አስቴር 9:1-32

  • አስቴር ንጉሡን ተማጸነች (1-19)

  • ንጉሡ ሌላ አዋጅ እንዲወጣ አደረገ (20-32)

9  አዳር* በተባለው በ12ኛው ወር፣ 13ኛ ቀን፣+ የንጉሡ ቃልና ሕግ በሚፈጸምበት+ እንዲሁም የአይሁዳውያን ጠላቶች በአይሁዳውያን ላይ ድል እንደሚቀዳጁ ተስፋ አድርገው በነበረበት ቀን ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆነ፤ አይሁዳውያኑ የሚጠሏቸውን ሰዎች ድል አደረጉ።+  አይሁዳውያኑ እነሱን ለመጉዳት በሚሹ ሰዎች ላይ እጃቸውን ለማንሳት በንጉሥ አሐሽዌሮስ+ አውራጃዎች በሙሉ በሚገኙ ከተሞቻቸው ውስጥ ተሰባሰቡ፤ ሕዝቡም ሁሉ ፈርቷቸው ስለነበር ሊቃወማቸው የቻለ አንድም ሰው አልነበረም።+  የአውራጃዎቹ መኳንንት በሙሉ፣ አስተዳዳሪዎቹ፣+ ገዢዎቹና የንጉሡን ጉዳይ የሚያስፈጽሙ ሰዎችም መርዶክዮስን ፈርተውት ስለነበር አይሁዳውያኑን ይረዷቸው ነበር።  መርዶክዮስ በንጉሡ ቤት* ውስጥ ገናና ሆኖ ነበር፤+ ገናናነቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ስለመጣ ዝናው በየአውራጃው ተዳረሰ።  አይሁዳውያኑ ጠላቶቻቸውን በሙሉ በሰይፍ ጨፈጨፏቸው፤ ገደሏቸው፤ እንዲሁም ደመሰሷቸው፤ በሚጠሏቸውም ሰዎች ላይ የፈለጉትን አደረጉባቸው።+  አይሁዳውያኑ በሹሻን* ግንብ*+ 500 ሰዎችን ገደሉ፤ ደግሞም አጠፉ።  በተጨማሪም ፓርሻንዳታ፣ ዳልፎን፣ አስፋታ፣  ፖራታ፣ አዳሊያ፣ አሪዳታ፣  ፓርማሽታ፣ አሪሳይ፣ አሪዳይ እና ዋይዛታ የተባሉትን፣ 10  የአይሁዳውያን ጠላት+ የነበረውን የሃመዳታን ልጅ የሃማን አሥር ወንዶች ልጆች ገደሉ። ከገደሏቸው በኋላ ግን አንድም ምርኮ አልወሰዱም።+ 11  በዚያ ቀን በሹሻን* ግንብ* የተገደሉት ሰዎች ብዛት ለንጉሡ ተነገረው። 12  ንጉሡ ንግሥት አስቴርን እንዲህ አላት፦ “አይሁዳውያኑ በሹሻን* ግንብ* 500 ሰዎችንና አሥሩን የሃማ ወንዶች ልጆች ገድለዋል፤ ደግሞም አጥፍተዋል። በቀሩት የንጉሡ አውራጃዎችስ+ ምን አድርገው ይሆን? አሁንስ የምትጠይቂው ምንድን ነው? የጠየቅሽው ይሰጥሻል። ሌላስ የምትፈልጊው ነገር አለ? ይደረግልሻል።” 13  አስቴርም እንዲህ ስትል መለሰች፦ “ንጉሡን ደስ የሚያሰኘው ከሆነ+ በሹሻን* የሚኖሩት አይሁዳውያን ዛሬ ተግባራዊ ያደረጉትን ሕግ+ ነገም እንዲደግሙት ይፈቀድላቸው፤ አሥሩ የሃማ ልጆችም በእንጨት ላይ ይሰቀሉ።”+ 14  ንጉሡም እንዲሁ እንዲደረግ አዘዘ። ከዚያም በሹሻን* ሕግ ወጣ፤ አሥሩ የሃማ ልጆችም ተሰቀሉ። 15  በሹሻን* የሚኖሩት አይሁዳውያን አዳር+ በተባለው ወር 14ኛ ቀን ላይ በድጋሚ ተሰበሰቡ፤ በሹሻንም* 300 ሰዎችን ገደሉ፤ ይሁንና አንድም ምርኮ አልወሰዱም። 16  በንጉሡ አውራጃዎች የሚኖሩት የቀሩት አይሁዳውያንም ተሰብስበው ሕይወታቸውን ከጥቃት ተከላከሉ።*+ እነሱን ይጠሏቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል 75,000 ሰዎችን በመግደል ጠላቶቻቸውን አጠፉ፤+ ይሁንና አንድም ምርኮ አልወሰዱም። 17  ይህ የሆነው አዳር በተባለው ወር 13ኛ ቀን ላይ ነበር፤ እነሱም በ14ኛው ቀን አረፉ፤ ዕለቱንም የግብዣና የሐሴት ቀን አደረጉት። 18  በሹሻን* የነበሩት አይሁዳውያን በ13ኛው ቀንና+ በ14ኛው ቀን+ ላይ ተሰበሰቡ፤ በ15ኛው ቀን ደግሞ አረፉ፤ ቀኑንም የግብዣና የሐሴት ቀን አደረጉት። 19  ከዋና ከተማዋ ውጭ በሚገኙ የገጠር ከተሞች የሚኖሩት አይሁዳውያን አዳር የተባለውን ወር 14ኛ ቀን የሐሴትና የግብዣ ቀን፣ የፈንጠዝያ ቀንና+ አንዳቸው ለሌላው ምግብ የሚልኩበት ጊዜ+ እንዲሆን ያደረጉት በዚህ የተነሳ ነው። 20  መርዶክዮስ+ እነዚህን ክንውኖች ከመዘገበ በኋላ በቅርብም ይሁን በሩቅ ስፍራ ላሉ፣ በመላው የንጉሥ አሐሽዌሮስ አውራጃዎች ለሚኖሩ አይሁዳውያን በሙሉ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ደብዳቤዎች ላከ። 