አስቴር 7:1-10

  • አስቴር ሃማን አጋለጠችው (1-6ሀ)

  • ሃማ ራሱ ባዘጋጀው እንጨት ላይ ተሰቀለ (6ለ-10)

7  ንጉሡና ሃማም+ ንግሥት አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ።  በሁለተኛው ቀን በወይን ጠጅ ግብዣው ላይ ንጉሡ አስቴርን በድጋሚ እንዲህ አላት፦ “ንግሥት አስቴር ሆይ፣ የምትጠይቂው ምንድን ነው? የጠየቅሽው ይሰጥሻል። የምትፈልጊውስ ምንድን ነው? እስከ መንግሥቴ እኩሌታ እንኳ ብትጠይቂ ይሰጥሻል!”+  ንግሥት አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ንጉሥ ሆይ፣ በፊትህ ሞገስ ካገኘሁና ንጉሡን የሚያስደስተው ከሆነ ሕይወቴን* እንድትታደግልኝ እማጸንሃለሁ፤ ሕዝቤንም+ እንድታድንልኝ እጠይቅሃለሁ።  እኔና ሕዝቤ ለጥፋት፣ ለመገደልና ለመደምሰስ+ ተሸጠናልና።+ የተሸጥነው ወንዶችና ሴቶች ባሪያዎች እንድንሆን ብቻ ቢሆን ኖሮ ዝም ባልኩ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ጥፋት በንጉሡም ላይ ጉዳት ስለሚያስከትል በቸልታ መታለፍ የለበትም።”  ንጉሥ አሐሽዌሮስም ንግሥት አስቴርን “ለመሆኑ ይህ ሰው ማን ነው? እንዲህ ያለውን ነገር ለማድረግ የደፈረውስ ሰው የታለ?” አላት።  አስቴርም “ባላጋራና ጠላት የሆነው ሰው ይህ ክፉው ሃማ ነው” አለች። ሃማም በንጉሡና በንግሥቲቱ ፊት በፍርሃት ተንቀጠቀጠ።  ንጉሡም ከወይን ጠጅ ግብዣው ላይ ተቆጥቶ ተነሳ፤ ወደ ቤተ መንግሥቱም የአትክልት ስፍራ ሄደ፤ ይሁንና ሃማ ንጉሡ ሊቀጣው ቆርጦ እንደተነሳ ስለተገነዘበ ንግሥት አስቴር ሕይወቱን* እንድታድንለት ለመማጸን ቆመ።  ንጉሡ ከቤተ መንግሥቱ የአትክልት ስፍራ ወደ ወይን ጠጅ ግብዣው ተመልሶ ሲመጣ ሃማ አስቴር ባለችበት ድንክ አልጋ ላይ ተደፍቶ ተመለከተ። ንጉሡም “ብሎ ብሎ በገዛ ቤቴ ንግሥቲቱን ሊደፍራት ያስባል?” ብሎ ጮኸ። ይህ ቃል ከንጉሡ አፍ እንደወጣ የሃማን ፊት ሸፈኑት።  ከንጉሡ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣናት አንዱ የሆነው ሃርቦና+ እንዲህ አለ፦ “ሃማ፣ የንጉሡ ሕይወት እንዲተርፍ ሴራውን ላጋለጠው+ ለመርዶክዮስ የመሰቀያ እንጨትም አዘጋጅቷል።+ እንጨቱ 50 ክንድ* ቁመት ያለው ሲሆን በሃማ ቤት ቆሟል።” በዚህ ጊዜ ንጉሡ “በዚያው እንጨት ላይ ስቀሉት” አለ። 10  በመሆኑም ሃማን ለመርዶክዮስ ባዘጋጀው እንጨት ላይ ሰቀሉት፤ የንጉሡም ቁጣ በረደ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነፍሴን።”
ወይም “ነፍሱን።”
ወደ 22.3 ሜትር ገደማ ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።