ኢሳይያስ 16:1-14

  • ለሞዓብ የተነገረው የፍርድ መልእክት ቀጣይ ክፍል (1-14)

16  ከሴላ በምድረ በዳው በኩል አድርጋችሁበጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ለሚገኘውለምድሪቱ ገዢ አውራ በግ ላኩ።   የሞዓብ ሴቶች ልጆች በአርኖን+ መልካ*ከጎጆው እንደተባረረ ወፍ ይሆናሉ።+   “ምክር ለግሱ፤ ውሳኔውን ተግባራዊ አድርጉ። እኩለ ቀን ላይ እንደ ምሽት ጨለማ ያለ ጥላ አጥሉ። የተበተኑትን ሸሽጉ፤ የሚሸሹትንም አሳልፋችሁ አትስጡ።   ሞዓብ ሆይ፣ የተበተኑት ሕዝቦቼ በአንተ ውስጥ ይኑሩ። ከአጥፊው+ የተነሳ መሸሸጊያ ቦታ ሁንላቸው። ጨቋኙ ፍጻሜው ይመጣል፤ጥፋቱም ያበቃል፤ሌሎችን የሚረግጡትም ከምድር ገጽ ይጠፋሉ።   ከዚያም ዙፋን በታማኝ ፍቅር ጸንቶ ይመሠረታል። በዳዊት ድንኳን ላይ በዙፋኑ የሚቀመጠው ታማኝ ይሆናል፤+በትክክል ይፈርዳል፤ ጽድቅንም በቶሎ ያስፈጽማል።”+   ስለ ሞዓብ ኩራት ይኸውም በጣም ኩሩ እንደሆነ ሰምተናል፤+ስለ ትዕቢቱ፣ ስለ ኩራቱና ስለ ታላቅ ቁጣው ሰምተናል፤+ይሁንና ድንፋታው ሁሉ ከንቱ ይሆናል።   በመሆኑም ሞዓብ፣ ስለ ሞዓብ ዋይ ዋይ ይላል፤አዎ፣ ሁሉም ዋይ ዋይ ይላሉ።+ የተመቱት ሰዎች ስለ ቂርሃረሰት+ የዘቢብ ቂጣ ያለቅሳሉ።   በሃሽቦን+ እርከኖች ላይ የሚገኙት ተክሎች ጠውልገዋልና፤የሲብማ+ የወይን ተክሎች ረግፈዋል፤የብሔራት ገዢዎች ቀያይ ቅርንጫፎቹን* ረጋግጠዋል፤እስከ ያዜር+ ደርሰዋል፤በምድረ በዳውም ተንሰራፍተዋል። ቀንበጦቹም ተዘርግተው እስከ ባሕሩ ድረስ ዘልቀዋል።   ስለዚህ ስለ ያዜር እንዳለቀስኩት ለሲብማ የወይን ተክልም አለቅሳለሁ። ሃሽቦንና ኤልዓሌ+ ሆይ፣ በእንባዬ አርሳችኋለሁ፤ምክንያቱም የበጋ ፍሬና መከር በምትሰበስቡበት ወቅት የሚሰማው ጩኸት አብቅቷል።* 10  ሐሴትና ደስታ ከፍራፍሬ እርሻው ተወስዷል፤በወይን እርሻዎቹም የደስታ ዝማሬ ወይም ጩኸት አይሰማም።+ ወይን የሚረግጥ ሰው ከእንግዲህ በወይን መጭመቂያው ውስጥ ወይን አይረግጥም፤ጩኸቱን ሁሉ ጸጥ አሰኝቻለሁና።+ 11  ከዚህም የተነሳ እንደሚርገበገብ የበገና ክርውስጤ ስለ ሞዓብ፣አንጀቴም ስለ ቂርሃረሰት ይታወካል።+ 12  ሞዓብ በከፍታ ስፍራው ላይ ራሱን ቢያደክምም እንኳ ዋጋ የለውም፤ ለመጸለይ ወደ መቅደሱ ቢመጣም ምንም ማድረግ አይችልም።+ 13  ይሖዋ አስቀድሞ ስለ ሞዓብ የተናገረው ቃል ይህ ነው። 14  ደግሞም ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ልክ እንደ ቅጥር ሠራተኛ የሥራ ዘመን፣* በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ የሞዓብ ክብር በብዙ ብጥብጥ ይዋረዳል፤ የሚተርፉትም በጣም ጥቂትና እዚህ ግቡ የማይባሉ ይሆናሉ።”+

የግርጌ ማስታወሻ

ወንዝ ማቋረጥ የሚቻልበት ጥልቀት የሌለው የወንዝ ክፍል።
ወይም “ቀይ የወይን ዘለላዎች የያዙ ቅርንጫፎቹን።”
“ምክንያቱም የበጋ ፍሬና መከር በምትሰበስቡበት ጊዜ የጦርነት ሁካታ መጥቷል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “አንድ ቅጥር ሠራተኛ እንደሚያደርገው በጥንቃቄ ተቆጥሮ።” ይህም ልክ በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማለት ነው።