ኢሳይያስ 22:1-25
22 ስለ ራእይ ሸለቆ* የተነገረ የፍርድ መልእክት፦+
ሁላችሁም ጣሪያ ላይ የወጣችሁት ምን ሆናችሁ ነው?
2 አንቺ ሁከት የነገሠብሽ መዲና፣ የፈንጠዝያም ከተማ፣በትርምስ ተሞልተሻል።
ነዋሪዎችሽ ያለቁት በሰይፍወይም በጦርነት ተገድለው አይደለም።+
3 አምባገነን መሪዎችሽ ሁሉ በአንድ ላይ ሸሽተዋል።+
ሆኖም ቀስት መጠቀም ሳያስፈልግ ተማርከዋል።
ወደ ሩቅ ቦታ ሸሽተው ቢሄዱምየተገኙት ሁሉ ተማርከዋል።+
4 ስለዚህ እንዲህ አልኩ፦ “ዓይናችሁን ከእኔ ላይ አንሱ፤እኔም አምርሬ አለቅሳለሁ።+
የሕዝቤ ሴት ልጅ* ከደረሰባት ጥፋት የተነሳእኔን ለማጽናናት አትድከሙ።+
5 ከሉዓላዊው ጌታ፣ ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ ዘንድበራእይ ሸለቆግራ የመጋባት፣ የሽንፈትና የመደናገጥ ቀን ሆኗልና።+
ቅጥሩ ይፈርሳል፤+ወደ ተራራውም ይጮኻሉ።*
6 ኤላም+ ሰዎችን ባሳፈሩ ሠረገሎችና በፈረሶች* ላይየፍላጻ ኮሮጆዋን ይዛለች፤ቂርም+ የጋሻውን ልባስ አወለቀች።*
7 ምርጥ የሆኑት ሸለቆዎችሽ*በጦር ሠረገሎች ይሞላሉ፤ፈረሶቹም* የከተማዋ በር ላይ ይቆማሉ፤
8 የይሁዳም መከለያ*+ ይወገዳል።
“አንተም በዚያ ቀን የደኑን የጦር መሣሪያ ግምጃ ቤት ትመለከታለህ፤
9 እናንተም በዳዊት ከተማ ቅጥር ላይ ያሉትን በርካታ ክፍተቶች ትመለከታላችሁ።+ በታችኛውም ኩሬ ውኃ ታጠራቅማላችሁ።+
10 የኢየሩሳሌምን ቤቶች ትቆጥራላችሁ፤ ቅጥሩንም ለማጠናከር ቤቶቹን ታፈርሳላችሁ።
11 በሁለቱ ቅጥሮች መካከል በድሮው ኩሬ ላለው ውኃ የሚሆን ማጠራቀሚያ ትሠራላችሁ፤ ይሁንና ይህን ወዳደረገው ታላቅ አምላክ አትመለከቱም፤ ከዘመናት በፊት ወደሠራውም አምላክ አታዩም።
12 በዚያም ቀን ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋእንድታለቅሱና እንድታዝኑ፣+ፀጉራችሁን እንድትላጩና ማቅ እንድትለብሱ ይጠራችኋል።
13 ይሁን እንጂ ድግስና ፈንጠዝያ፣ፍሪዳ መጣልና ሙክት ማረድ፣ሥጋ መብላትና የወይን ጠጅ መጠጣት ሆኗል።+
‘ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ’ ትላላችሁ።”+
14 ከዚያም የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በጆሮዬ ይህን ገለጠልኝ፦ “‘እናንተ እስክትሞቱ ድረስ ይህ በደል አይሰረይላችሁም’+ ይላል ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።”
15 ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “በቤቱ* ላይ ወደተሾመው ወደ መጋቢው ወደ ሸብና+ ሄደህ እንዲህ በለው፦
16 ‘በዚህ ለራስህ የመቃብር ቦታ የወቀርከው፣ የአንተ የሆነ ምን ነገር ቢኖርህ ነው? በዚህስ የአንተ የሆነ ማን አለ? በከፍታ ቦታ የራሱን መቃብር ወቅሯል፤ ቋጥኝ ጠርቦ ለራሱ ማረፊያ ስፍራ* አዘጋጅቷል።
17 ‘አንተ ሰው፣ እነሆ፣ ይሖዋ በኃይል አሽቀንጥሮ ይጥልሃል፤ ጨምድዶም ይይዝሃል።
18 ጠቅልሎና አጡዞ እንደ ኳስ ወደ ሰፊ ምድር ይወረውርሃል። በዚያ ትሞታለህ፤ ያማሩ ሠረገሎችህም በዚያ ለጌታህ ቤት ውርደት ይሆናሉ።
19 እኔም ከሹመትህ እሽርሃለሁ፤ ከኃላፊነትህም አባርርሃለሁ።
20 “‘በዚያም ቀን አገልጋዬን የኬልቅያስን ልጅ ኤልያቄምን+ እጠራለሁ፤
21 ቀሚስህን አለብሰዋለሁ፤ መታጠቂያህንም በደንብ አስታጥቀዋለሁ፤+ ሥልጣንህንም* በእጁ አሳልፌ እሰጠዋለሁ። እሱም ለኢየሩሳሌም ነዋሪዎችና ለይሁዳ ቤት አባት ይሆናል።
22 የዳዊትንም ቤት ቁልፍ+ በትከሻው ላይ አደርጋለሁ። እሱ የሚከፍተውን ማንም አይዘጋም፤ እሱ የሚዘጋውንም ማንም አይከፍትም።
23 በአስተማማኝ ቦታ ላይ እንደ ማንጠልጠያ እተክለዋለሁ፤ ለአባቱም ቤት እንደ ክብር ዙፋን ይሆናል።
24 በእሱም ላይ የአባቱን ቤት ክብር* በሙሉ፣ ልጆቹንና ዘሮቹን* ይኸውም ትናንሾቹን ዕቃዎች በሙሉ፣ ጎድጓዳ ሳህኖቹንና ትላልቆቹን እንስራዎች ሁሉ ይሰቅሉበታል።
25 “‘በዚያም ቀን’ ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ፣ ‘በአስተማማኝ ቦታ ላይ የተተከለው ማንጠልጠያ ይነቀላል፤+ ተቆርጦም ይወድቃል፤ በላዩ ላይ የተንጠለጠለው ሸክምም ወድቆ ይከሰከሳል፤ ይሖዋ ራሱ ተናግሯልና።’”
የግርጌ ማስታወሻ
^ ኢየሩሳሌምን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
^ በሰውኛ ዘይቤ የተገለጸ ቅኔያዊ አነጋገር፤ አዘኔታን ወይም ርኅራኄን የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
^ እርዳታ ለማግኘት ወይም በጦርነት ወቅት የሚሰማን ጩኸት ሊያመለክት ይችላል።
^ ወይም “በፈረሰኞች።”
^ ወይም “ጋሻውን አዘጋጀች።”
^ ወይም “ረባዳማ ሜዳዎችሽ።”
^ ወይም “ፈረሰኞቹም።”
^ ወይም “መከላከያ።”
^ ወይም “በቤተ መንግሥቱ።”
^ ቃል በቃል “መኖሪያ።”
^ ወይም “ግዛትህንም።”
^ ቃል በቃል “ክብደት።”
^ ወይም “ቅርንጫፎቹን።”