ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 10:1-11

  • ትንሽ ጥቅልል የያዘ ብርቱ መልአክ (1-7)

    • “ከእንግዲህ ወዲህ መዘግየት አይኖርም” (6)

    • ‘ቅዱሱ ሚስጥር ይፈጸማል’ (7)

  • ዮሐንስ ትንሿን ጥቅልል በላ (8-11)

10  እኔም ደመና የተጎናጸፈ* ሌላ ብርቱ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ በራሱም ላይ ቀስተ ደመና ነበር፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ፣+ ቅልጥሞቹም* እንደ እሳት ዓምዶች ነበሩ፤  በእጁም የተከፈተች ትንሽ ጥቅልል ይዞ ነበር። እሱም ቀኝ እግሩን በባሕር ላይ፣ ግራ እግሩን ደግሞ በምድር ላይ አሳረፈ፤  እንደሚያገሣ አንበሳም በታላቅ ድምፅ ጮኸ።+ በጮኸም ጊዜ የሰባቱ ነጎድጓዶች ድምፆች+ ተናገሩ።  ሰባቱ ነጎድጓዶች በተናገሩም ጊዜ ለመጻፍ ተዘጋጀሁ፤ ሆኖም ከሰማይ+ “ሰባቱ ነጎድጓዶች የተናገሯቸውን ነገሮች በማኅተም አሽጋቸው* እንጂ አትጻፋቸው” የሚል ድምፅ ሰማሁ።  በባሕሩና በምድሩ ላይ ቆሞ ያየሁት መልአክ ቀኝ እጁን ወደ ሰማይ አነሳ፤  ሰማይንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች፣ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ነገሮች እንዲሁም ባሕርንና በውስጡ ያሉትን ነገሮች በፈጠረውና+ ለዘላለም በሚኖረው+ በመማል እንዲህ አለ፦ “ከእንግዲህ ወዲህ መዘግየት አይኖርም።  ሆኖም ሰባተኛው መልአክ+ መለከቱን ሊነፋ+ በተዘጋጀባቸው ቀኖች አምላክ የገዛ ራሱ ባሪያዎች ለሆኑት ለነቢያት+ እንደ ምሥራች ያበሰረው ቅዱስ ሚስጥር+ በእርግጥ ይፈጸማል።”  ከሰማይ የመጣውም ድምፅ+ እንደገና ሲያናግረኝ ሰማሁ፤ እንዲህም አለኝ፦ “ሂድ፣ በባሕሩና በምድሩ ላይ በቆመው መልአክ እጅ ያለችውን የተከፈተች ጥቅልል ውሰድ።”+  እኔም ወደ መልአኩ ሄጄ ትንሿን ጥቅልል እንዲሰጠኝ ጠየቅኩት። እሱም “ውሰድና ብላት፤+ ሆድህን መራራ ታደርገዋለች፤ አፍህ ላይ ግን እንደ ማር ትጣፍጣለች” አለኝ። 10  ትንሿን ጥቅልል ከመልአኩ እጅ ወስጄ በላኋት፤+ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠች፤+ ከበላኋት በኋላ ግን ሆዴ መራራ ሆነ። 11  እነሱም “ሕዝቦችን፣ ብሔራትን፣ ቋንቋዎችንና ብዙ ነገሥታትን በተመለከተ እንደገና ትንቢት መናገር አለብህ” አሉኝ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በደመና የተሸፈነ።”
ቃል በቃል “እግሮቹም።”
ወይም “በሚስጥር ያዛቸው።”