ለሮም ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 9:1-33
9 የክርስቶስ ተከታይ እንደመሆኔ መጠን የምናገረው እውነት ነው፤ ሕሊናዬ በመንፈስ ቅዱስ እየተመራ ከእኔ ጋር ሆኖ ስለሚመሠክር አልዋሽም፤
2 ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ሥቃይ በልቤ ውስጥ አለ።
3 የሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑት ስለ ወንድሞቼ ስል እኔ ራሴ የተረገምኩ ሆኜ ከክርስቶስ ብለይ በወደድኩ ነበርና።
4 እነሱ እስራኤላውያን ናቸው፤ አምላክ ልጆቹ አድርጎ የወሰዳቸው፣+ ክብር ያገኙት፣ ቃል ኪዳን የተገባላቸው፣+ ሕግ የተሰጣቸው፣+ ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ መብት ያገኙትና+ ተስፋ የተሰጣቸው+ እነሱ ናቸው።
5 አባቶችም የእነሱ ናቸው፤+ ክርስቶስም በሥጋ የተገኘው ከእነሱ ነው።+ የሁሉ የበላይ የሆነው አምላክ ለዘላለም ይወደስ። አሜን።
6 ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ከንቱ ሆኖ ቀርቷል ማለት አይደለም። ከእስራኤል የተወለደ ሁሉ በእርግጥ “እስራኤል” አይደለምና።+
7 በተጨማሪም የአብርሃም ዘር ስለሆኑ+ ሁሉም ልጆቹ ናቸው ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ “ዘርህ የሚጠራልህ በይስሐቅ በኩል ይሆናል” ተብሎ ተጽፏል።+
8 ይህም ሲባል በሥጋ ልጆች የሆኑ በእርግጥ የአምላክ ልጆች አይደሉም፤+ በተስፋው ልጆች+ የሆኑት ግን ዘሩ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ።
9 የተስፋው ቃል “የዛሬ ዓመት በዚህ ጊዜ እመጣለሁ፤ ሣራም ወንድ ልጅ ትወልዳለች” ይላልና።+
10 ተስፋው የተሰጠው በዚያን ጊዜ ብቻ ሳይሆን ርብቃ ከአባታችን ከይስሐቅ መንታ ልጆች በፀነሰች ጊዜ ጭምር ነው፤+
11 ምርጫውን በተመለከተ የአምላክ ዓላማ በሥራ ሳይሆን በጠሪው ላይ የተመካ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ ልጆቹ ከመወለዳቸውና ጥሩም ሆነ ክፉ ከማድረጋቸው በፊት
12 ርብቃ “ታላቁ የታናሹ ባሪያ ይሆናል” ተብሎ ተነግሯት ነበር።+
13 ይህም “ያዕቆብን ወደድኩ፤ ኤሳውን ግን ጠላሁ” ተብሎ እንደተጻፈው ነው።+
14 እንግዲህ ምን እንበል? አምላክ ፍትሕ ያዛባል ማለት ነው? በፍጹም!+
15 ሙሴን “ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፤ ልራራለት የምፈልገውን ደግሞ እራራለታለሁ” ብሎታልና።+
16 ስለዚህ ይህ የተመካው በአንድ ሰው ፍላጎት ወይም ጥረት* ሳይሆን ምሕረት በሚያደርገው አምላክ ላይ ነው።+
17 ቅዱስ መጽሐፉ ስለ ፈርዖን ሲናገር “በሕይወት ያቆየሁህ ኃይሌን በአንተ ለማሳየትና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ለማድረግ ነው” ይላል።+
18 ስለዚህ አምላክ የፈለገውን ይምራል፤ የፈለገውን ደግሞ ግትር እንዲሆን ይፈቅዳል።+
19 በመሆኑም “እንደዚህ ከሆነ ታዲያ ሰዎችን ለምን ይወቅሳል?* ደግሞስ ፈቃዱን ማን መቃወም ይችላል?” ትለኝ ይሆናል።
20 ለመሆኑ ለአምላክ የምትመልሰው አንተ ማን ነህ?+ አንድ ዕቃ ቅርጽ አውጥቶ የሠራውን ሰው “ለምን እንዲህ አድርገህ ሠራኸኝ?” ይለዋል?+
21 ሸክላ ሠሪው ከዚያው ከአንዱ ጭቃ፣ አንዱን ዕቃ ክቡር ለሆነ አገልግሎት ሌላውን ዕቃ ደግሞ ክብር ለሌለው አገልግሎት ለመሥራት በጭቃው ላይ ሥልጣን እንዳለው+ አታውቅም?
22 አምላክ ቁጣውን ለማሳየትና ኃይሉ እንዲታወቅ ለማድረግ ቢፈልግም እንኳ ጥፋት የሚገባቸውን የቁጣ ዕቃዎች በብዙ ትዕግሥት ችሏቸው እንደሆነስ ምን ታውቃለህ?
23 ይህን ያደረገው ታላቅ ክብሩን አስቀድሞ ለክብር ባዘጋጃቸው የምሕረት ዕቃዎች+ ላይ ለመግለጥ
24 ይኸውም ከአይሁዳውያን ብቻ ሳይሆን ከአሕዛብም+ በጠራን በእኛ ላይ ታላቅ ክብሩን ለመግለጥ ቢሆንስ?
25 ይህም በሆሴዕ መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብሎ እንደተናገረው ነው፦ “ሕዝቤ ያልሆኑትን+ ‘ሕዝቤ’ ብዬ፣ ያልተወደደችውንም ‘የተወደደች’+ ብዬ እጠራለሁ፤
26 ‘ሕዝቤ አይደላችሁም’ ተብሎ በተነገራቸው ስፍራም በዚያ ‘የሕያው አምላክ ልጆች’ ተብለው ይጠራሉ።”+
27 ከዚህም በተጨማሪ ኢሳይያስ ስለ እስራኤል እንዲህ ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ይናገራል፦ “የእስራኤል ልጆች ቁጥር እንደ ባሕር አሸዋ ቢሆንም እንኳ የሚድኑት ቀሪዎች ብቻ ናቸው።+
28 ይሖዋ* በምድር የሚኖሩትን ይፋረዳልና፤ ይህን ደግሞ ሳይዘገይ* ይፈጽመዋል።”+
29 ደግሞም ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ* ዘር ባያስቀርልን ኖሮ እንደ ሰዶም በሆን፣ ገሞራንም በመሰልን ነበር።”+
30 እንግዲህ ምን እንበል? አሕዛብ ጽድቅን ባይከታተሉም እንኳ ጽድቅን ይኸውም በእምነት አማካኝነት የሚገኘውን ጽድቅ አገኙ፤+
31 ሆኖም እስራኤል የጽድቅን ሕግ ቢከታተልም ግቡ ላይ አልደረሰም፤ ይኸውም ሕጉን አልፈጸመም።
32 ይህ የሆነው ለምንድን ነው? በእምነት ሳይሆን በሥራ የሚገኝ እንደሆነ አድርገው ስለተከታተሉት ነው። ስለዚህ “በማሰናከያ ድንጋይ” ተሰናከሉ፤+
33 ይህም “እነሆ፣ በጽዮን የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዓለት አኖራለሁ፤+ በእሱ ላይ እምነት የሚጥል ግን አያፍርም”+ ተብሎ እንደተጻፈው ነው።