ኢሳይያስ 28:1-29

  • የኤፍሬም ሰካራሞች ወዮላቸው! (1-6)

  • የይሁዳ ካህናትና ነቢያት ይንገዳገዳሉ (7-13)

  • “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል” (14-22)

    • በጽዮን የተቀመጠ ክቡር የማዕዘን ድንጋይ (16)

    • ይሖዋ ያከናወነው እንግዳ የሆነ ተግባር (21)

  • የይሖዋን ተግሣጽ የሚያሳይ ምሳሌ (23-29)

28  ጎልታ ለምትታየው* ለኤፍሬም+ ሰካራሞች አክሊል* ወዮላት!ይህች የምታምር ጌጥ በወይን ጠጅ የተሸነፉ ሰዎች በሚኖሩበትለም ሸለቆ አናት ላይ የምትገኝ የምትጠወልግ አበባ ናት።   እነሆ፣ ይሖዋ ጠንካራና ብርቱ የሆነውን ይልካል። እሱም እንደ ነጎድጓዳማ የበረዶ ውሽንፍር፣ እንደ አጥፊ አውሎ ነፋስ፣ኃይለኛ ጎርፍ እንደሚያስከትል ነጎድጓዳማ ውሽንፍርበኃይል አሽቀንጥሮ ወደ ምድር ይጥላታል።   ጎልተው የሚታዩት* የኤፍሬም ሰካራሞች ያደረጓቸው አክሊሎችበእግር ይረገጣሉ።+   ለም በሆነው ሸለቆ አናት ላይ የምትገኘውናየምታምር ጌጥ የሆነችው የምትጠወልግ አበባከበጋ በፊት፣ በመጀመሪያው ወቅት እንደምትበስል በለስ ትሆናለች። ሰውም ባያት ጊዜ ቀጥፎ ወዲያውኑ ይውጣታል።  በዚያ ቀን የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ከሕዝቡ መካከል ለተረፉት ሰዎች የሚያምር አክሊልና ውብ የአበባ ጉንጉን ይሆናል።+  በፍርድ ወንበር ለተቀመጠውም የፍትሕ መንፈስ፣ የከተማዋ በር ላይ የሚሰነዘረውን ጥቃት ለሚመክቱም የብርታት ምንጭ ይሆናል።+   እነዚህም ከወይን ጠጅ የተነሳ መንገድ ይስታሉ፤ከሚያሰክር መጠጥ የተነሳም ይንገዳገዳሉ። ካህኑና ነቢዩ ከጠጡት መጠጥ የተነሳ መንገድ ይስታሉ፤ከወይን ጠጅ የተነሳ ግራ ይጋባሉ፤ከሚያሰክር መጠጥ የተነሳም ይንገዳገዳሉ፤የሚያዩት ራእይ መንገድ ያስታቸዋል፤ፍርድ ሲሰጡም ይሳሳታሉ።+   ገበታቸው ሁሉ በሚያስጸይፍ ትውከት ተሞልቷል፤ያልተበላሸ ቦታም የለም።   እነሱም እንዲህ ይላሉ፦ “እውቀትን የሚያካፍለው ለማን ነው?መልእክቱንስ የሚያስረዳው ለማን ነው? ገና ወተት ለተዉ፣ጡትም ለጣሉ ሕፃናት ነው? 10  ‘በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣በሥርዓት ላይ ሥርዓት፣ በሥርዓት ላይ ሥርዓት፣*+እዚህ ጥቂት፣ እዚያ ጥቂት’ ነውና።” 11  ስለዚህ በሚንተባተቡ ሰዎች አንደበትና በባዕድ ቋንቋ ለዚህ ሕዝብ ይናገራል።+ 12  በአንድ ወቅት “ይህ የእረፍት ቦታ ነው። የዛለው እንዲያርፍ አድርጉ፤ ይህ የእፎይታ ቦታ ነው” ብሏቸው ነበር፤ እነሱ ግን ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም።+ 13  የይሖዋም ቃል ለእነሱ “በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣ በትእዛዝ ላይ ትእዛዝ፣በሥርዓት ላይ ሥርዓት፣ በሥርዓት ላይ ሥርዓት፣*+እዚህ ጥቂት፣ እዚያ ጥቂት” ይሆንባቸዋል፤ በመሆኑም ሲሄዱ፣ተሰናክለው ወደ ኋላ ይወድቃሉ፤ደግሞም ይሰበራሉ፣ ይጠመዳሉ እንዲሁም ይያዛሉ።+ 14  ስለዚህ እናንተ ጉረኞች፣በኢየሩሳሌም የሚኖረው ሕዝብ ገዢዎች፣ የይሖዋን ቃል ስሙ፦ 15  እናንተ እንዲህ ብላችኋልና፦ “ከሞት ጋር ቃል ኪዳን ገብተናል፤+ከመቃብርም * ጋር ስምምነት አድርገናል።* በድንገት የሚያጥለቀልቅ ጎርፍ ሲያልፍእኛን አይነካንም፤ውሸትን መጠጊያችን አድርገናልና፤በሐሰትም ውስጥ ተደብቀናል።”