ነህምያ 2:1-20
2 ንጉሥ አርጤክስስ+ በነገሠ በ20ኛው ዓመት+ በኒሳን* ወር በንጉሡ ፊት የወይን ጠጅ ቀርቦ ነበር፤ እኔም እንደተለመደው የወይን ጠጁን አንስቼ ለንጉሡ ሰጠሁት።+ ሆኖም ከዚህ ቀደም እሱ ጋ ስቀርብ በፊቴ ላይ ሐዘን ታይቶ አያውቅም ነበር።
2 በመሆኑም ንጉሡ “ሳትታመም ፊትህ እንዲህ በሐዘን የጠቆረው ለምንድን ነው? ይህ መቼም የልብ ሐዘን እንጂ ሌላ ነገር ሊሆን አይችልም” አለኝ። በዚህ ጊዜ በጣም ፈራሁ።
3 ከዚያም ንጉሡን እንዲህ አልኩት፦ “ንጉሡ ለዘላለም ይኑር! አባቶቼ የተቀበሩባት ከተማ ፈራርሳ፣ በሮቿም በእሳት ተቃጥለው እያለ ለምን ፊቴ በሐዘን አይጠቁር?”+
4 ንጉሡም መልሶ “ታዲያ ምን እንዳደርግልህ ትፈልጋለህ?” አለኝ። እኔም ወዲያውኑ ወደ ሰማይ አምላክ ጸለይኩ።+
5 ከዚያም ንጉሡን እንዲህ አልኩት፦ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነና አገልጋይህ በፊትህ ሞገስ ካገኘ ከተማዋን መልሼ እንድገነባ አባቶቼ ወደተቀበሩባት ከተማ፣ ወደ ይሁዳ እንድሄድ ፍቀድልኝ።”+
6 ንጉሡም ንግሥቲቱ አጠገቡ ተቀምጣ ሳለ “ጉዞህ ምን ያህል ጊዜ ይፈጃል? መቼ ትመለሳለህ?” አለኝ። ንጉሡም ደስ ብሎት እንድሄድ ፈቀደልኝ፤+ እኔም ጊዜውን ቆርጬ ነገርኩት።+
7 ከዚያም ንጉሡን እንዲህ አልኩት፦ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ ከወንዙ+ ባሻገር* ያለው ክልል ገዢዎች ይሁዳ እስክደርስ ድረስ በሰላም ምድራቸውን አቋርጬ እንዳልፍ እንዲፈቅዱልኝ ደብዳቤ ይሰጠኝ፤
8 በተጨማሪም የንጉሡ መናፈሻ ቦታ* ጠባቂ የሆነው አሳፍ ለቤቱ* የግንብ አጥር+ በሮች፣ ለከተማዋ ቅጥሮችና+ ለምሄድበት ቤት የሚያገለግሉ ሳንቃዎች እንዲሰጠኝ ደብዳቤ ይጻፍልኝ።” በዚህ ጊዜ መልካም የሆነው የአምላኬ እጅ በእኔ ላይ ስለነበር+ ንጉሡ እነዚህን ሰጠኝ።+
9 በመጨረሻም ከወንዙ ባሻገር ወዳለው ክልል ገዢዎች ሄጄ የንጉሡን ደብዳቤዎች ሰጠኋቸው። በተጨማሪም ንጉሡ የጦር አለቆችና ፈረሰኞች አብረውኝ እንዲሄዱ አድርጎ ነበር።
10 ሆሮናዊው ሳንባላጥና+ አሞናዊው+ ባለሥልጣን* ጦብያ+ ይህን ነገር ሲሰሙ ለእስራኤላውያን መልካም ነገር የሚያደርግ ሰው በመምጣቱ በጣም ተበሳጩ።
11 በመጨረሻም ኢየሩሳሌም ደረስኩ፤ እዚያም ሦስት ቀን ቆየሁ።
12 ከዚያም በሌሊት ተነሳሁ፤ ከእኔም ጋር ጥቂት ሰዎች ነበሩ፤ አምላኬ ለኢየሩሳሌም እንዳደርግ በልቤ ያኖረውን ነገር ለማንም ሰው አልተናገርኩም፤ ከተቀመጥኩበት እንስሳም በስተቀር ሌላ እንስሳ ከእኔ ጋር አልነበረም።
13 በሌሊትም በሸለቆ በር+ ከወጣሁ በኋላ በትልቁ እባብ ምንጭ ፊት ለፊት በማለፍ ወደ አመድ ቁልል በር+ ሄድኩ፤ የፈራረሱትን የኢየሩሳሌም ቅጥሮችና በእሳት የተቃጠሉትን በሮቿንም አንድ በአንድ መረመርኩ።+
14 ከዚያም አልፌ ወደ ምንጭ በርና+ ወደ ንጉሡ ኩሬ ሄድኩ፤ በዚያም የተቀመጥኩበትን እንስሳ ማሳለፍ የሚያስችል በቂ ቦታ አልነበረም።
15 ሆኖም ሌሊቱን ሸለቆውን*+ ይዤ ሽቅብ ወጣሁ፤ ቅጥሩንም መመርመሬን ቀጠልኩ፤ ከዚያም ተመልሼ በሸለቆ በር ገባሁ፤ በኋላም ወደመጣሁበት ተመለስኩ።
16 ለአይሁዳውያኑ፣ ለካህናቱ፣ ለተከበሩት ሰዎች፣ ለበታች ገዢዎቹና+ ለቀሩት ሠራተኞች ገና ምንም የነገርኳቸው ነገር ስላልነበር የበታች ገዢዎቹ የት እንደሄድኩና ምን እያደረግኩ እንደነበር አላወቁም።
17 በመጨረሻም እንዲህ አልኳቸው፦ “መቼም ያለንበት ሁኔታ ምን ያህል አሳዛኝ እንደሆነ ሳትመለከቱ አትቀሩም፤ ኢየሩሳሌም ፈራርሳለች፣ በሮቿም በእሳት ተቃጥለዋል። እንግዲህ ተዋርደን እንዳንቀር ኑና የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሰን እንገንባ።”
18 ከዚያም የአምላኬ መልካም እጅ ምን ያህል በእኔ ላይ እንደነበርና+ ንጉሡም ምን እንዳለኝ ነገርኳቸው።+ እነሱም “እንነሳና እንገንባ” አሉ። በመሆኑም መልካሙን ሥራ ለመሥራት ራሳቸውን* አበረቱ።+
19 ሆሮናዊው ሳንባላጥና አሞናዊው+ ባለሥልጣን* ጦብያ+ እንዲሁም የዓረብ+ ተወላጅ የሆነው ጌሼም ይህን ሲሰሙ ያፌዙብንና+ በንቀት ዓይን ይመለከቱን ጀመር፤ እንዲህም አሉን፦ “ምን እያደረጋችሁ ነው? በንጉሡ ላይ ልታምፁ ነው?”+
20 እኔም እንዲህ ብዬ መለስኩላቸው፦ “ሥራችንን የሚያሳካልን የሰማይ አምላክ ነው፤+ እኛ አገልጋዮቹም ተነስተን እንገነባለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም ምንም ዓይነት ድርሻም ሆነ መብት ወይም መታሰቢያ የላችሁም።”+