ኢሳይያስ 24:1-23

  • ይሖዋ አገሪቱን ወና ያደርጋታል (1-23)

    • ይሖዋ በጽዮን ነግሦአል (23)

24  እነሆ፣ ይሖዋ ምድሪቱን ወና እና ባድማ ያደርጋታል።+ ይገለብጣታል፤*+ ነዋሪዎቿንም ይበትናቸዋል።+   በሁሉም ላይ ተመሳሳይ ነገር ይደርሳል፦ በሕዝቡ ላይ የሚሆነው በካህኑ፣በአገልጋዩ ላይ የሚሆነው በጌታው፣በአገልጋይዋ ላይ የሚሆነው በእመቤቷ፣በገዢው ላይ የሚሆነው በሻጩ፣በአበዳሪው ላይ የሚሆነው በተበዳሪው፣በወለድ ተቀባዩ ላይ የሚሆነው በወለድ ከፋዩ ላይ ይደርሳል።+   ምድሪቱ ሙሉ በሙሉ ወና ትሆናለች፤ፈጽሞ ትበዘበዛለች፤+ይሖዋ ይህን ቃል ተናግሯልና።   ምድሪቱ ታዝናለች፤*+ ትከስማለች። ፍሬያማዋ ምድር ትራቆታለች፤ ትጠፋለች። የምድሪቱ ታላላቅ ሰዎች ይዝላሉ።   ሕጎቹን ስለተላለፉ፣+ሥርዓቱን ስለለወጡና+ዘላቂውን* ቃል ኪዳን ስላፈረሱ+ምድሪቱ በገዛ ነዋሪዎቿ ተበክላለች።+   ስለዚህ እርግማኑ ምድሪቱን በላት፤+በላይዋም የሚኖሩ ሰዎች በደለኞች ሆነው ተገኝተዋል። የምድሪቱ ነዋሪዎች ቁጥር የመነመነው በዚህ ምክንያት ነው፤የቀሩት ሰዎችም በጣም ጥቂት ናቸው።+   አዲሱ የወይን ጠጅ ያለቅሳል፤* የወይን ተክሉም ይጠወልጋል፤+በልባቸውም ሐሴት አድርገው የነበሩ ሁሉ ያዝናሉ።+   አስደሳች የሆነው የአታሞ ድምፅ መሰማት አቁሟል፤ይፈነጥዙ የነበሩት ሰዎች ድምፅ ጠፍቷል፤ደስ የሚያሰኘው የበገና ድምፅ መሰማቱ ቀርቷል።+   ዘፈን በሌለበት የወይን ጠጅ ይጠጣሉ፤መጠጡም ለሚጠጡት ሰዎች መራራ ይሆናል። 10  የተተወችው ከተማ ፈራርሳለች፤+እያንዳንዱ ቤት ማንም እንዳይገባበት ተዘግቷል። 11  በየጎዳናው ላይ የወይን ጠጅ ፍለጋ ይጮኻሉ። ሐሴት ጨርሶ ጠፍቷል፤ምድሪቱም ደስታ ርቋታል።+ 12  ከተማዋ ፈራርሳለች፤በሩም ተሰባብሮ የፍርስራሽ ክምር ሆኗል።+ 13  የወይራ ዛፍ ሲራገፍ+ እንደሚቀር ፍሬ፣ ወይንም ተሰብስቦ ካበቃ በኋላ እንደሚቀር ቃርሚያ፣+ሕዝቤም በምድሪቱና በሌሎች ሕዝቦች መካከል እንዲሁ ይሆናል። 14  ድምፃቸውን ከፍ ያደርጋሉ፤በደስታ እልል ይላሉ። ከባሕሩ* የይሖዋን ግርማ ያውጃሉ።+ 15  ከዚህም የተነሳ በብርሃን ምድር*+ ለይሖዋ ክብር ይሰጣሉ፤በባሕር ደሴቶችም የእስራኤልን አምላክ የይሖዋን ስም ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።+ 16  ከምድር ዳርቻ “ለጻድቁ ክብር* ይሁን!”+ የሚል ዝማሬ እንሰማለን። እኔ ግን እንዲህ አልኩ፦ “አቅም አጣሁ፤ አቅም አጣሁ! ወዮልኝ! ከሃዲዎች ክህደት ፈጽመዋል፤ከሃዲዎች በማታለል ክህደት ፈጽመዋል።”+ 17  አንተ የምድሪቱ ነዋሪ ሆይ፣ ሽብር፣ ጉድጓድና ወጥመድ ይጠብቅሃል።+ 18  ከሚያሸብረው ድምፅ የሚሸሽ ሁሉ ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃል፤ከጉድጓዱም የሚወጣ ሁሉ በወጥመዱ ይያዛል።+ የሰማይ የውኃ በሮች ይከፈታሉና፤የምድርም መሠረቶች ይናወጣሉ። 19  ምድሪቱ ተሰነጣጥቃለች፤ምድሪቱ ተንቀጥቅጣለች፤ምድሪቱ በኃይል ትናወጣለች።+ 20  ምድሪቱ እንደሰከረ ሰው ትንገዳገዳለች፤ነፋስ እንደሚወዘውዘው ጎጆም በነፋስ ወዲያና ወዲህ ትወዛወዛለች። በደሏም በላይዋ ላይ እጅግ ከብዷል፤+ዳግመኛም እንደማትነሳ ሆና ትወድቃለች። 21  በዚያን ቀን ይሖዋ በላይ፣ በከፍታ ቦታ ባለው ሠራዊት ላይ፣እንዲሁም በታች፣ በምድር ባሉት ነገሥታት ላይ ትኩረቱን ያደርጋል። 22  እነሱም እንደ እስረኞች ጉድጓድ ውስጥአንድ ላይ ይታጎራሉ፤በእስር ቤት ውስጥም ይዘጋባቸዋል፤ከብዙ ቀናት በኋላ ጉዳያቸው ይታያል። 23  ሙሉ ጨረቃ ትዋረዳለች፤የምታበራው ፀሐይም ታፍራለች፤+የሠራዊት ጌታ ይሖዋ በጽዮን ተራራና+ በኢየሩሳሌም ነግሦአልና፤+በሕዝቡ ሽማግሌዎች ፊት* ክብር ተጎናጽፏል።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ፊቷን ያዞራል።”
“ትደርቃለች” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የጥንቱን።”
“ይደርቃል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ከምዕራብ።”
ወይም “በምሥራቅ።”
ወይም “ጌጥ።”
ቃል በቃል “በእሱ ሽማግሌዎች ፊት።”