ኢሳይያስ 21:1-17

  • በምድረ በዳው ባሕር ላይ የተላለፈ ፍርድ (1-10)

    • “በመጠበቂያው ግንብ ላይ ቆሜአለሁ” (8)

    • “ባቢሎን ወደቀች!” (9)

  • በዱማና በበረሃማው ሜዳ ላይ የተላለፈ ፍርድ (11-17)

    • “ጠባቂ ሆይ፣ ስለ ሌሊቱ ምን ትላለህ?” (11)

21  በምድረ በዳው ባሕር* ላይ የተላለፈ ፍርድ፦+ ከደቡብ አቅጣጫ አውሎ ነፋሳት እየጠራረጉ እንደሚመጡ፣ከምድረ በዳ ይኸውም አስፈሪ ከሆነው ምድር የሆነ ነገር እየመጣ ነው።+   አንድ የሚያስጨንቅ ራእይ ተነገረኝ፦ ከሃዲው ክህደት ይፈጽማል፤አጥፊውም ያጠፋል። ኤላም ሆይ፣ ተነሺ! ሜዶን ሆይ፣ ክበቢ!+ እሷ ያስከተለችው ሲቃ ሁሉ እንዲያከትም አደርጋለሁ።+   ከዚህም የተነሳ በጣም ተሠቃየሁ።*+ ልትወልድ እንደተቃረበች ሴት፣ምጥ ያዘኝ። እጅግ ከመጨነቄ የተነሳ መስማት ተሳነኝ፤እጅግ ከመረበሼም የተነሳ ማየት አቃተኝ።   ልቤ ደከመ፤ በፍርሃት ተንቀጠቀጥኩ። የምናፍቀው የምሽት ድንግዝግዝታ ሽብር ለቀቀብኝ።   ማዕዱን አሰናዱ፤ መቀመጫ ቦታዎቹን አዘጋጁ! ብሉ፣ ጠጡ!+ እናንተ መኳንንት፣ ተነሱ፤ ጋሻውን ዘይት ቀቡ!   ይሖዋ እንዲህ ብሎኛልና፦ “ሂድ፣ ጠባቂ አቁም፤ የሚያየውንም ነገር እንዲናገር አድርግ።”   እሱም በፈረሶች የሚጎተቱ የጦር ሠረገሎች፣በአህዮች የሚጎተቱ የጦር ሠረገሎች፣በግመሎች የሚጎተቱ የጦር ሠረገሎች አየ። ዓይኑን ተክሎ በከፍተኛ ትኩረት ተመለከተ።   ከዚያም እንደ አንበሳ ጮኾ እንዲህ አለ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ በየቀኑ በመጠበቂያው ግንብ ላይ ቆሜአለሁ፤በየሌሊቱም በጥበቃ ቦታዬ ላይ ተሰይሜአለሁ።+   እየመጣ ያለውን ነገር ተመልከት፦ ሰዎች በፈረሶች በሚጎተት የጦር ሠረገላ እየመጡ ነው!”+ ከዚያም ጮክ ብሎ እንዲህ አለ፦ “ወደቀች! ባቢሎን ወደቀች!+ የተቀረጹትን የአማልክቷን ምስሎች በሙሉ መሬት ላይ ጥሎ ሰባበረ!”+ 10  እንደ እህል የተወቃኸው ሕዝቤ፣የአውድማዬ ውጤት* ሆይ፣+ከእስራኤል አምላክ፣ ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ የሰማሁትን ነግሬሃለሁ። 11  በዱማ* ላይ የተላለፈ ፍርድ፦ አንዱ ከሴይር ጠርቶኝ እንዲህ አለኝ፦+ “ጠባቂ ሆይ፣ ስለ ሌሊቱ ምን ትላለህ? ጠባቂ ሆይ፣ ስለ ሌሊቱ ምን ትላለህ?” 12  ጠባቂውም እንዲህ አለ፦ “ሊነጋ ነው፤ ሆኖም ተመልሶ ይመሻል። መጠየቅ ከፈለጋችሁ ጠይቁ። ተመልሳችሁ ኑ!” 13  በበረሃማው ሜዳ ላይ የተላለፈ ፍርድ፦ እናንተ የዴዳን+ ተጓዥ ነጋዴዎች ሆይ፣በበረሃማው ሜዳ በሚገኘው ዱር ሌሊቱን ታሳልፋላችሁ። 14  የተጠማውን ለመገናኘት ውኃ ይዛችሁ ኑ፤እናንተ የቴማ+ ነዋሪዎች ሆይ፣ለሚሸሸውም ሰው ምግብ አምጡ። 15  እነሱ ከሰይፍ፣ ከተመዘዘ ሰይፍ፣ከተደገነ ቀስትና ከተፋፋመ ጦርነት ሸሽተዋልና። 16  ይሖዋ እንዲህ ብሎኛል፦ “እንደ ቅጥር ሠራተኛ የሥራ ዘመን፣* በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የቄዳር+ ክብር ሙሉ በሙሉ ይጠፋል። 17  ከቄዳር ተዋጊዎች የሚተርፉት ቀስተኞች ጥቂት ይሆናሉ፤ የእስራኤል አምላክ ይሖዋ ይህን ተናግሯልና።”

የግርጌ ማስታወሻ

የጥንቷን ባቢሎን ደቡባዊ ክፍል የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ዳሌዎቼ በሥቃይ ተሞሉ።”
ቃል በቃል “ወንድ ልጅ።”
“ዝምታ” የሚል ትርጉም አለው።
ወይም “አንድ ቅጥር ሠራተኛ እንደሚያደርገው በጥንቃቄ ተቆጥሮ።” ይህም ልክ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ማለት ነው።