ኢሳይያስ 29:1-24

  • ለአርዔል ወዮላት! (1-16)

    • ‘በከንፈሩ ያከብረኛል’ (13)

  • መስማት የተሳናቸው ይሰማሉ፤ ዓይነ ስውራኑም ያያሉ (17-24)

29  “ለአርዔል፣* ዳዊት ለሰፈረባት ከተማ+ ለአርዔል ወዮላት! በዓመት ላይ ዓመት ጨምሩ፤ዓመታዊ በዓሎቻችሁን+ ማክበራችሁን ቀጥሉ።   እኔ ግን በአርዔል ላይ የሚያስጨንቅ ነገር አመጣለሁ፤+ለቅሶና ዋይታም ይሆናል፤+እሷም ለእኔ፣ እንደ አምላክ የመሠዊያ ምድጃ ትሆናለች።+   አንቺን ለማጥቃት በዙሪያሽ እሰፍራለሁ፤በሹል እንጨት አጥርሻለሁ፤በአንቺም ዙሪያ ቅጥር እገነባለሁ።+   ትወድቂያለሽ፤ ትዋረጃለሽም፤መሬት ላይ ሆነሽ ትናገሪያለሽ፤የምትናገሪው ነገር በአፈር ይታፈናል። ድምፅሽ እንደ መናፍስት ጠሪ ድምፅከመሬት ይመጣል፤+ቃልሽም ከአፈር ይጮኻል።   የጠላቶችሽ* ