ሶፎንያስ 3:1-20
3 ዓመፀኛ ለሆነችው፣ ለረከሰችውና ለጨቋኟ ከተማ ወዮላት!+
2 ማንንም ለመታዘዝ ፈቃደኛ አልሆነችም፤+ ምንም ዓይነት ተግሣጽ አልተቀበለችም።+
በይሖዋ አልታመነችም፤+ ወደ አምላኳም አልቀረበችም።+
3 በውስጧ ያሉት መኳንንቷ የሚያገሱ አንበሶች ናቸው።+
ፈራጆቿ የሌሊት ተኩላዎች ናቸው፤ለጠዋት ምንም ሳያስቀሩ አጥንቱን ሁሉ ይግጣሉ።
4 ነቢያቷ እብሪተኞችና አታላዮች ናቸው።+
ካህናቷ ቅዱስ የሆነውን ነገር ያረክሳሉ፤+በሕጉ ላይ ያምፃሉ።+
5 በመካከሏ ያለው ይሖዋ ጻድቅ ነው፤+ እሱ ምንም ዓይነት ስህተት አይፈጽምም።
ፍርዱን እንደማይነጥፍ የንጋት ብርሃን፣በየማለዳው ያሳውቃል።+
ክፉ ሰው ግን ኀፍረት የሚባል ነገር አያውቅም።+
6 “ብሔራትን አጥፍቻለሁ፤ በቅጥር ማዕዘኖች ላይ ያሉ ማማዎቻቸው ወድመዋል።
ማንም ሰው እንዳያልፍባቸው መንገዶቻቸውን አፍርሻለሁ።
ከተሞቻቸው ፈራርሰዋል፤ በዚያ አንድም ሰው የለም፤ ነዋሪም አይገኝባቸውም።+
7 እኔም ‘በእርግጥ ትፈሪኛለሽ፤ ተግሣጽም* ትቀበያለሽ’ አልኩ፤+
ይህም መኖሪያዋ እንዳይጠፋ ነው፤+ለሠራችው ኃጢአት ሁሉ ተጠያቂ አደርጋታለሁ።*
እነሱ ግን ብልሹ ነገር ለመፈጸም ይበልጥ ጓጉ።+
8 ‘ስለዚህ ለመበዝበዝ እስከምነሳበት ቀን* ድረስእኔን በተስፋ ተጠባበቁ’*+ ይላል ይሖዋ፤‘ብሔራትን ለመሰብሰብ፣ መንግሥታትን ለማከማቸት፣በእነሱም ላይ መዓቴንና የሚነደውን ቁጣዬን ሁሉ ለማውረድ የፍርድ ውሳኔ አስተላልፌአለሁና፤+መላዋ ምድር በቅንዓቴ እሳት ትበላለች።+
9 በዚያን ጊዜ ሰዎች ሁሉ የይሖዋን ስም እንዲጠሩናእጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲያገለግሉት*ቋንቋቸውን ለውጬ ንጹሕ ቋንቋ እሰጣቸዋለሁ።’+
10 የሚለምኑኝ ሰዎች ይኸውም የተበተኑት ሕዝቦቼየኢትዮጵያ ወንዞች ከሚገኙበት ስፍራ ስጦታ ያመጡልኛል።+
11 በዚያን ቀን በእኔ ላይ በማመፅ በፈጸምሻቸው ሥራዎች ሁሉለኀፍረት አትዳረጊም፤+በዚያን ጊዜ በትዕቢት ጉራ የሚነዙትን ከመካከልሽ አስወግዳለሁና፤አንቺም ከእንግዲህ በተቀደሰው ተራራዬ ላይ ፈጽሞ አትታበዪም።+
12 እኔም ትሑት የሆነና ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሕዝብ በመካከላችሁ እንዲቀር አደርጋለሁ፤+እነሱም የይሖዋን ስም መጠጊያቸው ያደርጉታል።
13 የእስራኤል ቀሪዎች+ ምንም ዓይነት ክፋት አይሠሩም፤+ውሸት አይናገሩም፤ በአፋቸውም ውስጥ አታላይ ምላስ አይገኝም፤ይልቁንም ይመገባሉ፤* ይተኛሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።”+
14 የጽዮን ሴት ልጅ ሆይ፣ እልል በይ!
እስራኤል ሆይ፣ በድል አድራጊነት ጩኺ!+
የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ሆይ፣ በሙሉ ልብሽ ደስ ይበልሽ፤ ሐሴትም አድርጊ!+
15 ይሖዋ በአንቺ ላይ የተላለፈውን ፍርድ ሽሯል።+
ጠላትሽን ከአንቺ መልሷል።+
የእስራኤል ንጉሥ ይሖዋ በመካከልሽ ነው።+
ከእንግዲህ ወዲህ ጥፋት አያስፈራሽም።+
16 በዚያን ቀን ለኢየሩሳሌም እንዲህ ይባላል፦
“ጽዮን ሆይ፣ አትፍሪ።+
እጆችሽ አይዛሉ።
17 አምላክሽ ይሖዋ በመካከልሽ ነው።+
እንደ ኃያል ተዋጊ ያድናል።
በታላቅ ደስታ በአንቺ ሐሴት ያደርጋል።+
ለአንቺ ፍቅር በማሳየቱ ረክቶ ዝም ይላል።*
በእልልታ በአንቺ ሐሴት ያደርጋል።
18 በበዓላትሽ ላይ ባለመገኘታቸው ያዘኑትን ሰዎች እሰበስባለሁ፤+ለእሷ ሲሉ በደረሰባቸው ነቀፋ የተነሳ ወደ አንቺ አልመጡም።+
19 እነሆ፣ በዚያን ጊዜ በሚጨቁኑሽ ሁሉ ላይ እርምጃ እወስዳለሁ፤+የምታነክሰውንም አድናታለሁ፤+የተበተነችውንም እሰበስባለሁ።+
ኀፍረት በተከናነቡበት ምድር ሁሉእንዲወደሱና ዝና* እንዲያተርፉ አደርጋቸዋለሁ።
20 በዚያን ጊዜ መልሼ አመጣችኋለሁ፤አዎ፣ በዚያን ጊዜ እሰበስባችኋለሁ።
ተማርከው የተወሰዱባችሁን ሰዎች በፊታችሁ መልሼ በምሰበስብበት ጊዜ+በምድር ሕዝቦች ሁሉ መካከል ዝና* እንድታተርፉና እንድትወደሱ አደርጋለሁና”+ ይላል ይሖዋ።