ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 19:1-21
19 ከዚህ በኋላ በሰማይ እንደ ብዙ ሠራዊት ድምፅ ያለ ታላቅ ድምፅ ሰማሁ። እንዲህም አሉ፦ “ያህን አወድሱ!*+ ማዳን፣ ክብርና ኃይል የአምላካችን ነው፤
2 ምክንያቱም ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸው።+ ምድርን በዝሙቷ* ባረከሰችው በታላቂቱ አመንዝራ ላይ የፍርድ እርምጃ ወስዷልና፤ እንዲሁም ስለ ባሪያዎቹ ደም ተበቅሏታል።”*+
3 ወዲያውኑም ለሁለተኛ ጊዜ “ያህን አወድሱ!*+ ከእሷ የሚወጣው ጭስም ለዘላለም ወደ ላይ ይወጣል” አሉ።+
4 ደግሞም 24ቱ ሽማግሌዎችና+ አራቱ ሕያዋን ፍጥረታት+ ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አምላክ ሰገዱ፤ እንዲሁም “አሜን! ያህን አወድሱ!”* አሉ።+
5 በተጨማሪም ከዙፋኑ የወጣ አንድ ድምፅ “እሱን የምትፈሩ ባሪያዎቹ ሁሉ፣+ ታናናሾችና ታላላቆች፣+ አምላካችንን አወድሱ” አለ።
6 እንደ ብዙ ሠራዊት ድምፅ፣ እንደ ብዙ ውኃዎች ድምፅና እንደ ኃይለኛ ነጎድጓድ ድምፅ ያለ ነገር ሰማሁ። እንዲህም አሉ፦ “ያህን አወድሱ፤*+ ምክንያቱም ሁሉን ቻይ የሆነው አምላካችን ይሖዋ*+ ነግሦአል!+
7 የበጉ ሠርግ ስለደረሰና ሙሽራዋ ራሷን ስላዘጋጀች እንደሰት፤ ሐሴትም እናድርግ፤ ለእሱም ክብር እንስጠው።
8 አዎ፣ የሚያንጸባርቅና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ እንድትለብስ ተሰጥቷታል፤ ይህ ጥሩ በፍታ የቅዱሳንን የጽድቅ ተግባር ያመለክታልና።”+
9 እሱም “ይህን ጻፍ፦ ወደ በጉ ሠርግ+ የራት ግብዣ የተጠሩ ደስተኞች ናቸው” አለኝ። ደግሞም “እነዚህ እውነተኛ የአምላክ ቃሎች ናቸው” አለኝ።
10 እኔም በዚህ ጊዜ ልሰግድለት በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እሱ ግን “ተጠንቀቅ! ፈጽሞ እንዳታደርገው!+ እኔ ከአንተም ሆነ ስለ ኢየሱስ የመመሥከር ሥራ ካላቸው ወንድሞችህ ጋር አብሬ የማገለግል ባሪያ ነኝ።+ ለአምላክ ስገድ!+ ትንቢት የሚነገረው ስለ ኢየሱስ ለመመሥከር ነውና” አለኝ።+
11 እኔም ሰማይ ተከፍቶ አየሁ፤ እነሆም፣ ነጭ ፈረስ ነበር።+ በእሱም ላይ የተቀመጠው “ታማኝና+ እውነተኛ”+ ተብሎ ይጠራል፤ እሱም በጽድቅ ይፈርዳል እንዲሁም ይዋጋል።+
12 ዓይኖቹ የእሳት ነበልባል ናቸው፤+ በራሱም ላይ ብዙ ዘውዶች አሉ። ከራሱ በቀር ማንም የማያውቀው ስም ተጽፎበታል፤
13 ደም የነካው* መደረቢያም ለብሷል፤ ደግሞም “የአምላክ ቃል”+ በሚል ስም ይጠራል።
14 በተጨማሪም በሰማይ ያሉት ሠራዊቶች በነጭ ፈረሶች ተቀምጠው ይከተሉት ነበር፤ እነሱም ነጭና ንጹሕ የሆነ ጥሩ በፍታ ለብሰው ነበር።
15 እሱም ብሔራትን ይመታበት ዘንድ ከአፉ ረጅም ስለታም ሰይፍ+ ይወጣል፤ እንደ እረኛም በብረት በትር ይገዛቸዋል።*+ በተጨማሪም ሁሉን ቻይ የሆነውን የአምላክን የመዓቱን የቁጣ ወይን ጠጅ መጭመቂያ ይረግጣል።+
16 በመደረቢያው አዎ፣ በጭኑ ላይ “የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ”+ የሚል ስም ተጽፏል።
17 በተጨማሪም አንድ መልአክ በፀሐይ መካከል ቆሞ አየሁ፤ እሱም በታላቅ ድምፅ ጮኾ በሰማይ መካከል* ለሚበርሩት ወፎች ሁሉ እንዲህ አለ፦ “ወደዚህ ኑ፤ ወደ ታላቁ የአምላክ ራት ተሰብሰቡ፤+
18 የነገሥታትን ሥጋ፣ የጦር አዛዦችን ሥጋ፣ የብርቱ ሰዎችን ሥጋ፣+ የፈረሶችንና የፈረሰኞችን ሥጋ+ እንዲሁም የሁሉንም ሥጋ ይኸውም የነፃ ሰዎችንና የባሪያዎችን፣ የታናናሾችንና የታላላቆችን ሥጋ ብሉ።”
19 ከዚህ በኋላ አውሬው፣ የምድር ነገሥታትና ሠራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ።+
20 አውሬውም ተያዘ፤ በፊቱ ተአምራዊ ምልክቶች የፈጸመው ሐሰተኛው ነቢይም+ ከእሱ ጋር ተያዘ፤ ይህ ነቢይ በእነዚህ ምልክቶች አማካኝነት፣ የአውሬውን ምስል የተቀበሉትንና+ ለምስሉ የሰገዱትን+ አስቷል። ሁለቱም በሕይወት እንዳሉ በድኝ ወደሚነደው የእሳት ሐይቅ ተወረወሩ።+
21 የቀሩት ግን በፈረሱ ላይ ከተቀመጠው አፍ በወጣው ረጅም ሰይፍ ተገደሉ።+ ወፎችም ሁሉ ሥጋቸውን በልተው ጠገቡ።+