ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 6:1-23
6 እንግዲህ ምን እንበል? ጸጋ እንዲበዛ ኃጢአት መሥራታችንን እንቀጥል?
2 በፍጹም! እኛ ለኃጢአት የሞትን+ ሆነን ሳለን ከእንግዲህ እንዴት በኃጢአት ውስጥ መኖራችንን እንቀጥላለን?+
3 ወይስ ክርስቶስ ኢየሱስ ውስጥ የተጠመቅን+ ሁላችን እሱ ሞት ውስጥ እንደተጠመቅን+ አታውቁም?
4 ስለዚህ ክርስቶስ በአብ ክብር ከሞት እንደተነሳ ሁሉ እኛም አዲስ ሕይወት እንድንኖር+ እሱ ሞት ውስጥ በመጠመቅ ከእሱ ጋር ተቀብረናል።+
5 ሞቱን በሚመስል ሞት ከእሱ ጋር አንድ ከሆንን+ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ+ ደግሞ ከእሱ ጋር አንድ እንደምንሆን ጥርጥር የለውም።
6 ምክንያቱም ኃጢአተኛው ሰውነታችን በእኛ ላይ ምንም ኃይል እንዳይኖረውና+ ከእንግዲህ የኃጢአት ባሪያዎች ሆነን እንዳንኖር+ አሮጌው ስብዕናችን ከእሱ ጋር በእንጨት ላይ እንደተቸነከረ እናውቃለን።+
7 የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷልና።*
8 በተጨማሪም ከክርስቶስ ጋር ከሞትን ከእሱ ጋር እንደምንኖር እናምናለን።
9 ክርስቶስ አሁን ከሞት እንደተነሳና+ ዳግመኛ እንደማይሞት+ እናውቃለን፤ ከእንግዲህ ሞት በእሱ ላይ እንደ ጌታ ሊሠለጥን አይችልም።
10 ምክንያቱም እሱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኃጢአት ሞቷል፤*+ ሆኖም አሁን እየኖረ ያለውን ሕይወት የሚኖረው ለአምላክ ነው።
11 በተመሳሳይም እናንተ ለኃጢአት እንደሞታችሁ ሆኖም በክርስቶስ ኢየሱስ ለአምላክ እንደምትኖሩ አድርጋችሁ አስቡ።+
12 በመሆኑም ኃጢአት ለሰውነታችሁ ምኞት ተገዢ እንድትሆኑ በማድረግ ሟች በሆነው ሰውነታችሁ ላይ መንገሡን እንዲቀጥል አትፍቀዱ።+
13 በተጨማሪም ሰውነታችሁን* የክፋት መሣሪያ* አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፤ ከዚህ ይልቅ ከሞት ወደ ሕይወት እንደተሻገሩ ሰዎች አድርጋችሁ ራሳችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ሰውነታችሁንም* የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለአምላክ አቅርቡ።+
14 ምክንያቱም በጸጋ+ ሥር እንጂ በሕግ ሥር ስላልሆናችሁ+ ኃጢአት በእናንተ ላይ ጌታ ሊሆን አይገባም።
15 እንግዲህ ከዚህ በመነሳት ምን ማለት እንችላለን? በጸጋ ሥር እንጂ በሕግ ሥር ስላልሆንን ኃጢአት እንሥራ ማለት ነው?+ በፍጹም!
16 ለማንም ቢሆን ታዛዥ ባሪያዎች ሆናችሁ ራሳችሁን ካቀረባችሁ ለዚያ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች+ እንደሆናችሁ አታውቁም? በመሆኑም ሞት+ ለሚያስከትለው ለኃጢአት+ አለዚያም ጽድቅ ለሚያስገኘው ለታዛዥነት ባሪያዎች ናችሁ።
17 ሆኖም እናንተ በአንድ ወቅት የኃጢአት ባሪያዎች የነበራችሁ ቢሆንም እንድትከተሉት ለተሰጣችሁ ለእንዲህ ዓይነቱ ትምህርት ከልብ ስለታዘዛችሁ አምላክ የተመሰገነ ይሁን።
18 አዎ፣ ከኃጢአት ነፃ ስለወጣችሁ+ የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል።+
19 እኔ ሰዎች በሚረዱት ቋንቋ የምናገረው በሥጋችሁ ድክመት የተነሳ ነው፤ የአካል ክፍሎቻችሁን ክፉ ድርጊት ለመፈጸም ለርኩሰትና ለክፋት ባሪያዎች አድርጋችሁ አቅርባችሁ እንደነበረ ሁሉ አሁን ደግሞ የአካል ክፍሎቻችሁን ቅዱስ ሥራ ለመሥራት የጽድቅ ባሪያዎች አድርጋችሁ አቅርቡ።+
20 የኃጢአት ባሪያዎች በነበራችሁበት ጊዜ በጽድቅ ሥር አልነበራችሁምና።
21 ታዲያ በዚያን ጊዜ ታፈሯቸው የነበሩት ፍሬዎች ምን ዓይነት ነበሩ? አሁን የምታፍሩባቸው ነገሮች ናቸው። የእነዚህ ነገሮች መጨረሻ ሞት ነውና።+
22 ይሁን እንጂ አሁን ከኃጢአት ነፃ ወጥታችሁ የአምላክ ባሪያዎች ስለሆናችሁ በቅድስና ጎዳና ፍሬ እያፈራችሁ ነው፤+ የዚህም መጨረሻ የዘላለም ሕይወት ነው።+
23 የኃጢአት ደሞዝ ሞት ነውና፤*+ አምላክ የሚሰጠው ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ+ የዘላለም ሕይወት ነው።+