ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 6:1-17

  • በጉ የመጀመሪያዎቹን ስድስት ማኅተሞች ከፈተ (1-17)

    • በነጭ ፈረስ ላይ የተቀመጠ ድል አድራጊ (1, 2)

    • ከምድር ላይ ሰላምን የሚወስድ ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ፈረስ ጋላቢ (3, 4)

    • ረሃብ የሚያመጣው የጥቁሩ ፈረስ ጋላቢ (5, 6)

    • ሞት የተባለው የግራጫው ፈረስ ጋላቢ (7, 8)

    • የታረዱ ሰዎች ነፍሳት ከመሠዊያው በታች ታዩ (9-11)

    • ታላቅ የምድር ነውጥ (12-17)

6  እኔም በጉ+ ከሰባቱ ማኅተሞች አንዱን ሲከፍት አየሁ፤+ ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታትም+ አንዱ እንደ ነጎድጓድ ባለ ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ።  እኔም አየሁ፣ እነሆ ነጭ ፈረስ ነበር፤+ በእሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤+ እሱም ድል እያደረገ ወጣ፤ ድሉንም ለማጠናቀቅ ወደ ፊት ገሰገሰ።+  ሁለተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ።  ደማቅ ቀይ ቀለም ያለው ሌላ ፈረስ ወጣ፤ በእሱም ላይ ለተቀመጠው ሰዎች እርስ በርሳቸው ይተራረዱ ዘንድ ሰላምን ከምድር እንዲወስድ ተፈቀደለት፤ እንዲሁም ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው።+  ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ+ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም አየሁ፣ እነሆ ጥቁር ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር።  ከአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት መካከል እንደ ድምፅ ያለ ነገር “አንድ እርቦ* ስንዴ በዲናር፣*+ ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፤ ደግሞም የወይራ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ።+  አራተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ አራተኛው ሕያው ፍጡር+ “ና!” ሲል ሰማሁ።  እኔም አየሁ፣ እነሆ ግራጫ ፈረስ ነበር፤ በእሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበር። መቃብርም* በቅርብ ይከተለው ነበር። ሞትና መቃብርም በረጅም ሰይፍ፣ በምግብ እጥረት፣+ በገዳይ መቅሰፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።+  አምስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ በአምላክ ቃል የተነሳና በሰጡት ምሥክርነት የተነሳ የታረዱትን ሰዎች ነፍሳት*+ ከመሠዊያው በታች+ አየሁ።+ 10  እነሱም “ቅዱስና እውነተኛ የሆንከው ሉዓላዊ ጌታ ሆይ፣+ በምድር በሚኖሩት ላይ የማትፈርደውና ደማችንን የማትበቀለው እስከ መቼ ነው?”+ ብለው በታላቅ ድምፅ ጮኹ። 11  ለእያንዳንዳቸውም ነጭ ልብስ ተሰጣቸው፤+ እንዲሁም ወደፊት እንደ እነሱ የሚገደሉት ባልንጀሮቻቸው የሆኑ ባሪያዎችና የወንድሞቻቸው ቁጥር እስኪሞላ ድረስ ለጥቂት ጊዜ እንዲጠብቁ ተነገራቸው።+ 12  ስድስተኛውንም ማኅተም ሲከፍት አየሁ፤ ታላቅ የምድር ነውጥም ተከሰተ፤ ፀሐይም ከፀጉር* እንደተሠራ ማቅ ጠቆረች፤ ጨረቃም ሙሉ በሙሉ ደም መሰለች፤+ 13  ኃይለኛ ነፋስ የበለስን ዛፍ ሲያወዛውዝ ያልበሰሉት ፍሬዎች ከዛፉ ላይ እንደሚረግፉ፣ የሰማይ ከዋክብትም ወደ ምድር ወደቁ። 14  ሰማይም እየተጠቀለለ እንዳለ የመጽሐፍ ጥቅልል ከቦታው ተነሳ፤+ እንዲሁም ተራሮች ሁሉና ደሴቶች ሁሉ ከቦታቸው ተወገዱ።+ 15  ከዚያም የምድር ነገሥታት፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የጦር አዛዦች፣ ሀብታሞች፣ ብርቱዎች፣ ባሪያዎች ሁሉና ነፃ ሰዎች ሁሉ በዋሻዎች ውስጥና ተራራ ላይ ባሉ ዓለቶች መካከል ተደበቁ።+ 16  ተራሮቹንና ዓለቶቹንም እንዲህ እያሉ ተማጸኑ፦ “በላያችን ውደቁና+ በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ፊትና ከበጉ+ ቁጣ ሰውሩን፤ 17  ምክንያቱም ቁጣቸውን የሚገልጹበት ታላቁ ቀን መጥቷል፤+ ማንስ ሊቆም ይችላል?”+

የግርጌ ማስታወሻ

አንድ እርቦ ስንዴ 0.7 ኪሎ ግራም ገደማ ይመዝናል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የሮም የብር ሳንቲም ሲሆን አንድ ሠራተኛ ከሚከፈለው የቀን ደሞዝ ጋር እኩል ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
ወይም “ሐዲስም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
መሠዊያው ላይ የፈሰሰውን ለሕይወታቸው ወሳኝ የሆነውን ደማቸውን እንደሚያመለክት ግልጽ ነው። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
የፍየል ፀጉር ሳይሆን አይቀርም።