ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 3:1-31

  • “የአምላክ እውነተኝነት የተረጋገጠ ነው” (1-8)

  • ‘አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን የኃጢአት ተገዢዎች ናቸው’ (9-20)

  • በእምነት መጽደቅ (21-31)

    • ‘ሁሉም የአምላክን ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል’ (23)

3  ታዲያ አይሁዳዊ መሆን ጥቅሙ ምኑ ላይ ነው? ግርዘትስ ፋይዳው ምንድን ነው?  በሁሉም መንገድ ትልቅ ጥቅም አለው። በመጀመሪያ ደረጃ የአምላክ ቅዱስ ቃል+ በአደራ ተሰጥቷቸዋል።  አንዳንድ አይሁዳውያን እምነት ቢጎድላቸውስ? የእነሱ እምነት ማጣት ሰዎች በአምላክ እንዳይታመኑ ሊያደርግ ይችላል?  በፍጹም! ከዚህ ይልቅ “በቃልህ ጻድቅ ሆነህ ትገኝ ዘንድ፣ በፍርድም ፊት ትረታ ዘንድ”+ ተብሎ እንደተጻፈ ሰው ሁሉ ሐሰተኛ ሆኖ ቢገኝ+ እንኳ የአምላክ እውነተኝነት የተረጋገጠ ነው።+  ይሁን እንጂ የእኛ ክፋት የአምላክን ጽድቅ አጉልቶ የሚያሳይ ከሆነ ምን ማለት እንችላለን? አምላክ ቁጣውን መግለጹ ኢፍትሐዊ ያሰኘዋል እንዴ? (አንዳንድ ሰዎች እንደሚያስቡት ማለት ነው።)  በፍጹም! አለዚያ አምላክ በዓለም ላይ እንዴት ይፈርዳል?+  ይሁንና በእኔ ውሸት የተነሳ የአምላክ እውነት ለእሱ ክብር በሚያመጣ መንገድ ይበልጥ ጎልቶ የሚወጣ ከሆነ ታዲያ እኔ ለምን ኃጢአተኛ ተብዬ ይፈረድብኛል?  እንዲህ ከሆነማ አንዳንድ ሰዎች “ጥሩ ነገር እንዲገኝ መጥፎ ነገር እንሥራ” ይላሉ በማለት በሐሰት እንደሚያስወሩብን ለምን አንልም? በእነዚህ ሰዎች ላይ የሚበየነው ፍርድ ፍትሐዊ ነው።+  እንግዲህ ምን ማለት ይቻላል? እኛ የተሻልን ነን ማለት ነው? በፍጹም! ምክንያቱም አይሁዳውያንም ሆኑ ግሪካውያን ሁሉም የኃጢአት ተገዢዎች+ እንደሆኑ በመናገር አስቀድመን ከሰናቸዋል፤ 10  ይህም እንዲህ ተብሎ እንደተጻፈው ነው፦ “ጻድቅ ሰው የለም፤ አንድም እንኳ የለም፤+ 11  ማስተዋል ያለው አንድም ሰው የለም፤ ደግሞም አምላክን የሚፈልግ አንድም ሰው የለም። 12  ሁሉም መንገድ ስተዋል፤ ሁሉም የማይረቡ ሆነዋል፤ ደግነት የሚያሳይ አንድም ሰው የለም፤ አንድም እንኳ አይገኝም።”+ 13  “ጉሮሯቸው የተከፈተ መቃብር ነው፤ በምላሳቸው ያታልላሉ።”+ “ከከንፈራቸው ሥር የእባብ መርዝ አለ።”+ 14  “አፋቸውም በእርግማንና በምሬት የተሞላ ነው።”+ 15  “እግሮቻቸው ደም ለማፍሰስ ፈጣኖች ናቸው።”+ 16  “በመንገዳቸው ላይ ጥፋትና መከራ አለ፤ 17  የሰላምንም መንገድ አያውቁም።”+ 18  “በዓይኖቻቸው ፊት አምላክን መፍራት የሚባል ነገር የለም።”+ 19  እንግዲህ አፍ ሁሉ እንዲዘጋና ዓለም በሙሉ በአምላክ ፊት ተጠያቂ እንዲሆን+ ሕግ የሚናገረው ሁሉ ከሕግ በታች ላሉት እንደሆነ እናውቃለን። 20  ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም ሰው* በፊቱ ጻድቅ ነህ ሊባል አይችልም፤+ ምክንያቱም ስለ ኃጢአት ትክክለኛ ግንዛቤ* የሚገኘው በሕጉ አማካኝነት ነው።+ 21  አሁን ግን ሕግ ሳያስፈልግ፣ በሕጉና በነቢያት የተመሠከረለት+ የአምላክ ጽድቅ ግልጽ ሆኗል፤+ 22  እምነት ያላቸው ሁሉ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት አማካኝነት የአምላክን ጽድቅ ያገኛሉ። ይህም የሆነው በሰዎች መካከል ምንም ልዩነት ስለሌለ ነው።+ 23  ምክንያቱም ሁሉም ኃጢአት ሠርተዋል፤ የአምላክንም ክብር ማንጸባረቅ ተስኗቸዋል፤+ 24  ይሁንና ክርስቶስ ኢየሱስ የከፈለው ቤዛ+ በሚያስገኘው ነፃነት አማካኝነት በጸጋው+ ጻድቃን ናችሁ መባላቸው እንዲሁ የተገኘ ነፃ ስጦታ ነው።+ 25  በኢየሱስ ደም የሚያምኑ+ ሁሉ ማስተሰረያ ያገኙ*+ ዘንድ አምላክ እሱን መባ አድርጎ አቅርቦታል። አምላክ ይህን ያደረገው የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው፤ ምክንያቱም አምላክ ቻይ በመሆን በቀደሙት ዘመናት የተፈጸሙትን ኃጢአቶች ይቅር ብሏል። 26  ይህን ያደረገው በዚህም ዘመን የራሱን ጽድቅ ለማሳየት ነው፤+ ይህም በኢየሱስ የሚያምነውን ሰው ጻድቅ ነህ በማለት እሱ ራሱ ጻድቅ ይሆን ዘንድ ነው።+ 27  ታዲያ እንድንኮራ የሚያደርገን ነገር ይኖራል? ምንም ነገር የለም። እንዳንኮራ የሚያደርገን ሕግ የትኛው ነው? የሥራ ሕግ ነው?+ በፍጹም አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ እንዳንኮራ የሚያደርገን የእምነት ሕግ ነው። 28  ምክንያቱም አንድ ሰው ጻድቅ ነህ የሚባለው የሕግን ሥራ በመፈጸም ሳይሆን በእምነት እንደሆነ እንረዳለን።+ 29  ወይስ አምላክ የአይሁዳውያን አምላክ ብቻ ነው?+ የአሕዛብስ አምላክ አይደለም?+ አዎ፣ የአሕዛብም አምላክ ነው።+ 30  አምላክ አንድ ስለሆነ+ የተገረዙትን ከእምነት የተነሳ ጻድቃን ይላቸዋል፤+ ያልተገረዙትንም በእምነታቸው አማካኝነት ጻድቃን ናችሁ ይላቸዋል።+ 31  ታዲያ በእምነታችን አማካኝነት ሕግን እንሽራለን ማለት ነው? በፍጹም! እንዲያውም ሕግን እንደግፋለን።+

የግርጌ ማስታወሻ

ቃል በቃል “ሥጋ ሁሉ።”
ወይም “እውቀት።”
ወይም “እርቅ ይፈጥሩ።”