ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 11:1-36

  • አምላክ እስራኤልን ሙሉ በሙሉ አልተወውም (1-16)

  • የወይራ ዛፉ ምሳሌ (17-32)

  • ጥልቅ የሆነው የአምላክ ጥበብ (33-36)

11  እንግዲያው ‘አምላክ ሕዝቡን ትቷል ማለት ነው?’ ብዬ እጠይቃለሁ፤+ በፍጹም! ምክንያቱም እኔም ራሴ እስራኤላዊ ነኝ፤ ከአብርሃም ዘር፣ ከቢንያም ነገድ ነኝ።  አምላክ መጀመሪያ እውቅና የሰጣቸውን ሰዎች አልተዋቸውም።+ ቅዱስ መጽሐፉ ኤልያስ እስራኤልን በአምላክ ፊት በከሰሰበት ጊዜ የሆነውን ነገር በተመለከተ ምን እንደሚል አታውቁም?  “ይሖዋ* ሆይ፣ ነቢያትህን ገድለዋል፤ መሠዊያዎችህንም አፍርሰዋል፤ እኔ ብቻ ቀረሁ፤ አሁንም ሕይወቴን* ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ ነው።”+  ይሁንና አምላክ የሰጠው መልስ ምን ነበር? “ለባአል ያልተንበረከኩ 7,000 ሰዎች አሉኝ።”+  ስለዚህ በዚህ መንገድ በጸጋ የተመረጡ ቀሪዎች+ በአሁኑ ዘመንም አሉ።  የተመረጡት በጸጋ+ ከሆነ በሥራ መሆኑ ቀርቷል፤+ አለዚያ ጸጋው ጸጋ መሆኑ በቀረ ነበር።  እንግዲህ ምን ማለት እንችላለን? እስራኤል አጥብቆ ይፈልገው የነበረውን ነገር አላገኘም፤ የተመረጡት ግን አገኙት።+ የቀሩት የማስተዋል ስሜታቸው ደነዘዘ፤+  ይህም “አምላክ እስከ ዛሬ ኃይለኛ የእንቅልፍ መንፈስ ጣለባቸው፤+ የማያይ ዓይንና የማይሰማ ጆሮ ሰጣቸው” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+  በተጨማሪም ዳዊት እንዲህ ብሏል፦ “ማዕዳቸው ወጥመድና አሽክላ እንዲሁም እንቅፋትና ቅጣት ይሁንባቸው። 10  ዓይኖቻቸው ማየት እንዳይችሉ ይጨልሙ፤ ጀርባቸውም ጎብጦ እንዲቀር አድርግ።”+ 11  በመሆኑም ‘የተሰናከሉት ወድቀው እንዲቀሩ ነው?’ ብዬ እጠይቃለሁ፤ በፍጹም! ከዚህ ይልቅ እነሱ ሕጉን በመተላለፋቸው ለአሕዛብ የመዳን መንገድ ተከፈተ፤ ይህም የሆነው እነሱን ለማስቀናት ነው።+ 12  እነሱ ሕጉን መተላለፋቸው ለዓለም በረከት ከሆነና የእነሱ ማነስ ለአሕዛብ በረከት ካስገኘ+ ቁጥራቸው መሙላቱማ ምን ያህል ታላቅ በረከት ያስገኝ ይሆን! 13  አሁን ደግሞ የምናገረው ከአሕዛብ ወገን ለሆናችሁት ነው። ለአሕዛብ የተላክሁ ሐዋርያ+ እንደመሆኔ መጠን አገልግሎቴን አከብራለሁ፤*+ 14  ይህን የማደርገው የገዛ ወገኖቼ* የሆኑትን በማስቀናት ከእነሱ መካከል አንዳንዶቹን ማዳን እችል እንደሆነ ብዬ ነው። 15  የእነሱ መጣል+ ለዓለም እርቅ ካስገኘ፣ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት ወደ ሕይወት መሻገር ማለት አይሆንም? 16  በተጨማሪም በኩራት ተደርጎ የተወሰደው የሊጡ ክፍል ቅዱስ ከሆነ ሊጡ በሙሉ ቅዱስ ነው፤ እንዲሁም ሥሩ ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው። 17  ይሁን እንጂ ከቅርንጫፎቹ መካከል አንዳንዶቹ ቢሰበሩና አንተ የዱር ወይራ ሆነህ ሳለህ በእነሱ መካከል ከተጣበቅክ እንዲሁም ከወይራው ዛፍ ሥር ከሚገኘው በረከት ተካፋይ ከሆንክ 18  በተሰበሩት ቅርንጫፎች ላይ አትታበይ።* በእነሱ ላይ የምትታበይ+ ከሆነ ግን አንተን የተሸከመህ ሥሩ ነው እንጂ አንተ ሥሩን እንዳልተሸከምከው አስታውስ። 19  ይሁንና “ቅርንጫፎቹ የተሰበሩት እኔ በቦታቸው እንድጣበቅ ነው”+ ብለህ ታስብ ይሆናል። 