።+ 26  ጻድቅ የግጦሽ መሬቱን በሚገባ ይቃኛል፤የክፉዎች መንገድ ግን እንዲባዝኑ ያደርጋቸዋል። 27  ሰነፍ ሰው አደኑን አሳድዶ አይዝም፤+ትጋት ግን የሰው ውድ ሀብት ነው። 28  የጽድቅ ጎዳና ወደ ሕይወት ይመራል፤+በጎዳናው ላይ ሞት የለም።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ማስተዋል።”
ወይም “አሳፋሪ ድርጊት የምትፈጽም።”
ቃል በቃል “ደም ለማፍሰስ ያደባል።”
ቃል በቃል “ዳቦ።”
ወይም “የቤት እንስሳቱን ነፍስ።”
ቃል በቃል “ልብ።”
ወይም “በዚያው ቀን።”
ቃል በቃል “ይሸፍናል።”
ቃል በቃል “ጽድቅ የሆነውን።”
ቃል በቃል “የሰላም አማካሪ የሆኑ።”
ወይም “የመንፈስ ጭንቀት ያስከትልበታል።”