ለቆላስይስ ሰዎች የተጻፈ ደብዳቤ 2:1-23
2 ለእናንተና በሎዶቅያ+ ላሉት እንዲሁም በአካል አይተውኝ ለማያውቁ* ሁሉ ስል ምን ያህል ብርቱ ትግል እያደረግኩ እንዳለሁ እንድትገነዘቡ እፈልጋለሁ።
2 ይህም ልባቸው እንዲጽናና+ እንዲሁም ስምም ሆነው በፍቅር እርስ በርስ እንዲተሳሰሩ ነው።+ በዚህ መንገድ ታላቅ የሆነውን ብልጽግና ይኸውም ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ የሆኑበትን የእውነት ግንዛቤ ማግኘት ብሎም የአምላክ ቅዱስ ሚስጥር ስለሆነው ስለ ክርስቶስ+ ትክክለኛ እውቀት መቅሰም ይችላሉ።
3 የጥበብና የእውቀት ውድ ሀብት ሁሉ በሚገባ ተሰውሮ የሚገኘው በክርስቶስ ውስጥ ነው።+
4 ይህን የምለው ማንም ሰው አግባብቶ እንዳያታልላችሁ ነው።
5 በአካል ከእናንተ ጋር ባልሆንም በመንፈስ ግን ከእናንተ ጋር ስለሆንኩ ሥርዓት ያለውን አኗኗራችሁንና+ በክርስቶስ ላይ ያላችሁን ጽኑ እምነት+ በማየት እየተደሰትኩ ነው።
6 ስለዚህ ጌታ ክርስቶስ ኢየሱስን እንደተቀበላችሁት ሁሉ ከእሱ ጋር በአንድነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ፤
7 በተማራችሁት መሠረት በእሱ ላይ ሥር ሰዳችሁና ታንጻችሁ ኑሩ፤+ እንዲሁም በእምነት ጸንታችሁ መኖራችሁን ቀጥሉ፤+ ብዙ ምስጋናም አቅርቡ።+
8 በክርስቶስ ላይ ሳይሆን በዓለም መሠረታዊ ነገሮች እንዲሁም በሰው ወግ ላይ በተመሠረተ ፍልስፍናና ከንቱ ማታለያ+ ማንም ማርኮ* እንዳይወስዳችሁ ተጠንቀቁ፤
9 ምክንያቱም መለኮታዊው ባሕርይ በተሟላ ሁኔታ በአካል የሚኖረው በእሱ ውስጥ ነው።+
10 በመሆኑም የገዢነትና የሥልጣን ሁሉ ራስ+ በሆነው በእሱ አማካኝነት ሁሉንም ነገር አግኝታችኋል።
11 ከእሱ ጋር ባላችሁ ዝምድና የተነሳ በእጅ ባልተከናወነ ግርዘት ተገርዛችኋል፤ ይህም ኃጢአተኛውን ሥጋዊ አካል በማስወገድ+ የሚከናወን የክርስቶስ አገልጋዮች ግርዘት ነው።+
12 የእሱን ዓይነት ጥምቀት በመጠመቅ ከእሱ ጋር ተቀብራችሁ ነበርና፤+ ከእሱ ጋር ባላችሁ ዝምድና የተነሳም አብራችሁ ተነስታችኋል፤+ ይህም የሆነው እሱን ከሞት ያስነሳው+ አምላክ ባከናወነው ታላቅ ሥራ ላይ ባላችሁ እምነት አማካኝነት ነው።
13 በተጨማሪም በበደላችሁና በሥጋችሁ አለመገረዝ የተነሳ ሙታን የነበራችሁ ቢሆንም አምላክ ከእሱ ጋር ሕያዋን አድርጓችኋል።+ በደላችንን ሁሉ በደግነት ይቅር ብሎናል፤+
14 ድንጋጌዎችን የያዘውንና+ ይቃወመን የነበረውን+ በእጅ የተጻፈ ሰነድም ደመሰሰው።+ በመከራው እንጨት* ላይ ቸንክሮም ከመንገድ አስወገደው።+
15 በመከራው እንጨት* አማካኝነት መንግሥታትንና ባለሥልጣናትን ገፎ በድል ሰልፍ እየመራ እንደ ምርኮኛ በአደባባይ እንዲታዩ አድርጓቸዋል።+
16 ስለዚህ በምትበሉትም ሆነ በምትጠጡት ወይም በዓልን፣ የወር መባቻንና*+ ሰንበትን በማክበር+ ረገድ ማንም ሰው አይፍረድባችሁ።+
17 እነዚህ ለሚመጡት ነገሮች ጥላ ናቸው፤+ እውነተኛው ነገር* ግን የክርስቶስ ነው።+
18 በውሸት ትሕትናና በመላእክት አምልኮ* የሚደሰት ማንኛውም ሰው ሽልማቱን እንዲያሳጣችሁ አትፍቀዱ።+ እንዲህ ያለ ሰው ባያቸው ነገሮች ላይ ተመሥርቶ “ጥብቅ አቋም የሚይዝ”* ከመሆኑም በላይ ሥጋዊ አስተሳሰቡ በከንቱ እንዲታበይ ያደርገዋል።
19 እነዚህ ሰዎች ራስ+ ከሆነው ጋር በጥብቅ የተቆራኙ አይደሉም፤ መላው አካል በመገጣጠሚያዎችና በጅማቶች አማካኝነት የሚያስፈልገውን ነገር የሚያገኘውና እርስ በርስ ስምም ሆኖ የተያያዘው እንዲሁም የሚያድገው ራስ በሆነው አማካኝነት ነው። ይህም እድገት የሚገኘው ከአምላክ ነው።+
20 የዚህን ዓለም መሠረታዊ ነገሮች በመተው ከክርስቶስ ጋር ከሞታችሁ+ ለድንጋጌዎቹ+ ራሳችሁን በማስገዛት አሁንም የዓለም ክፍል የሆናችሁ በሚመስል ሁኔታ ለምን ትኖራላችሁ?
21 ድንጋጌዎቹም “አትውሰድ፣ አትቅመስ፣ አትንካ” የሚሉ ናቸው።
22 እነዚህ ሁሉ የሰው ትእዛዛትና ትምህርቶች ስለሆኑ ሁሉም ጥቅም ላይ ውለው እንዲጠፉ የተወሰነባቸው ናቸው።+
23 እነዚህ ነገሮች በገዛ ፈቃድ በሚቀርብ አምልኮና በውሸት ትሕትና፣ ሰውነትን በማሠቃየት+ የሚገለጹ ጥበብ ያለባቸው ነገሮች ቢመስሉም የሥጋን ፍላጎት በማሸነፍ ረገድ አንዳች ፋይዳ የላቸውም።