ምሳሌ 21:1-31

  • ይሖዋ የንጉሥን ልብ ይመራል (1)

  • ፍትሕ መሥዋዕት ከማቅረብ ይሻላል (3)

  • ትጋት ለስኬት ያበቃል (5)

  • የችግረኛውን ጩኸት የማይሰማ ራሱም ሰሚ አያገኝም (13)

  • ይሖዋን የሚጻረር ጥበብ ከንቱ ነው (30)

21  የንጉሥ ልብ በይሖዋ እጅ እንዳለ ጅረት ነው።+ እሱ ደስ ወዳሰኘው አቅጣጫ ሁሉ ይመራዋል።+   ሰው መንገዱ ሁሉ ትክክል መስሎ ይታየዋል፤+ይሖዋ ግን ልብን ይመረምራል።*+   መሥዋዕት ከማቅረብ ይልቅትክክልና ፍትሐዊ የሆነ ነገር ማድረግ ይሖዋን ይበልጥ ደስ ያሰኘዋል።+   ትዕቢተኛ ዓይንና እብሪተኛ ልብየክፉዎች መብራት ናቸው፤ ደግሞም ኃጢአት ናቸው።+   የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል፤*+ችኩሎች ሁሉ ግን ለድህነት ይዳረጋሉ።+   በሐሰተኛ ምላስ የሚገኝ ውድ ሀብትወዲያው እንደሚጠፋ ጉም ነው፤ ገዳይ ወጥመድም ነው።*+   ክፉዎች ፍትሕን ማስፈን ስለማይፈልጉየሚፈጽሙት ግፍ ጠራርጎ ይወስዳቸዋል።+   የበደለኛ ሰው መንገድ ጠማማ ነው፤የንጹሕ ሰው ሥራ ግን ቀና ነው።+   ከጨቅጫቃ* ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖርበጣሪያ ማዕዘን ላይ መኖር ይሻላል።+ 10  ክፉ ሰው* መጥፎ ነገር ይመኛል፤+ለባልንጀራው ሞገስ አያሳይም።+ 11  ፌዘኛ ሲቀጣ ተሞክሮ የሌለው ሰው ይበልጥ ጥበበኛ ይሆናል፤ጥበበኛ ሰው ጥልቅ ማስተዋል ሲያገኝም እውቀት ይቀስማል።*+ 12  ጻድቅ የሆነው አምላክ፣ የክፉውን ቤት ልብ ብሎ ይመለከታል፤ክፉዎችንም ይጠፉ ዘንድ ይገለብጣቸዋል።+ 13  ችግረኛው የሚያሰማውን ጩኸት ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን ሁሉ፣እሱ ራሱ ይጮኻል፤ መልስም አያገኝም።+ 14  በድብቅ የተሰጠ ስጦታ ቁጣን ያበርዳል፤+በስውር የተሰጠ ጉቦም* ኃይለኛ ቁጣ እንዲከስም ያደርጋል። 15  ጻድቅ ፍትሐዊ ነገር ማድረግ ያስደስተዋል፤+ክፉ ድርጊት ለሚፈጽሙ ግን አስከፊ ነገር ነው። 16  ከማስተዋል መንገድ ወጥቶ የሚባዝን ሰው፣በሞት ከተረቱት ጋር ያርፋል።+ 17  ፈንጠዝያ* የሚወድ ሰው ይደኸያል፤+የወይን ጠጅና ዘይት የሚወድ ባለጸጋ አይሆንም። 18  ክፉ ሰው ለጻድቅ ቤዛ ነው፤ከዳተኛ የሆነ ሰውም በቅን ሰው ፋንታ ይወሰዳል።+ 19  ጨቅጫቃና* ቁጡ ከሆነች ሚስት ጋር ከመኖርበምድረ በዳ መኖር ይሻላል።+ 20  ውድ ሀብትና ምርጥ ዘይት በጥበበኛ ሰው ቤት ይገኛል፤+ሞኝ ሰው ግን ያለውን ያባክናል።*+ 21  ጽድቅንና ታማኝ ፍቅርን የሚከታተል ሰው ሁሉሕይወትን፣ ጽድቅንና ክብርን ያገኛል።+ 22  ጥበበኛ ሰው የኃያላን ሰዎች ከተማ ላይ ይወጣል፤*የሚታመኑበትንም ብርታት ያዳክማል።+ 23  አፉንና ምላሱን የሚጠብቅ፣ራሱን ከችግር ይጠብቃል።*+ 24  በእብሪት የመሰለውን የሚያደርግ ሰውእብሪተኛና ጉረኛ ይባላል።+ 25  ሰነፍ ሰው ምኞቱ ይገድለዋል፤እጆቹ መሥራት አይፈልጉምና።+ 26  ቀኑን ሙሉ በስግብግብነት ሲመኝ ይውላል፤ጻድቅ ግን ምንም ሳይሰስት ይሰጣል።+ 27  የክፉ ሰው መሥዋዕት አስጸያፊ ነው።+ በክፉ ዓላማ ተነሳስቶ* ሲያቀርብማ ምንኛ የከፋ ይሆናል! 28  ውሸታም ምሥክር ይጠፋል፤+በጥሞና የሚያዳምጥ ሰው ግን የምሥክርነት ቃሉ ተቀባይነት ያገኛል።* 29  ክፉ ሰው ኀፍረት የሚባል ነገር አያውቅም፤+የቅን ሰው አካሄድ ግን አስተማማኝ ነው።*+ 30  ይሖዋን የሚጻረር ጥበብ፣ ማስተዋልም ሆነ ምክር ከንቱ ነው።+ 31  ፈረስ ለጦርነት ቀን ይዘጋጃል፤+መዳን ግን ከይሖዋ ዘንድ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ውስጣዊ ዓላማን ይመረምራል።”
ወይም “ጥቅም ያስገኝለታል።”
“ሞትን ለሚሹ ወዲያው እንደሚጠፋ ጉም ነው” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከነዝናዛ።”
ወይም “የክፉ ሰው ነፍስ።”
ወይም “ምን ማድረግ እንዳለበት ያውቃል።”
ቃል በቃል “በጉያ የተሸጎጠ ጉቦም።”
ወይም “ደስታ።”
ወይም “ነዝናዛና።”
ቃል በቃል “ያለውን ይውጣል።”
ወይም “ከተማን ድል ያደርጋል።”
ወይም “ነፍሱን ከችግር ይጠብቃል።”
ወይም “አሳፋሪ ምግባር እያለው።”
ቃል በቃል “ለዘላለም ይናገራል።”
ወይም “ቅን ሰው ግን መንገዱን አስተማማኝ ያደርጋል።”