ሰቆቃወ ኤርምያስ 5:1-22

  • ሕዝቡ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ለመመለስ ያቀረበው ጸሎት

    • “የደረሰብንን ነገር አስታውስ” (1)

    • “ኃጢአት ስለሠራን ወዮልን!” (16)

    • ‘ይሖዋ ሆይ፣ መልሰን’ (21)

    • ‘ዘመናችንን አድስልን’ (21)

5  ይሖዋ ሆይ፣ የደረሰብንን ነገር አስታውስ። ውርደታችንን እይ፤ ደግሞም ተመልከት።+   ርስታችን ለእንግዶች፣ ቤቶቻችን ለባዕድ አገር ሰዎች ተሰጡ።+   አባት እንደሌላቸው ወላጅ አልባ ልጆች ሆንን፤ እናቶቻችን እንደ መበለቶች ሆኑ።+   የገዛ ራሳችንን ውኃ ለመጠጣት መክፈል ነበረብን፤+ የገዛ እንጨታችንን የምናገኘውም በግዢ ነበር።   አሳዳጆቻችን አንገታችንን ሊይዙ ተቃረቡ፤ዝለናል፤ እረፍት የሚባል ነገርም አላገኘንም።+   በቂ ምግብ ለማግኘት ወደ ግብፅና ወደ አሦር እጃችንን ዘረጋን።+   ኃጢአት የሠሩት አባቶቻችን አሁን በሕይወት የሉም፤ እኛ ግን የእነሱን በደል ለመሸከም ተገደድን።   አሁን አገልጋዮች ይገዙናል፤ ከእጃቸው የሚያስጥለን ማንም የለም።   በምድረ በዳ ካለው ሰይፍ የተነሳ ምግባችንን የምናመጣው በሕይወታችን* ቆርጠን ነው።+ 10  ከከባድ ረሃብ የተነሳ ቆዳችን እንደ ምድጃ ጋለ።+ 11  በጽዮን ያሉ ሚስቶችና በይሁዳ ከተሞች ያሉ ደናግል ተዋረዱ።*+ 12  መኳንንቱ በእጃቸው ተንጠለጠሉ፤+ ሽማግሌዎችም አልተከበሩም።+ 13  ወጣቶች ወፍጮውን ይሸከማሉ፤ ልጆችም ከባድ እንጨት ሲሸከሙ ይደናቀፋሉ። 14  ሽማግሌዎች ከከተማዋ በር ሄደዋል፤+ ወጣቶችም ሙዚቃቸውን መጫወት አቁመዋል።+ 15  ደስታ ከልባችን ራቀ፤ ጭፈራችን በሐዘን ተተካ።+ 16  ራሳችን ላይ ያለው አክሊል ወድቋል። ኃጢአት ስለሠራን ወዮልን! 17  ከዚህ የተነሳ ልባችን ታመመ፤+ከእነዚህም ነገሮች የተነሳ ዓይኖቻችን ፈዘዙ፤+ 18  ባድማ የሆነችው የጽዮን ተራራ+ አሁን የቀበሮዎች መፈንጫ ሆናለችና። 19  ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ግን ለዘላለም በዙፋንህ ላይ ትቀመጣለህ። ዙፋንህ ከትውልድ እስከ ትውልድ ነው።+ 20  ለዘላለም የረሳኸንና ለረጅም ዘመን የተውከን ለምንድን ነው?+ 21  ይሖዋ ሆይ፣ ወደ አንተ መልሰን፤ እኛም በፈቃደኝነት እንመለሳለን።+ ዘመናችንን እንደቀድሞው አድስልን።+ 22  አንተ ግን ፈጽሞ ጥለኸናል። አሁንም በእኛ ላይ እጅግ እንደተቆጣህ ነህ።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በነፍሳችን።”
ወይም “ተደፈሩ።”