21  በየዓመቱ የአዳርን ወር 14ኛና 15ኛ ቀን እንዲያከብሩ አዘዛቸው፤ 22  ምክንያቱም እነዚህ ቀናት አይሁዳውያኑ ከጠላቶቻቸው ያረፉባቸውና ሐዘናቸው ወደ ሐሴት፣ ለቅሷቸውም ወደ ፈንጠዝያ የተለወጠባቸው ቀናት ናቸው።+ እነዚህን ቀናት የግብዣና የደስታ እንዲሁም አንዳቸው ለሌላው ምግብ የሚልኩባቸውና ለድሆች ምጽዋት የሚሰጡባቸው ቀናት አድርገው እንዲያከብሩ ታዘው ነበር። 23  አይሁዳውያንም ማክበር የጀመሩትን ይህን በዓል ማክበራቸውን ለመቀጠልና መርዶክዮስ የጻፈላቸውን ነገር ለመፈጸም ተስማሙ። 24  የአይሁዳውያን ሁሉ ጠላት የነበረው የአጋጋዊው+ የሃመዳታ ልጅ ሃማ+ አይሁዳውያንን ለማጥፋት ሴራ ሸርቦ ነበርና፤+ እንዲሁም እነሱን ለማሸበርና ለመደምሰስ ፑር+ ወይም ዕጣ ጥሎ ነበር። 25  ሆኖም አስቴር ወደ ንጉሡ በገባች ጊዜ ንጉሡ “በአይሁዳውያን ላይ የሸረበው መጥፎ ሴራ+ በራሱ ላይ ይድረስበት” የሚል የጽሑፍ ትእዛዝ አስተላለፈ፤+ እነሱም እሱንና ልጆቹን በእንጨት ላይ ሰቀሏቸው።+ 26  በዚህም የተነሳ እነዚህን ቀናት ፑሪም አሏቸው፤ ይህ ስም የተወሰደው ፑር*+ ከተባለው ቃል ነው። በመሆኑም በዚህ ደብዳቤ ላይ ከሰፈረው ሐሳብ እንዲሁም ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ካዩአቸውና ካጋጠሟቸው ነገሮች የተነሳ 27  አይሁዳውያኑ ራሳቸውም ሆኑ ዘሮቻቸው እንዲሁም ከእነሱ ጋር የተባበሩ ሁሉ+ በየዓመቱ እነዚህን ሁለት ቀናት በተወሰነላቸው ጊዜ ላይ ለማክበርና እነዚህን ቀናት አስመልክቶ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ለመፈጸም ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ። 28  እያንዳንዱ ትውልድ፣ እያንዳንዱ ቤተሰብ፣ እያንዳንዱ አውራጃና እያንዳንዱ ከተማ እነዚህን ቀናት ማሰብና ማክበር ይጠበቅበት ነበር፤ እነዚህን የፑሪም ቀናት አይሁዳውያኑ ማክበራቸውን መተው የለባቸውም፤ መታሰቢያቸውም ከዘሮቻቸው መካከል መጥፋት የለበትም። 29  ከዚያም የአቢሃይል ልጅ ንግሥት አስቴርና አይሁዳዊው መርዶክዮስ ፑሪምን በተመለከተ የተጻፈውን ሁለተኛ ደብዳቤ በሙሉ ሥልጣናቸው አጸኑት። 30  እሱም የሰላምና የእውነት ቃል የያዙ ሕጋዊ እውቅና ያላቸው ደብዳቤዎችን በአሐሽዌሮስ+ ግዛት ውስጥ በሚገኙት 127 አውራጃዎች+ ለሚኖሩት አይሁዳውያን በሙሉ ላከ፤ 31  ይህም አይሁዳዊው መርዶክዮስና ንግሥት አስቴር ባዘዟቸው መሠረት+ እንዲሁም እነሱ ራሳቸው መጾምንና+ ምልጃ+ ማቅረብን ጨምሮ የሚጠበቅባቸውን ነገር ለመፈጸም ራሳቸውንና* ዘሮቻቸውን ግዴታ ውስጥ ባስገቡት መሠረት+ የፑሪምን ቀናት በተወሰነው ጊዜ እንዲያከብሩ ለማድረግ ነው። 32  አስቴር ያስተላለፈችውም ትእዛዝ ከፑሪም+ ጋር የተያያዙትን እነዚህን ነገሮች አጸና፤ ደግሞም መጽሐፍ ላይ ሰፈረ።

የግርጌ ማስታወሻ

ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ቤተ መንግሥት።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ቤተ መንግሥት፤ ምሽግ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “በሱሳም።”
ወይም “በሱሳ።”
ወይም “ለነፍሳቸው ቆሙ።”
ወይም “በሱሳ።”
“ፑር” የሚለው ቃል “ዕጣ” የሚል ትርጉም አለው። ብዙ ቁጥርን ለማመልከት የሚሠራበት “ፑሪም” የሚለው ቃል በቅዱሱ የቀን መቁጠሪያ በ12ኛው ወር የሚከበረው የአይሁዳውያን በዓል መጠሪያ ሆኗል። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ15ን ተመልከት።
ወይም “ነፍሳቸውንና።”