ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 7:1-25
7 ወንድሞች፣ (እየተናገርኩ ያለሁት ሕግ ለሚያውቁ ሰዎች ነው፤) ሕጉ በአንድ ሰው ላይ ሥልጣን የሚኖረው በሕይወት እስከኖረ ድረስ ብቻ እንደሆነ አታውቁም?
2 ለምሳሌ ያህል፣ ያገባች ሴት ባሏ በሕይወት እስካለ ድረስ በሕግ ለእሱ የታሰረች ናት፤ ባሏ ከሞተ ግን ከባሏ ሕግ ነፃ ትወጣለች።+
3 በመሆኑም ባሏ በሕይወት እያለ የሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ ትባላለች።+ ባሏ ከሞተ ግን ከእሱ ሕግ ነፃ ስለምትሆን የሌላ ወንድ ብትሆን አመንዝራ አትባልም።+
4 ስለዚህ ወንድሞቼ፣ እናንተም የሌላ ይኸውም ከሞት የተነሳው+ የክርስቶስ እንድትሆኑ+ በእሱ አካል አማካኝነት ለሕጉ ሞታችኋል፤* ይህም የሆነው ለአምላክ ፍሬ እንድናፈራ ነው።+
5 ምክንያቱም እንደ ሥጋ ፍላጎት እንኖር በነበረበት ጊዜ ሕጉ ይፋ ያወጣቸው የኃጢአት ምኞቶች ለሞት ፍሬ እንድናፈራ በሰውነታችን* ውስጥ ይሠሩ ነበር።+
6 አሁን ግን አሮጌ በሆነው በተጻፈው ሕግ+ ሳይሆን በአዲስ መልክ በመንፈስ ባሪያዎች+ እንሆን ዘንድ አስሮ ይዞን ለነበረው ሕግ ስለሞትን ከሕጉ ነፃ ወጥተናል።+
7 እንግዲህ ምን እንበል? ሕጉ ጉድለት አለበት ማለት ነው?* በፍጹም! እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጉ ባይኖር ኖሮ ኃጢአት ምን እንደሆነ ባላወቅኩ ነበር።+ ለምሳሌ ሕጉ “አትጎምጅ”+ ባይል ኖሮ መጎምጀት ምን እንደሆነ ባላወቅኩ ነበር።
8 ሆኖም ኃጢአት፣ ይህ ትእዛዝ ባስገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ ማንኛውንም ዓይነት ነገር የመጎምጀት ፍላጎት በውስጤ እንዲያድር አደረገ፤ ሕግ ባልነበረበት ጊዜ ኃጢአት የሞተ ነበርና።+
9 በእርግጥ ሕግ ባልነበረበት ጊዜ ሕያው ነበርኩ። ትእዛዙ ሲመጣ ግን ኃጢአት ዳግመኛ ሕያው ሆነ፤ እኔ ግን ሞትኩ።+
10 ወደ ሕይወት እንዲመራ የታሰበውም ትእዛዝ+ ሞት እንዳመጣ ተገነዘብኩ።
11 ምክንያቱም ኃጢአት ትእዛዙ ባስገኘው አጋጣሚ ተጠቅሞ አታሎኛል፤ እንዲሁም በትእዛዙ አማካኝነት ገድሎኛል።
12 ስለዚህ ሕጉ በራሱ ቅዱስ ነው፤ ትእዛዙም ቅዱስ፣ ጻድቅና ጥሩ ነው።+
13 ታዲያ ይህ ጥሩ የሆነው ነገር* ሞት አመጣብኝ ማለት ነው? በፍጹም! ከዚህ ይልቅ የገደለኝ ኃጢአት ነው። የኃጢአት ምንነት እንዲገለጥ ጥሩ በሆነው ነገር አማካኝነት ሞት ያመጣብኝ ኃጢአት ነው።+ ትእዛዙም ኃጢአት ምን ያህል ክፉ እንደሆነ አሳይቷል።+
14 ሕጉ መንፈሳዊ* እንደሆነ እናውቃለንና፤ እኔ ግን ለኃጢአት የተሸጥኩ ሥጋዊ ነኝ።+
15 ለምን እንዲህ እንደማደርግ አላውቅም። ለማድረግ የምፈልገውን ነገር አላደርግምና፤ ከዚህ ይልቅ የማደርገው የምጠላውን ነገር ነው።
16 ይሁን እንጂ የማደርገው የማልፈልገውን ከሆነ ሕጉ መልካም ነው በሚለው እስማማለሁ።
17 ሆኖም አሁን ይህን የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኃጢአት ነው+ እንጂ እኔ አይደለሁም።
18 ምክንያቱም በውስጤ ማለትም በሥጋዬ ውስጥ የሚኖር ምንም ጥሩ ነገር የለም፤ መልካም የሆነውን ነገር የማድረግ ፍላጎት እንጂ የመፈጸም ችሎታ የለኝም።+
19 የምመኘውን መልካም ነገር አላደርግምና፤ የማልፈልገውን መጥፎ ነገር ግን አደርጋለሁ።
20 እንግዲህ የማደርገው የማልፈልገውን ነገር ከሆነ ይህን የማደርገው እኔ ሳልሆን በውስጤ የሚኖረው ኃጢአት ነው።
21 እንግዲያው ይህ ሕግ በራሴ ላይ ሲሠራ አያለሁ፦ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው።+
22 በውስጤ በአምላክ ሕግ እጅግ ደስ ይለኛል፤+
23 በሰውነቴ* ውስጥ ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና+ በሰውነቴ* ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን+ ሌላ ሕግ አያለሁ።
24 እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! እንዲህ ወዳለው ሞት ከሚመራኝ ሰውነት ማን ይታደገኛል?
25 በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚታደገኝ አምላክ የተመሰገነ ይሁን! ስለዚህ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለአምላክ ሕግ ባሪያ ስሆን በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።+