አስቴር 5:1-14

  • አስቴር ንጉሡ ፊት ቀረበች (1-8)

  • የሃማ ቁጣና እብሪት (9-14)

5  በሦስተኛው ቀን+ አስቴር ልብሰ መንግሥቷን ለብሳ ከንጉሡ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው በንጉሡ ቤት* ውስጠኛ ግቢ ቆመች፤ ንጉሡም በመግቢያው ፊት ለፊት በሚገኘው በንጉሡ ቤት ውስጥ በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር።  ንጉሡ፣ ንግሥት አስቴርን ግቢ ውስጥ ቆማ ሲያያት በፊቱ ሞገስ አገኘች፤ ንጉሡም እጁ ላይ የነበረውን የወርቅ በትረ መንግሥት ለአስቴር ዘረጋላት።+ በዚህ ጊዜ አስቴር ቀርባ የበትሩን ጫፍ ነካች።  ንጉሡም “ንግሥት አስቴር ሆይ፣ ምን ችግር አጋጠመሽ? የምትፈልጊው ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!” አላት።  አስቴርም መልሳ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ ንጉሡ ለእሱ ባዘጋጀሁት ግብዣ ላይ ዛሬ ከሃማ+ ጋር ይገኝልኝ” አለች።  በመሆኑም ንጉሡ አገልጋዮቹን “አስቴር ባቀረበችው ጥያቄ መሠረት በአስቸኳይ እንዲመጣ ለሃማ ንገሩት” አለ። ስለዚህ ንጉሡና ሃማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ።  በወይን ጠጅ ግብዣው ላይ ንጉሡ አስቴርን እንዲህ አላት፦ “የምትጠይቂው ምንድን ነው? የጠየቅሽው ይሰጥሻል! የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!”+  አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “የምጠይቀውም ሆነ የምፈልገው ነገር ይህ ነው፦  በንጉሡ ዘንድ ሞገስ ካገኘሁ እንዲሁም ንጉሡ የምጠይቀውን ነገር መስጠትና የምፈልገውን መፈጸም ደስ ካሰኘው ነገ ንጉሡና ሃማ ለእነሱ በማዘጋጅላቸው ግብዣ ላይ ይገኙ፤ እኔም በነገው ዕለት ንጉሡ ያለውን አደርጋለሁ።”  በዚያ ቀን ሃማ ተደስቶ ልቡም ሐሴት አድርጎ ወጣ። ሆኖም ሃማ፣ መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ሲያየው እንዲሁም እንዳልተነሳለትና በፊቱ እንዳልተንቀጠቀጠ ሲመለከት በመርዶክዮስ ላይ ቁጣው ነደደ።+ 10  ይሁንና ሃማ ራሱን ተቆጣጥሮ ወደ ቤቱ ሄደ። ከዚያም ጓደኞቹንና ሚስቱን ዜሬሽን+ አስጠራቸው። 11  ሃማም ስለ ሀብቱ ታላቅነትና ስለ ወንዶች ልጆቹ ብዛት+ እንዲሁም ንጉሡ ላቅ ያለ ሹመት እንደሰጠውና ከመኳንንቱም ሆነ ከንጉሡ አገልጋዮች በላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገው+ በጉራ ይነግራቸው ጀመር። 12  ሃማ በመቀጠል እንዲህ አለ፦ “ምን ይሄ ብቻ፣ ንግሥት አስቴር አዘጋጅታ በነበረው ግብዣ+ ላይ ከንጉሡ ጋር እንድገኝ የጋበዘችው እኔን ብቻ ነው። በተጨማሪም ነገ ከንጉሡና ከእሷ ጋር እንድገኝ ጋብዛኛለች።+ 13  ይሁን እንጂ አይሁዳዊውን መርዶክዮስን በንጉሡ በር ላይ ተቀምጦ የማየው ከሆነ ይህ ሁሉ ምንም አያስደስተኝም።” 14  በዚህ ጊዜ ሚስቱ ዜሬሽና ጓደኞቹ በሙሉ እንዲህ አሉት፦ “ቁመቱ 50 ክንድ* የሆነ እንጨት አስተክል። ከዚያም ነገ ጠዋት በላዩ ላይ መርዶክዮስ እንዲሰቀል ለንጉሡ ንገረው።+ አንተም ከንጉሡ ጋር በግብዣው ላይ ተገኝተህ ሐሴት አድርግ።” ይህ ሐሳብ ሃማን አስደሰተው፤ እንጨቱንም አስተከለ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወደ 22.3 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።