ሩት 4:1-22

  • ቦዔዝ ለመቤዠት ተስማማ (1-12)

  • ቦዔዝና ሩት ኢዮቤድን ወለዱ (13-17)

  • የዳዊት የዘር ሐረግ (18-22)

4  ከዚያም ቦዔዝ ወደ ከተማዋ በር+ ሄዶ በዚያ ተቀመጠ። በዚህ ጊዜ ቦዔዝ ቀደም ሲል ጠቅሶት የነበረው የሚቤዠው ሰው+ በዚያ ሲያልፍ ተመለከተ። ቦዔዝም “እገሌ፣ አንዴ ወደዚህ ና፤ እዚህ ተቀመጥ” አለው። ሰውየውም መጥቶ ተቀመጠ።  ከዚያም ቦዔዝ ከከተማዋ ሽማግሌዎች+ መካከል አሥር ሰዎች አምጥቶ “እዚህ ተቀመጡ” አላቸው። እነሱም ተቀመጡ።  ቦዔዝም የሚቤዠውን+ ሰው እንዲህ አለው፦ “ከሞዓብ ምድር+ የተመለሰችው ናኦሚ የወንድማችንን የኤሊሜሌክን+ የእርሻ ቦታ ልትሸጠው ነው።  ስለዚህ ጉዳዩን ለአንተ ላሳውቅህና እንዲህ ልልህ አሰብኩ፦ ‘እዚህ በተሰበሰቡት ነዋሪዎችና በአገሬ ሽማግሌዎች ፊት ግዛው።+ ልትቤዠው የምትፈልግ ከሆነ ተቤዠው። ልትቤዠው የማትፈልግ ከሆነ ግን ንገረኝና ልወቀው፤ ምክንያቱም በቅድሚያ የመቤዠት መብት ያለህ አንተ ነህ፤ እኔ ደግሞ ከአንተ ቀጥሎ ነኝ።’” ሰውየውም “ልቤዠው ፈቃደኛ ነኝ” አለ።+  ከዚያም ቦዔዝ “መሬቱን ከናኦሚ በምትገዛበት ቀን ውርሱ በሟቹ ስም እንዲጠራ ለማድረግ የሟቹ ሚስት ከሆነችው ከሞዓባዊቷ ሩት ላይም መግዛት እንዳለብህ እወቅ” አለው።+  የሚቤዠውም ሰው “የገዛ ርስቴን አደጋ ላይ ልጥል ስለምችል ልቤዠው አልችልም። እኔ ልቤዠው ስለማልችል በእኔ የመቤዠት መብት ተጠቅመህ አንተ ለራስህ ተቤዠው” አለው።  በጥንት ዘመን በእስራኤል ውስጥ በነበረው ልማድ መሠረት ከመቤዠት መብትም ሆነ ይህን መብት ለሌላ ሰው ከማስተላለፍ ጋር በተያያዘ ማንኛውም ዓይነት ስምምነት የሚጸድቀው አንድ ሰው ጫማውን አውልቆ+ ለሌላው ወገን ሲሰጥ ነበር፤ በእስራኤል ውስጥ አንድ ውል* የሚጸናው በዚህ መንገድ ሲከናወን ነበር።  በመሆኑም የሚቤዠው ሰው ቦዔዝን “አንተ ለራስህ ግዛው” በማለት ጫማውን አወለቀ።  ከዚያም ቦዔዝ ለሽማግሌዎቹና ለሕዝቡ ሁሉ እንዲህ አለ፦ “የኤሊሜሌክ የሆነውን ሁሉ እንዲሁም የኪሊዮንና የማህሎን የሆነውን ሁሉ ከናኦሚ ለመግዛቴ ዛሬ እናንተ ምሥክሮች ናችሁ።+ 10  በተጨማሪም የሟቹ ስም ከወንድሞቹ መካከል እንዲሁም ከሚኖርባት ከተማ በር እንዳይጠፋ የሟቹን ስም ዳግም በርስቱ ለማስጠራት+ የማህሎን ሚስት የሆነችውን ሞዓባዊቷን ሩትን ሚስት አድርጌ ወስጃታለሁ። ለዚህም እናንተ ዛሬ ምሥክሮች ናችሁ።”+ 11  በዚህ ጊዜ በከተማዋ በር ላይ የነበሩት ሰዎች ሁሉና ሽማግሌዎቹ እንዲህ አሉ፦ “እኛ ምሥክሮች ነን! ይሖዋ ወደ ቤትህ የምትገባውን ሚስት የእስራኤልን ቤት እንደገነቡት እንደ ራሔልና እንደ ሊያ ያድርጋት።+ አንተም በኤፍራታ+ የበለጸግክ ሁን፤ በቤተልሔምም+ መልካም ስም አትርፍ።* 12  እንዲሁም ይሖዋ ከዚህች ወጣት ሴት በሚሰጥህ ዘር አማካኝነት ቤትህ ትዕማር ለይሁዳ እንደወለደችለት እንደ ፋሬስ+ ቤት ይሁን።”+ 13  በመሆኑም ቦዔዝ ሩትን ወሰዳት፤ ሚስቱም ሆነች። ከእሷም ጋር ግንኙነት ፈጸመ፤ ይሖዋም እንድትፀንስ አደረጋት፤ ወንድ ልጅም ወለደች። 14  ሴቶቹም ናኦሚን እንዲህ አሏት፦ “ዛሬ የሚቤዥ ሰው ያላሳጣሽ ይሖዋ ይወደስ። ስሙም በእስራኤል ይታወጅ! 15  የምትወድሽና+ ከሰባት ወንዶች ልጆች የምትበልጥብሽ ምራትሽ የወለደችው ስለሆነ እሱ* ሕይወትሽን* የሚያድስ ይሆናል፤ በእርጅናሽም ዘመን ይጦርሻል።” 16  ናኦሚም ልጁን ወስዳ አቀፈችው፤ ትንከባከበውም ጀመር።* 17  ከዚያም ጎረቤቶቿ የሆኑ ሴቶች ስም አወጡለት። እንዲሁም “ለናኦሚ ወንድ ልጅ ተወለደላት” አሉ፤ ስሙንም ኢዮቤድ+ አሉት። እሱም የዳዊት አባት የሆነው የእሴይ+ አባት ነው። 18  እንግዲህ የፋሬስ+ የትውልድ ሐረግ ይህ ነው፦ ፋሬስ ኤስሮንን+ ወለደ፤ 19  ኤስሮንም ራምን ወለደ፤ ራምም አሚናዳብን ወለደ፤+ 20  አሚናዳብም+ ነአሶንን ወለደ፤ ነአሶንም ሰልሞንን ወለደ፤ 21  ሰልሞንም ቦዔዝን ወለደ፤ ቦዔዝም ኢዮቤድን ወለደ፤ 22  ኢዮቤድም እሴይን ወለደ፤+ እሴይም ዳዊትን+ ወለደ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የምሥክርነት ቃል።”
ቃል በቃል “ስምህ ይግነን።”
የናኦሚን የልጅ ልጅ ያመለክታል።
ወይም “ነፍስሽን።”
ወይም “ሞግዚትም ሆነችው።”