ምሳሌ 7:1-27
7 ልጄ ሆይ፣ ቃሌን ጠብቅ፤ትእዛዛቴንም እንደ ውድ ሀብት ያዝ።+
2 ትእዛዛቴን ጠብቅ፤ በሕይወትም ትኖራለህ፤+መመሪያዬን* እንደ ዓይንህ ብሌን ጠብቅ።
3 በጣቶችህ ላይ እሰራቸው፤በልብህ ጽላት ላይ ጻፋቸው።+
4 ጥበብን “እህቴ ነሽ” በላት፤
ማስተዋልንም “ዘመዴ” ብለህ ጥራት፤
5 ጋጠወጥና*+ ባለጌ* ከሆነች ሴት፣እንዲሁም ከምትናገረው የሚያባብል* ቃል ይጠብቁሃል።+
6 በቤቴ መስኮት በፍርግርጉ በኩልአጮልቄ ወደ ታች ተመለከትኩ፤
7 ደግሞም ሞኞችን* ትክ ብዬ በማይበት ጊዜ፣በዚያ ከነበሩት ወንዶች ልጆች መካከል ማስተዋል* የጎደለውን አንድ ወጣት አየሁ።+
8 በቤቷ አቅራቢያ በሚገኝ መታጠፊያ አልፎወደ ቤቷ አቅጣጫ አመራ፤
9 ቀኑ መሸትሸት ብሎ ለዓይን ያዝ አድርጓል፤+የሌሊቱ ጨለማ እየተቃረበ ነበር።
10 ከዚያም እንደ ዝሙት አዳሪ* የለበሰችና+በልቧ አታላይ የሆነች ሴት ከእሱ ጋር ስትገናኝ አየሁ።
11 ሴትየዋ ጯኺና ማን አለብኝ ባይ ነች።+
ፈጽሞ ቤቷ አትቀመጥም።*
12 አንዴ በመንገድ፣ አንዴ በአደባባይ ትታያለች፤በየመንገዱ መታጠፊያም ታደባለች።+
13 አፈፍ አድርጋ ይዛ ሳመችው፤ያላንዳች ኀፍረትም እንዲህ አለችው፦
14 “የኅብረት መሥዋዕት ማቅረብ ነበረብኝ።+
ዛሬ ስእለቴን ፈጽሜአለሁ።
15 አንተን ለማግኘት የወጣሁት ለዚህ ነው፤አንተን ፍለጋ ወጣሁ፤ ደግሞም አገኘሁህ!
16 መኝታዬን ባማረ የአልጋ ልብስ፣ከግብፅ በመጣ በቀለማት ያሸበረቀ በፍታ አስጊጬዋለሁ።+
17 አልጋዬ ላይ ከርቤ፣ እሬትና* ቀረፋ አርከፍክፌአለሁ።+
18 ና፣ እስኪነጋ ድረስ በፍቅር እንርካ፤እርስ በርሳችን ፍቅራችንን በመግለጽ እንደሰት፤
19 ባሌ ቤት የለምና፤ወደ ሩቅ ቦታ ሄዷል።
20 በከረጢት ገንዘብ ይዟል፤ደግሞም ጨረቃዋ ሙሉ እስክትሆን ድረስ ወደ ቤት አይመለስም።”
21 እንደ ምንም ብላ አግባብታ ታሳስተዋለች።+
በለሰለሰ አንደበቷ ታታልለዋለች።
22 ለእርድ እንደሚነዳ በሬ፣ለቅጣትም በእግር ግንድ* እንደታሰረ ሞኝ ሰው በድንገት ይከተላታል፤+
23 ፍላጻ ጉበቱን እስኪሰነጥቀው ድረስ፣በወጥመድ ለመያዝ እንደምትቸኩል ወፍ ተከትሏት ይሄዳል፤ ሕይወቱን* ሊያሳጣው እንደሚችል አላወቀም።+
24 እንግዲህ ልጆቼ ሆይ፣ አዳምጡኝ፤የምናገረውንም ቃል በትኩረት ስሙ።
25 ልባችሁን ወደ መንገዷ አታዘንብሉ።
መንገድ ስታችሁ ወደ ጎዳናዋ አትግቡ፤+
26 ተሰይፈው እንዲወድቁ ያደረገቻቸው ብዙ ናቸውና፤+እሷ የገደለቻቸውም እጅግ ብዙ ናቸው።+
27 ቤቷ ወደ መቃብር* ይወስዳል፤ሙታን ወዳሉበት ስፍራም* ይወርዳል።
የግርጌ ማስታወሻ
^ ወይም “ሕጌን፤ ትምህርቴን።”
^ ወይም “የሚያማልል።”
^ ወይም “ተሞክሮ የሌላቸውን።”
^ ቃል በቃል “ልብ።”
^ ወይም “የዝሙት አዳሪ ልብስ።”
^ ቃል በቃል “እግሮቿ ቤት አይቀመጡም።”
^ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ሽቶ ለመሥራት የሚያገለግል ጥሩ መዓዛ ያለው ንጥረ ነገር የሚገኝበትን ዛፍ ያመለክታል።
^ ወይም “በእግር ብረት።”
^ ወይም “ነፍሱን።”
^ ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “ወደ ሞት ውስጠኛ ክፍሎችም።”