ኢሳይያስ 14:1-32

  • እስራኤላውያን በገዛ ምድራቸው ላይ ይሰፍራሉ (1, 2)

  • በባቢሎን ንጉሥ ላይ ትሳለቃለህ (3-23)

    • የሚያበራው ኮከብ ከሰማይ ወደቀ (12)

  • የይሖዋ እጅ አሦራዊውን ያደቃል (24-27)

  • በፍልስጤም ላይ የተላለፈ ፍርድ (28-32)

14  ይሖዋ ለያዕቆብ ምሕረት ያሳያልና፤+ እስራኤልንም እንደገና ይመርጠዋል።+ በምድራቸው ላይ ያሰፍራቸዋል፤*+ የባዕድ አገር ሰዎችም ከእነሱ ጋር ይሆናሉ፤ ከያዕቆብም ቤት ጋር ይጣበቃሉ።+  ሕዝቦችም ይወስዷቸዋል፤ ወደ ገዛ ስፍራቸውም ይመልሷቸዋል፤ የእስራኤልም ቤት በይሖዋ ምድር ላይ ወንድና ሴት አገልጋዮቻቸው ያደርጓቸዋል፤+ ማርከው የወሰዷቸውንም ይማርካሉ፤ አስገድደው ያሠሯቸው የነበሩትንም* ይገዟቸዋል።  ይሖዋ ከሥቃይህ፣ ከጭንቀትህና በላይህ ተጭኖ ከነበረው ከባድ የባርነት ቀንበር ባሳረፈህ ቀን፣+  በባቢሎን ንጉሥ ላይ እንዲህ ብለህ ትተርታለህ፦* “ሌሎችን አስገድዶ ሲያሠራ የነበረው* እንዴት አበቃለት! ጭቆናውስ እንዴት አከተመ!+   ይሖዋ የክፉዎችን ዘንግ፣የገዢዎችን በትር ሰብሯል፤+   ሕዝቦችን ያለማቋረጥ በቁጣ ሲመታ የነበረውን፣+ብሔራትን በማያባራ ስደት በቁጣ ሲገዛቸው የቆየውን ሰብሯል።+   መላዋ ምድር አርፋለች፤ ከረብሻም ነፃ ሆናለች። ሕዝቦች በደስታ እልል ብለዋል።+   የጥድ ዛፎችና አርዘ ሊባኖሶች እንኳ ሳይቀሩበአንተ ላይ በደረሰው ነገር ሐሴት ያደርጋሉ። ‘አንተ ከወደቅክ ጀምሮማንም ዛፍ ቆራጭ በእኛ ላይ አልተነሳም’ ይላሉ።   “ከታች ያለው መቃብር* እንኳወደዚያ በወረድክ ጊዜ አንተን ለመቀበል ሲል ተረበሸ። በሞት የተረቱትን፣ ጨቋኝ የምድር መሪዎች* ሁሉበአንተ የተነሳ ቀሰቀሳቸው። የብሔራትን ነገሥታት ሁሉ ከዙፋኖቻቸው ላይ አስነሳቸው። 10  ሁሉም እንዲህ በማለት ይናገራሉ፤ እንዲህም ይሉሃል፦‘አንተም እንደ እኛው ደከምክ ማለት ነው? አንተም እንደ እኛው ሆንክ? 11  ኩራትህና ባለ አውታር መሣሪያዎችህ የሚያሰሙት ድምፅወደ መቃብር* ወረዱ።+ እጮች ከበታችህ እንደ አልጋ ተነጥፈውልሃል፤የአልጋ ልብስህም ትሎች ናቸው።’ 12  አንተ የምታበራ ኮከብ፣ የንጋት ልጅ ሆይ፣እንዴት ከሰማይ ወደቅክ! አንተ ብሔራትን ድል ያደረግክ፣እንዴት ተቆርጠህ ወደ ምድር ወደቅክ!+ 13  በልብህ እንዲህ ብለህ ነበር፦ ‘ወደ ሰማያት እወጣለሁ።+ ዙፋኔን ከአምላክ ከዋክብት በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤+በስተ ሰሜን ርቆ በሚገኘውየመሰብሰቢያ ተራራም ላይ እቀመጣለሁ።+ 14  ከደመናዎች ከፍታ በላይ እወጣለሁ፤ራሴንም እንደ ልዑል አምላክ አደርጋለሁ።’ 15  ከዚህ ይልቅ ወደ መቃብር፣*ወደ ጥልቁም ጉድጓድ ትወርዳለህ። 16  የሚያዩህ አተኩረው ይመለከቱሃል፤በሚገባም ይመረምሩሃል፤ እንዲህም ይላሉ፦‘ምድርን ሲያንቀጠቅጥ፣መንግሥታትንም ሲያናውጥ የነበረው ይህ ሰው አይደለም?+ 17  ሰው የሚኖርበትን ምድር፣ ምድረ በዳ ያደረገው፣ከተሞቹንም የገለበጠው፣+እስረኞቹንም ወደ ቤታቸው እንዳይመለሱ የከለከለው እሱ አይደለም?’+ 18  ሌሎቹ የብሔራት ነገሥታት ሁሉ፣አንዳቸውም እንኳ ሳይቀሩ በክብር አንቀላፍተዋል፤እያንዳንዳቸው በየመቃብራቸው* አርፈዋል። 