ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 7:1-17

  • አጥፊ ነፋሳትን የያዙ አራት መላእክት (1-3)

  • የ144,000ዎቹ መታተም (4-8)

  • ነጭ ልብስ የለበሰ እጅግ ብዙ ሕዝብ (9-17)

7  ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማዕዘናት ቆመው አየሁ፤ እነሱም በምድር ወይም በባሕር ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ ምንም ነፋስ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት አጥብቀው ይዘው ነበር።  እንዲሁም የሕያው አምላክ ማኅተም ያለው ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ* ወደ ላይ ሲወጣ አየሁ፤ እሱም ምድርንና ባሕርን እንዲጎዱ ሥልጣን የተሰጣቸውን አራቱን መላእክት በታላቅ ድምፅ  እንዲህ አላቸው፦ “የአምላካችንን ባሪያዎች ግንባራቸው ላይ ማኅተም እስክናደርግባቸው ድረስ+ ምድርን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ።”+  የታተሙትን ሰዎች ቁጥር ሰማሁ፤ ቁጥራቸው 144,000+ ሲሆን የታተሙትም ከእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ነገድ ነበር፦+  ከይሁዳ ነገድ 12,000 ታተሙ፤ከሮቤል ነገድ 12,000፣ከጋድ ነገድ 12,000፣  ከአሴር ነገድ 12,000፣ከንፍታሌም ነገድ 12,000፣ከምናሴ+ ነገድ 12,000፣  ከስምዖን ነገድ 12,000፣ከሌዊ ነገድ 12,000፣ከይሳኮር ነገድ 12,000፣  ከዛብሎን ነገድ 12,000፣ከዮሴፍ ነገድ 12,000፣ከቢንያም ነገድ 12,000 ታተሙ።  ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም፣ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ+ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ ነጭ ልብስ ለብሰው+ በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር፤ የዘንባባ ዝንጣፊዎችንም በእጆቻቸው ይዘው ነበር።+ 10  በታላቅም ድምፅ እየጮኹ “መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ+ ነው” ይሉ ነበር። 11  መላእክቱ ሁሉ በዙፋኑ፣ በሽማግሌዎቹና+ በአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት ዙሪያ ቆመው ነበር፤ እነሱም በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለአምላክ ሰገዱ፤ 12  እንዲህም አሉ፦ “አሜን! ውዳሴ፣ ግርማ፣ ጥበብ፣ ምስጋና፣ ክብር፣ ኃይልና ብርታት ለዘላለም ለአምላካችን ይሁን።+ አሜን።” 13  ከሽማግሌዎቹ አንዱ መልሶ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት+ እነማን ናቸው? ከወዴትስ የመጡ ናቸው?” አለኝ። 14  እኔም ወዲያውኑ “ጌታዬ፣ የምታውቀው አንተ ነህ” አልኩት። እሱም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ታላቁን መከራ+ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።+ 15  በአምላክ ዙፋን ፊት ያሉትም ለዚህ ነው፤ በቤተ መቅደሱም ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡለት ነው፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም+ ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል።+ 16  ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም እንዲሁም አይጠሙም፤ ፀሐይ አይመታቸውም፤ ሐሩሩም አያቃጥላቸውም፤+ 17  ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ+ እረኛቸው ይሆናል፤+ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋል።+ አምላክም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።”*+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ከምሥራቅ።”
ወይም “ይጠርጋል።”