ኢሳይያስ 23:1-18
-
ስለ ጢሮስ የተነገረ የፍርድ መልእክት (1-18)
23 ስለ ጢሮስ የተነገረ የፍርድ መልእክት፦+
እናንተ የተርሴስ መርከቦች+ ዋይ ዋይ በሉ!
ወደቧ ወድሟልና፤ ወደ እሷ መግባት አይቻልም።
ከኪቲም+ አገር ወሬው ደርሷቸዋል።
2 እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ ሰዎች፣ ጸጥ በሉ።
ባሕሩን አቋርጠው የሚመጡት የሲዶና+ ነጋዴዎች ሀብት በሀብት አድርገዋችኋል።
3 የገቢ ምንጮቿ የሆኑት የሺሆር*+ እህልና*የአባይ መከር በብዙ ውኃዎች ላይ ተጓጉዘውየብሔራትን ትርፍ ያመጡላት ነበር።+
4 አንቺ የባሕር ምሽግ ሲዶና ሆይ፣ እፈሪ፤ምክንያቱም ባሕሩ እንዲህ ብሏል፦
“አላማጥኩም፤ አልወለድኩምም፤ወጣት ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን* አላሳደግኩም።”+
5 ስለ ግብፅ በተነገረው ወሬ እንደሆነው ሁሉ+ስለ ጢሮስም በሚነገረው ወሬ ሰዎች ጭንቅ ይይዛቸዋል።+
6 ባሕሩን አቋርጣችሁ ወደ ተርሴስ ተሻገሩ!
እናንተ በባሕር ዳርቻ የምትኖሩ ሰዎች ዋይ ዋይ በሉ!
7 ከጥንት ዘመን፣ ከድሮ ጀምሮ ሐሴት ታደርግ የነበረችው ከተማችሁ ይህች ናት?
በዚያ ትኖር ዘንድ እግሮቿ ወደ ሩቅ ቦታዎች ይወስዷት ነበር።
8 ዘውድ በምታጎናጽፈው፣እንዲሁም መኳንንት የሆኑ ነጋዴዎች፣በመላውም ምድር ላይ የተከበሩ ሻጮችና ለዋጮች በነበሯትበጢሮስ ላይ ይህን ውሳኔ ያስተላለፈው ማን ነው?+
9 በውበቷ ሁሉ የተነሳ የሚሰማትን ኩራት ለማርከስእንዲሁም በመላው ምድር ላይ የተከበሩትን ሁሉ ለማዋረድይህን ውሳኔ ያስተላለፈው የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ራሱ ነው።+
10 የተርሴስ ሴት ልጅ ሆይ፣ እንደ አባይ ወንዝ ምድርሽን አጥለቅልቂ።
ከእንግዲህ ወዲያ መርከብ የሚሠራበት ቦታ* አይኖርም።+
11 አምላክ እጁን በባሕሩ ላይ ዘርግቷል፤መንግሥታትን አንቀጥቅጧል።
ይሖዋ የፊንቄ ምሽጎች እንዲወድሙ ትእዛዝ አስተላልፏል።+
12 እሱም እንዲህ ይላል፦ “አንቺ የተጨቆንሽ የሲዶና ድንግል ሆይ፣ዳግመኛ ሐሴት አታደርጊም።+
ተነሽ፣ ወደ ኪቲም+ ተሻገሪ።
እዚያም ቢሆን እረፍት አታገኚም።”
13 የከለዳውያንን+ ምድር ተመልከቱ!
በበረሃ የሚኖሩ እንስሳት መፈንጫ ያደረጓትአሦራውያን+ ሳይሆኑ እነዚህ ሰዎች ናቸው።
ጥቃት ለመሰንዘር የሚያስችል ማማ አቁመዋል፤የማይደፈሩ ማማዎቿን በማፈራረስ+የፍርስራሽ ክምር አድርገዋታል።
14 እናንተ የተርሴስ መርከቦች፣ምሽጋችሁ ስለወደመ ዋይ ዋይ በሉ።+
15 በዚያም ቀን ጢሮስ እንደ አንድ ንጉሥ ዕድሜ* ለ70 ዓመት የተረሳች ትሆናለች።+ በ70ኛው ዓመት ማብቂያ ላይ ጢሮስ እንዲህ ተብሎ እንደሚዘመርላት ዝሙት አዳሪ ትሆናለች፦
16 “አንቺ የተረሳሽ ዝሙት አዳሪ፣ በገና ይዘሽ በከተማው ውስጥ ተዘዋወሪ።
በገናሽንም ጥሩ አድርገሽ ተጫወቺ፤እነሱም እንዲያስታውሱሽብዙ ዘፈን ዝፈኚ።”
17 በሰባው ዓመት መጨረሻ ላይ ይሖዋ ትኩረቱን በጢሮስ ላይ ያደርጋል፤ እሷም ዳግመኛ ክፍያ መቀበሏን ትቀጥላለች፤ በመላው ምድር ላይ ካሉ የዓለም መንግሥታትም ጋር ታመነዝራለች።
18 ሆኖም ትርፏና የምትቀበለው ክፍያ ለይሖዋ የተቀደሰ ይሆናል። አይከማችም ወይም አይጠራቀምም፤ ምክንያቱም በይሖዋ ፊት የሚኖሩ ሰዎች እስኪጠግቡ ድረስ እንዲበሉና የሚያምር ልብስ እንዲለብሱ እሷ የምትቀበለው ክፍያ ለእነሱ ይሰጣል።+