19  አንተ ግን እንደተጠላ ቀንበጥ*መቀበሪያ ሳታገኝ ተጥለሃል፤በሰይፍ ተወግተውወደ ዓለታማ ጉድጓድ በወረዱ አስከሬኖች ተሸፍነሃል፤እንደተረገጠም ሬሳ ሆነሃል። 20  ከእነሱ ጋር አብረህ በመቃብር አትቀበርም፤የገዛ ምድርህን አጥፍተሃልና፤የገዛ ሕዝብህንም ፈጅተሃል። የክፉ አድራጊዎች ዘር ስም ዳግመኛ አይጠራም። 21  ተነስተው ምድሪቱን እንዳይወርሱናምድሪቱን በከተሞች እንዳይሞሏትበአባቶቻቸው በደል የተነሳልጆቹ የሚታረዱበትን ስፍራ አዘጋጁ።” 22  “በእነሱ ላይ እነሳለሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። “ከባቢሎን ስምን፣ ቀሪዎችን፣ ልጆችንና ዘርማንዘርን አጠፋለሁ”+ ይላል ይሖዋ። 23  “የጃርት መኖሪያና ረግረጋማ ቦታ አደርጋታለሁ፤ በጥፋት መጥረጊያም እጠርጋታለሁ”+ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ። 24  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ሲል ምሏል፦ “ልክ እንዳሰብኩት ይሆናል፤በወሰንኩትም መሠረት ይፈጸማል። 25  አሦራዊውን በምድሬ ላይ አደቀዋለሁ፤በተራሮቼም ላይ እረግጠዋለሁ።+ ቀንበሩ ከላያቸው ላይ ይነሳል፤ሸክሙም ከትከሻቸው ላይ ይወርዳል።”+ 26  በመላው ምድር ላይ የተላለፈው ውሳኔ* ይህ ነው፤በብሔራትም ሁሉ ላይ የተዘረጋው* እጅ ይህ ነው። 27  የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ወስኗልና፤ውሳኔውን ማን ሊያጨናግፍ ይችላል?+ እጁ ተዘርግቷል፤ማንስ ሊያጥፈው ይችላል?+ 28  ንጉሥ አካዝ በሞተበት+ ዓመት የሚከተለው ፍርድ ተላለፈ፦ 29  “ፍልስጤማውያን ሆይ፣ የመቺያችሁ በትር ስለተሰበረአንዳችሁም ብትሆኑ ደስ አይበላችሁ። ከእባቡ ሥር+ መርዘኛ እባብ ይወጣልና፤+ዘሩም የሚበርና የሚያቃጥል እባብ* ይሆናል። 30  የችግረኞቹ የበኩር ልጆች ሲመገቡ፣ድሆቹም ያለስጋት ሲተኙ፣የአንተን ሥር ግን በረሃብ እገድላለሁ፤ከአንተ የሚተርፈውም ይገደላል።+ 31  አንተ በር ሆይ፣ አላዝን! አንቺ ከተማ ሆይ፣ ጩኺ! ፍልስጤማውያን ሆይ፣ ሁላችሁም ተስፋ ትቆርጣላችሁ! ከሰሜን ጭስ እየመጣ ነውና፤አንዳቸውም ቢሆኑ ከሰልፉ ተነጥለው ወደ ኋላ አይቀሩም።” 32  ለብሔሩ መልእክተኞች ምን ብለው መመለስ ይገባቸዋል? ‘የጽዮንን መሠረት የጣለው ይሖዋ ነው፤+በሕዝቡም መካከል ያሉት ችግረኛ ሰዎች እሷን መጠጊያ ያደርጋሉ’ ብለው ይመልሱላቸዋል።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “እረፍት ይሰጣቸዋል።”
ወይም “ተቆጣጣሪዎቻቸውንም።”
ወይም “ትሳለቃለህ።”
ወይም “ተቆጣጣሪው።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “አውራ ፍየሎች።”
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ቃል በቃል “በየቤታቸው።”
ወይም “ቅርንጫፍ።”
ቃል በቃል “በምድር ላይ የተመከረው ምክር።”
ወይም “ብሔራትንም ሁሉ ለመምታት የተዘጋጀው።”
ወይም “ተወርዋሪ መርዘኛ እባብ።”