+ 16  ስለዚህ ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “እነሆ፣ በጽዮን የመሠረት ድንጋይ ይኸውም የተፈተነ ድንጋይ፣+አስተማማኝ መሠረት+ ሆኖ የተጣለ ክቡር የማዕዘን ድንጋይ+ አኖራለሁ። በእሱ የሚያምን አይደናገጥም።+ 17  እኔም ፍትሕን የመለኪያ ገመድ፣+ጽድቅንም ውኃ ልክ* አደርጋለሁ።+ የውሸት መጠጊያውን፣ በረዶ ጠራርጎ ይወስደዋል፤ውኃዎቹም መደበቂያ ቦታውን ያጥለቀልቁታል። 18  ከሞት ጋር የገባችሁት ቃል ኪዳን ይፈርሳል፤ከመቃብርም * ጋር ያደረጋችሁት ስምምነት አይጸናም።+ በድንገት የሚያጥለቀልቀው ጎርፍ ሲያልፍድምጥማጣችሁን ያጠፋል። 19  ጎርፉ ባለፈ ቁጥርጠራርጎ ይወስዳችኋል፤+በየማለዳው እንዲሁምበቀንና በሌሊት ያልፋልና። የተነገረውን ነገር እንዲረዱ የሚያደርገው ሽብር ብቻ ነው።”* 20  እግር ተዘርግቶ እንዳይተኛ አልጋው አጭር ነውና፤ተሸፋፍኖም እንዳይተኛ ጨርቁ በጣም ጠባብ ነው። 21  ይሖዋ ተግባሩን ይኸውም እንግዳ የሆነ ተግባሩን ያከናውን ዘንድእንዲሁም ሥራውን ይኸውም ያልተለመደ ሥራውን ይሠራ ዘንድ+በጰራጺም ተራራ እንዳደረገው ይነሳልና፤በገባኦን አቅራቢያ ባለው ሸለቆ* እንዳደረገውም ራሱን ያነሳሳል።+ 22  እንግዲህ ፌዘኞች አትሁኑ፤+አለዚያ እስራቱ ይበልጥ ይጠብቅባችኋል፤ሉዓላዊው ጌታ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋአገሪቱን በሙሉ* ለማጥፋት ያስተላለፈውን ፍርድ ሰምቻለሁና።+ 23  ጆሯችሁን አዘንብሉ፤ ድምፄንም ስሙ፤ለምናገረው ነገር ትኩረት ስጡ፤ በጥሞናም አዳምጡ። 24  ገበሬ ዘር ከመዝራቱ በፊት ቀኑን ሙሉ ሲያርስ ይውላል? ደግሞስ ጓሉን ሲከሰክስና መሬቱን ሲያለሰልስ ይከርማል?+ 25  ከዚህ ይልቅ መሬቱን ከደለደለ በኋላጥቁር አዝሙድና ከሙን አይዘራም?ስንዴውን፣ ማሽላውንና ገብሱንስ በቦታ በቦታቸው አይዘራም?ደግሞስ አጃውን+ ዳር ላይ አይዘራም? 26  አምላክ ሰውን በትክክለኛው መንገድ ያስተምረዋል፤*ደግሞም ይመራዋል።+ 27  ጥቁር አዝሙድ በማሄጃ*+ አይወቃም፤በከሙንም ላይ የመውቂያ መንኮራኩር* እንዲሄድ አይደረግም። ጥቁር አዝሙድ በበትር፣ከሙንም በዘንግ ይወቃል። 28  ሰው የዳቦ እህል እንዲደቅ ያደርጋል? በጭራሽ፤ እስኪደቅ ድረስ አይወቃውም፤+በፈረሶቹ የሚጎተተውን የመውቂያ መንኮራኩር በሚያስኬድበት ጊዜ፣እህሉን አያደቀውም።+ 29  ይህም የተገኘው፣ አስደናቂ ምክር* ካለውናታላላቅ ሥራዎችን ካከናወነው*ከሠራዊት ጌታ ከይሖዋ ነው።+

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ትዕቢተኛ ወይም ኩሩ ለሆነችው።”
ዋና ከተማዋን ሰማርያን የምታመለክት ልትሆን ትችላለች።
ወይም “ትዕቢተኛ ወይም ኩሩ የሆኑት።”
ወይም “በመለኪያ ገመድ ላይ መለኪያ ገመድ፣ በመለኪያ ገመድ ላይ መለኪያ ገመድ።”
ወይም “በመለኪያ ገመድ ላይ መለኪያ ገመድ፣ በመለኪያ ገመድ ላይ መለኪያ ገመድ።”
ወይም “ከሲኦልም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“ራእይ አይተናል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ቱምቢ።”
ወይም “ከሲኦልም።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
“የተነገረውን ነገር ሲረዱ በሽብር ይዋጣሉ” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “ረባዳማ ሜዳ።”
ወይም “መላዋን ምድር።”
ወይም “ሰውን . . . ይገሥጸዋል፤ ይቀጣዋል።”
ጥርስ መሳይ ጉጦች ያሉት የእህል መውቂያ።
ተሽከርካሪ እግር።
ወይም “ዓላማ።”
ወይም “ጥበቡ ታላቅ ከሆነው።”