ምሳሌ 25:1-28
25 እነዚህም የይሁዳ ንጉሥ የሕዝቅያስ+ ሰዎች የጻፏቸው* የሰለሞን ምሳሌዎች ናቸው፦+
2 አንድን ጉዳይ መሰወር ለአምላክ ክብሩ ነው፤+ጉዳይን በሚገባ መመርመር ደግሞ ለነገሥታት ክብራቸው ነው።
3 ሰማያት ከፍ ያሉ እንደሆኑ፣ ምድርም ጥልቅ እንደሆነች ሁሉየንጉሥም ልብ አይመረመርም።
4 የብርን ቆሻሻ አስወግድ፤ሙሉ በሙሉም የጠራ ይሆናል።+
5 ክፉን ሰው ከንጉሥ ፊት አስወግድ፤ዙፋኑም በጽድቅ ይጸናል።+
6 በንጉሥ ፊት ራስህን ከፍ ከፍ አታድርግ፤+ታላላቅ ሰዎችም ባሉበት ስፍራ አትቀመጥ፤+
7 በተከበረ ሰው ፊት ከሚያዋርድህ
እሱ ራሱ “ወደዚህ ከፍ በል” ቢልህ ይሻላልና።+
8 ክስ ለመመሥረት አትቸኩል፤የኋላ ኋላ ባልንጀራህ ቢያዋርድህ ምን ይውጥሃል?+
9 ከባልንጀራህ ጋር ስለ ራስህ ጉዳይ ተሟገት፤+ሆኖም በሚስጥር የተነገረህን ጉዳይ* አትግለጥ፤+
10 አለዚያ የሚሰማህ ሰው ያዋርድሃል፤ያናፈስከውንም መጥፎ ወሬ* መመለስ አትችልም።
11 በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃልከብር በተሠራ ዕቃ ላይ* እንዳለ የወርቅ ፖም ነው።+
12 በጥበብ ወቀሳ የሚሰጥ ሰው፣ የሚሰማ ጆሮ ላለውእንደ ወርቅ ጉትቻና ከጥሩ ወርቅ እንደተሠራ ጌጥ ነው።+
13 ታማኝ መልእክተኛ ለላኩት ሰዎችበመከር ወቅት እንደሚገኝ የበረዶ ቅዝቃዜ ነው፤የጌታውን መንፈስ* ያድሳልና።+
14 የማይሰጠውን ስጦታ* እሰጣለሁ እያለ ጉራውን የሚነዛ ሰውዝናብ እንደማያመጣ ደመናና ነፋስ ነው።+
15 በትዕግሥት አዛዥን ማሸነፍ ይቻላል፤ለስላሳም አንደበት* አጥንትን ይሰብራል።+
16 ማር ካገኘህ የሚበቃህን ያህል ብቻ ብላ፤ከልክ በላይ ከበላህ ሊያስመልስህ ይችላልና።+
17 እንዳይሰለችህና እንዳይጠላህወደ ባልንጀራህ ቤት እግር አታብዛ።
18 በባልንጀራው ላይ በሐሰት የሚመሠክርእንደ ቆመጥ፣ እንደ ሰይፍና እንደ ሹል ፍላጻ ነው።+
19 በችግር ወቅት እምነት በማይጣልበት* ሰው መተማመን፣እንደተሰበረ ጥርስና እንደሰለለ እግር ነው።
20 ላዘነ ልብ የሚዘምር ሰው፣በብርድ ቀን ልብሱን እንደሚያወልቅ፣በሶዳም ላይ እንደተጨመረ ኮምጣጤ ነው።+
21 ጠላትህ* ቢራብ ምግብ ስጠው፤ቢጠማ ውኃ ስጠው፤+
22 ይህን ብታደርግ በራሱ ላይ ፍም ትከምራለህና፤*+ይሖዋም ወሮታ ይከፍልሃል።
23 የሰሜን ነፋስ ኃይለኛ ዝናብ ያመጣል፤ሐሜተኛ ምላስም የሰውን ፊት ያስቆጣል።+
24 ከጨቅጫቃ* ሚስት ጋር በአንድ ቤት ከመኖርበጣሪያ ማዕዘን ላይ መኖር ይሻላል።+
25 ቀዝቃዛ ውኃ የዛለችን ነፍስ* እንደሚያረካ ሁሉከሩቅ አገር የመጣ መልካም ወሬም እንዲሁ ነው።+
26 ለክፉ ሰው የሚንበረከክ* ጻድቅ፣እንደጨቀየ ምንጭና እንደተበከለ የውኃ ጉድጓድ ነው።
27 ብዙ ማር መብላት ጥሩ አይደለም፤+የራስንም ክብር መሻት አያስከብርም።+
28 ስሜቱን መቆጣጠር የማይችል ሰው*ቅጥር እንደሌላት የፈረሰች ከተማ ነው።+
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “የገለበጧቸውና ያጠናቀሯቸው።”
^ ወይም “የሌሎችን ሚስጥር።”
^ ወይም “ተንኮል ያዘለ አሉባልታ።”
^ ወይም “በብር መደብ ላይ።”
^ ወይም “ነፍስ።”
^ ቃል በቃል “የውሸት ስጦታ።”
^ ወይም “የለዘበም አንደበት።”
^ “በከዳተኛ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
^ ቃል በቃል “የሚጠላህ ሰው።”
^ የሰውየውን ልብ ለማለስለስና ግትር አቋሙን ለማለዘብ የሚደረግን ጥረት ያመለክታል።
^ ወይም “ከነዝናዛ።”
^ የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “በክፉ ሰው ፊት አቋሙን የሚያላላ።” ቃል በቃል “በክፉ ሰው ፊት የሚንገዳገድ።”
^ ወይም “መንፈሱን የማይገታ ሰው።”