ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 12:1-17

  • ሴቲቱ፣ ወንዱ ልጅና ዘንዶው (1-6)

  • ሚካኤል ከዘንዶው ጋር ተዋጋ (7-12)

    • ዘንዶው ወደ ምድር ተወረወረ (9)

    • ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ያውቃል (12)

  • ዘንዶው ሴቲቱን አሳደዳት (13-17)

12  ከዚያም በሰማይ ታላቅ ምልክት ታየ፦ አንዲት ሴት+ ፀሐይን ተጎናጽፋ* ነበር፤ ጨረቃም ከእግሯ ሥር ነበረች፤ በራሷም ላይ 12 ከዋክብት ያሉት አክሊል ነበር፤  እሷም ነፍሰ ጡር ነበረች። ልትወልድ ስትል ምጥ ይዟት በጭንቅ ትጮኽ ነበር።  ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ። እነሆ፣ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶች ያሉት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች የደፋ፣ ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ታላቅ ዘንዶ+ ታየ፤  ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት+ አንድ ሦስተኛ ጎትቶ ወደ ምድር ወረወረ።+ ዘንዶውም በምትወልድበት ጊዜ ልጇን ለመዋጥ ፈልጎ ልትወልድ በተቃረበችው ሴት+ ፊት ቆሞ ይጠብቅ ነበር።  እሷም ብሔራትን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛውን*+ ልጅ አዎ፣ ወንድ ልጅ ወለደች።+ ልጇም ወደ አምላክና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።  ሴቲቱም 1,260 ቀን በዚያ እንዲመግቧት አምላክ ወዳዘጋጀላት ስፍራ ወደ ምድረ በዳ ሸሸች።+  በሰማይም ጦርነት ተነሳ፦ ሚካኤልና*+ መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም ተዋጓቸው፤  ነገር ግን አልቻሏቸውም፤* ከዚያ በኋላም በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም።  ስለሆነም ታላቁ ዘንዶ+ ይኸውም መላውን ዓለም እያሳሳተ ያለው+ ዲያብሎስና+ ሰይጣን+ ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ+ ወደ ታች ተወረወረ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤+ መላእክቱም ከእሱ ጋር ተወረወሩ። 10  በሰማይ እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ፦ “አሁን የአምላካችን ማዳን፣+ ኃይልና መንግሥት+ እንዲሁም የእሱ መሲሕ ሥልጣን ሆኗል፤ ምክንያቱም ቀንና ሌሊት በአምላካችን ፊት የሚከሳቸው የወንድሞቻችን ከሳሽ ወደ ታች ተወርውሯል!+ 11  እነሱም ከበጉ ደም+ የተነሳና ከምሥክርነታቸው ቃል+ የተነሳ ድል ነሱት፤+ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ለነፍሳቸው* አልሳሱም።+ 12  ስለዚህ እናንተ ሰማያትና በውስጣቸው የምትኖሩ ሁሉ ደስ ይበላችሁ! ምድርና ባሕር+ ግን ወዮላችሁ! ምክንያቱም ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው+ ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።” 13  ዘንዶውም ወደ ምድር እንደተወረወረ+ ባየ ጊዜ ወንድ ልጅ በወለደችው ሴት ላይ ስደት አደረሰባት።+ 14  ሆኖም ሴቲቱ ከእባቡ+ ፊት ርቃ ለአንድ ዘመን፣ ለዘመናትና ለግማሽ ዘመን*+ ወደምትመገብበት በምድረ በዳ ወደተዘጋጀላት ስፍራ በርራ መሄድ እንድትችል የታላቅ ንስር ሁለት ክንፎች+ ተሰጧት። 15  እባቡም ሴቲቱ በወንዝ ውስጥ እንድትሰምጥ ከአፉ የወጣ እንደ ወንዝ ያለ ውኃ ከኋላዋ ለቀቀባት። 16  ይሁን እንጂ ምድሪቱ ለሴቲቱ ደረሰችላት፤ ምድሪቱም አፏን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ የለቀቀውን ወንዝ ዋጠች። 17  ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ እጅግ ተቆጥቶ የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁትንና ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ+ የተሰጣቸውን ከዘሯ+ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ለብሳ።”
ቃል በቃል “እንደ እረኛ በብረት በትር የሚያግደውን።”
“እንደ አምላክ ያለ ማን ነው?” የሚል ትርጉም አለው።
“ሆኖም እሱ [ማለትም ዘንዶው] ድል ተመታ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ለሕይወታቸው።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ሦስት ተኩል ዘመናትን ያመለክታል።