አሞጽ 2:1-16

  • በተደጋጋሚ በተፈጸመ ዓመፅ የተነሳ የተላለፈ ፍርድ (1-16)

    • ሞዓብ (1-3)፣ ይሁዳ (4, 5)፣ እስራኤል (6-16)

2  “ይሖዋ እንዲህ ይላል፦‘“ስለ ሦስቱ የሞዓብ ዓመፅ*+ ብሎም ስለ አራቱ እጄን አልመልስም፤ምክንያቱም ኖራ ለማግኘት የኤዶምን ንጉሥ አጥንቶች አቃጥሏል።   በመሆኑም በሞዓብ ላይ እሳት እሰዳለሁ፤ የቀሪዮትንም+ የማይደፈሩ ማማዎች ይበላል፤ ሞዓብ በትርምስ፣በቀረርቶና በቀንደ መለከት ድምፅ መካከል ይሞታል።+   ገዢውን* ከመካከሏ አስወግዳለሁ፤መኳንንቷንም ሁሉ ከእሱ ጋር እገድላለሁ”+ ይላል ይሖዋ።’   ይሖዋ እንዲህ ይላል፦‘ስለ ሦስቱ የይሁዳ ዓመፅ+ ብሎም ስለ አራቱ እጄን አልመልስም፤ምክንያቱም የይሖዋን ሕግ* ንቀዋል፤ሥርዓቱንም አልጠበቁም፤+ይልቁንም አባቶቻቸው በተከተሉት በዚያው ውሸት ስተዋል።+   በመሆኑም በይሁዳ ላይ እሳት እሰዳለሁ፤የኢየሩሳሌምንም የማይደፈሩ ማማዎች ይበላል።’+   ይሖዋ እንዲህ ይላል፦‘ስለ ሦስቱ የእስራኤል ዓመፅ+ ብሎም ስለ አራቱ እጄን አልመልስም፤ምክንያቱም ጻድቁን ለብር፣*ድሃውንም ለጥንድ ጫማ ሲሉ ይሸጣሉ።+   የችግረኞችን ራስ በምድር አፈር ላይ ይረግጣሉ፤+የየዋሆችንም መንገድ ይዘጋሉ።+ አባትና ልጅ ከአንዲት ሴት ጋር ግንኙነት በመፈጸምቅዱስ ስሜን ያረክሳሉ።   የብድር መያዣ አድርገው በወሰዱት ልብስ+ ላይ በየመሠዊያው ሥር ይተኛሉ፤+መቀጫ በማስከፈል ያገኙትን የወይን ጠጅ በአማልክታቸው ቤት* ይጠጣሉ።’   ‘ይሁንና ቁመቱ እንደ አርዘ ሊባኖስ፣ ጥንካሬውም እንደ ባሉጥ ዛፍ የሆነውን አሞራዊበፊታቸው ያጠፋሁት እኔ ነኝ፤+ከላይ ያለውን ፍሬውንም ሆነ ከታች ያሉትን ሥሮቹን አጠፋሁ።+ 10  ከግብፅ ምድር አወጣኋችሁ፤+የአሞራዊውንም ምድር እንድትወርሱበምድረ በዳ ለ40 ዓመት መራኋችሁ።+ 11  ከልጆቻችሁ መካከል አንዳንዶቹን ነቢያት፣+ከወጣቶቻችሁም መካከል አንዳንዶቹን ናዝራውያን አድርጌ አስነሳሁ።+ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፣ ይህን አላደረግኩም?’ ይላል ይሖዋ። 12  ‘እናንተ ግን ናዝራውያኑ የወይን ጠጅ እንዲጠጡ ሰጣችኋቸው፤+ነቢያቱንም “ትንቢት አትናገሩ” በማለት አዘዛችኋቸው።+ 13  ስለዚህ በታጨደ እህል የተሞላ ጋሪ ከሥሩ ያለውን እንደሚያደቅ፣ባላችሁበት ስፍራ አደቃችኋለሁ። 14  ፈጣኑ ሰው የሚሸሽበት ቦታ አያገኝም፤+ብርቱ የሆነው ሰው ኃይሉን ይዞ አይቀጥልም፤ተዋጊውም ሕይወቱን* አያድንም። 15  ቀስተኛው በቦታው ጸንቶ አይቆምም፤ፈጣኑም ሮጦ አያመልጥም፤ፈረሰኛውም ሕይወቱን* አያድንም። 16  ከተዋጊዎቹ መካከል እጅግ ደፋር* የሆነው እንኳበዚያን ቀን ራቁቱን ይሸሻል’+ ይላል ይሖዋ።”

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ወንጀል።”
ቃል በቃል “ፈራጅ የሆነውን።”
ወይም “መመሪያ፤ ትምህርት።”
ብር የተባለውን ማዕድን ያመለክታል።
ወይም “ቤተ መቅደስ።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወይም “ልበ ሙሉ።”