20  እውነት ነው! እነሱ ባለማመናቸው ተሰብረዋል፤+ አንተ ግን በእምነት ቆመሃል።+ ቢሆንም መፍራት እንጂ መታበይ አይገባህም። 21  አምላክ በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራ ለአንተም አይራራምና። 22  ስለዚህ አምላክ ደግም+ ጥብቅም እንደሆነ ተመልከት። በወደቁት ላይ ጥብቅ ይሆናል፤+ አንተ ግን የአምላክ ደግነት የሚገባህ ሆነህ እስከተገኘህ ድረስ ደግነቱን ያሳይሃል፤ አለዚያ ግን አንተም ተቆርጠህ ትጣላለህ። 23  እነሱም እምነት የለሽ ሆነው ካልቀጠሉ ይጣበቃሉ፤ አምላክ መልሶ ሊያጣብቃቸው+ ይችላልና። 24  አንተ በተፈጥሮ የዱር ከሆነው የወይራ ዛፍ ተቆርጠህ፣ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ መጣበቅ ከቻልክ እነዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑት ቅርንጫፎችማ በራሳቸው የወይራ ዛፍ ላይ ተመልሰው መጣበቅ እንደሚችሉ የታወቀ ነው! 25  ወንድሞች፣ በራሳችሁ ዓይን ጥበበኞች የሆናችሁ እንዳይመስላችሁ ይህን ቅዱስ ሚስጥር እንድታውቁ እፈልጋለሁ፦+ የአሕዛብ ቁጥር እስኪሞላ ድረስ የእስራኤል ሕዝብ በከፊል ስሜቱ ደንዝዟል፤ 26  በዚህም መንገድ እስራኤል ሁሉ+ ይድናል። ይህም እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ነው፦ “አዳኝ* ከጽዮን ይወጣል፤+ የያዕቆብም ዘሮች የክፋት ድርጊታቸውን እንዲተዉ ያደርጋል። 27  ኃጢአታቸውንም በማስወግድበት ጊዜ+ ከእነሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው።”+ 28  እርግጥ ከምሥራቹ ጋር በተያያዘ ለእናንተ ጥቅም ሲባል የአምላክ ጠላቶች ናቸው፤ በአምላክ ምርጫ መሠረት ግን ለአባቶቻቸው በተገባው የተስፋ ቃል የተነሳ በአምላክ ዘንድ የተወደዱ ናቸው።+ 29  አምላክ በስጦታውና በጠራቸው ሰዎች አይጸጸትምና። 30  በአንድ ወቅት እናንተ አምላክን የማትታዘዙ ነበራችሁ፤+ አሁን ግን በእነሱ አለመታዘዝ+ ምክንያት ምሕረት አግኝታችኋል።+ 31  ስለዚህ አይሁዳውያን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው አምላክ ለእናንተ ምሕረት አሳይቷችኋል፤ ከዚህም የተነሳ ለእነሱም ምሕረት ሊያሳያቸው ይችላል። 32  አምላክ ለሁሉም ምሕረት ያሳይ ዘንድ+ ሁሉም ያለመታዘዝ እስረኞች+ እንዲሆኑ ፈቅዷልና። 33  የአምላክ ብልጽግና፣ ጥበብና እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው! 34  እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ “የይሖዋን* ሐሳብ ማወቅ የቻለ ማን ነው? አማካሪውስ የሆነ ማን ነው?”+ 35  ወይስ “መልሶ ይከፍለው ዘንድ ለእሱ ያበደረ ማን ነው?”+ 36  ምክንያቱም ሁሉም ነገር የተገኘው ከእሱ፣ በእሱና ለእሱ ነው። ለእሱ ለዘላለም ክብር ይሁን። አሜን።

የግርጌ ማስታወሻ

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።
ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ከፍ ከፍ አደርጋለሁ።”
ቃል በቃል “ሥጋዬ።”
ወይም “ጉራ አትንዛ።”
ወይም “ነፃ አውጪ።”
ከተጨማሪው መረጃ ላይ ሀ5ን ተመልከት።