አስቴር 4:1-17

  • መርዶክዮስ አለቀሰ (1-5)

  • መርዶክዮስ አስቴርን አንድ እርምጃ እንድትወስድ ጠየቃት (6-17)

4  መርዶክዮስ+ የተደረገውን ነገር ሁሉ ባወቀ ጊዜ+ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅም ለበሰ፤ በራሱም ላይ አመድ ነሰነሰ። ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ እየጮኸና ምርር ብሎ እያለቀሰ ወደ ከተማዋ መሃል ወጣ።  ማንም ሰው ማቅ ለብሶ በንጉሡ በር እንዲገባ ስለማይፈቀድለት እስከ ንጉሡ በር ድረስ መጣ።  የንጉሡ ቃልና ድንጋጌ በተሰማባቸው አውራጃዎች በሙሉ+ በሚገኙ አይሁዳውያን መካከል ታላቅ ሐዘን ሆነ፤ እነሱም ጾሙ፤+ አለቀሱ፤ እንዲሁም ዋይታ አሰሙ። ብዙዎቹ ማቅ አንጥፈው፣ አመድ ነስንሰው ተኙ።+  የአስቴር ሴት አገልጋዮችና ጃንደረቦችም ወደ እሷ ገብተው በነገሯት ጊዜ ንግሥቲቱ እጅግ ተጨነቀች። ከዚያም መርዶክዮስ ማቁን አውልቆ የሚለብሰው ልብስ ላከችለት፤ እሱ ግን አልተቀበለም።  በዚህ ጊዜ አስቴር ከንጉሡ ጃንደረቦች አንዱ የሆነውንና ንጉሡ እሷን እንዲያገለግል የመደበውን ሃታክን ጠርታ ወደ መርዶክዮስ ሄዶ ምን ችግር እንደተፈጠረና ምን እንደተከሰተ እንዲያጣራ አዘዘችው።  ስለዚህ ሃታክ በንጉሡ በር ፊት ለፊት ባለው የከተማዋ አደባባይ ወደሚገኘው ወደ መርዶክዮስ ወጣ።  መርዶክዮስም ያጋጠመውን ነገር ሁሉ ነገረው፤ እንዲሁም ሃማ አይሁዳውያንን ለማጥፋት+ ወደ ንጉሡ ግምጃ ቤት ለማስገባት ቃል ስለገባው ገንዘብ መጠን ነገረው።+  በተጨማሪም እነሱን ለማጥፋት በሹሻን*+ በጽሑፍ የወጣውን ድንጋጌ ቅጂ ሰጠው። ቅጂውን ለአስቴር እንዲያሳያትና እንዲያስረዳት እንዲሁም ወደ ንጉሡ ገብታ ሞገስ እንዲያሳያት እንድትለምነውና ስለ ሕዝቧ በግንባር ቀርባ እንድትማጸነው ይነግራት ዘንድ+ አሳሰበው።  ሃታክ ተመልሶ መርዶክዮስ ያለውን ለአስቴር ነገራት። 10  አስቴርም ለመርዶክዮስ+ እንዲህ ብሎ እንዲነግረው ሃታክን አዘዘችው፦ 11  “የንጉሡ አገልጋዮች ሁሉና በንጉሡ አውራጃዎች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ ሳይጠራ ወደ ንጉሡ ውስጠኛ ግቢ+ የሚገባን ማንኛውንም ወንድ ወይም ሴት በተመለከተ ንጉሡ አንድ ሕግ እንዳለው ያውቃሉ፦ እንዲህ ያደረገ ሰው ይገደላል፤ ሰውየው በሕይወት ሊተርፍ የሚችለው ንጉሡ የወርቅ በትረ መንግሥቱን ከዘረጋለት ብቻ ነው።+ እኔ ደግሞ ላለፉት 30 ቀናት ወደ ንጉሡ እንድገባ አልተጠራሁም።” 12  መርዶክዮስ፣ የአስቴር ቃል በተነገረው ጊዜ 13  ለአስቴር ይህን መልስ ላከ፦ “በንጉሡ ቤት ስላለሽ ብቻ ከሌሎቹ አይሁዳውያን ተለይቼ እኔ እተርፋለሁ ብለሽ እንዳታስቢ። 14  በዚህ ጊዜ አንቺ ዝም ብትዪ አይሁዳውያን እፎይታና መዳን ከሌላ ቦታ ያገኛሉ፤+ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ። ደግሞስ ንግሥት ለመሆን የበቃሽው እንዲህ ላለው ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?”+ 15  ከዚያም አስቴር በምላሹ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ መርዶክዮስ ላከች፦ 16  “ሂድ፤ በሹሻን* ያሉትን አይሁዳውያን ሁሉ ሰብስብ፤ ስለ እኔም ጹሙ።+ ቀንም ሆነ ሌሊት ለሦስት ቀን እንዳትበሉ እንዲሁም እንዳትጠጡ።+ እኔም ከሴት አገልጋዮቼ ጋር እጾማለሁ። ከዚያም ሕጉ ባይፈቅድም እንኳ ወደ ንጉሡ እገባለሁ፤ ከጠፋሁም ልጥፋ።” 17  በመሆኑም መርዶክዮስ ሄደ፤ አስቴር ያዘዘችውንም ነገር ሁሉ አደረገ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “በሱሳ።”
ወይም “በሱሳ።”