ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 15:1-8

  • “ሰባት መቅሰፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት” (1-8)

    • ‘የሙሴና የበጉ መዝሙር’ (3, 4)

15  እኔም ሌላ ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ አየሁ፤ ሰባት መቅሰፍቶች የያዙ ሰባት መላእክት+ ነበሩ። የአምላክ ቁጣ የሚደመደመው በእነዚህ ስለሆነ እነዚህ መቅሰፍቶች የመጨረሻዎቹ ናቸው።+  እኔም ከእሳት ጋር የተቀላቀለ የብርጭቆ ባሕር+ የሚመስል ነገር አየሁ፤ እንዲሁም አውሬውን፣ ምስሉንና+ የስሙን ቁጥር+ ድል የነሱት+ የአምላክን በገናዎች ይዘው በብርጭቆው ባሕር አጠገብ ቆመው ነበር።  የአምላክን ባሪያ የሙሴን መዝሙርና+ የበጉን+ መዝሙር እንዲህ እያሉ ይዘምሩ ነበር፦ “ሁሉን ቻይ የሆንከው ይሖዋ* አምላክ ሆይ፣+ ሥራዎችህ ታላቅና አስደናቂ ናቸው።+ የዘላለም ንጉሥ ሆይ፣+ መንገድህ ጽድቅና እውነት ነው።+  ይሖዋ* ሆይ፣ ለመሆኑ አንተን የማይፈራና ስምህን ከፍ ከፍ የማያደርግ ማን ነው? አንተ ብቻ ታማኝ ነህና!+ የጽድቅ ድንጋጌዎችህ ስለተገለጡ ሕዝቦች ሁሉ መጥተው በፊትህ ይሰግዳሉ።”+  ከዚህ በኋላ አየሁ፤ የምሥክሩ ድንኳን+ ቅዱስ ስፍራ* በሰማይ ተከፍቶ ነበር፤+  ሰባቱን መቅሰፍቶች የያዙት ሰባቱ መላእክትም+ ንጹሕና የሚያንጸባርቅ በፍታ ለብሰው እንዲሁም ደረታቸውን በወርቅ መታጠቂያ ታጥቀው ከቅዱሱ ስፍራ ወጡ።  ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት አንዱ ለዘላለም በሚኖረው አምላክ ቁጣ+ የተሞሉ ሰባት የወርቅ ሳህኖችን ለሰባቱ መላእክት ሰጣቸው።  ቅዱሱ ስፍራም ከአምላክ ክብርና+ ከኃይሉ የተነሳ በጭስ ተሞላ፤ የሰባቱ መላእክት ሰባት መቅሰፍቶች+ እስኪፈጸሙ ድረስም ወደ ቅዱሱ ስፍራ ማንም መግባት አልቻለም።

የግርጌ ማስታወሻ

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
የቤተ መቅደሱን ቅድስተ ቅዱሳን ያመለክታል።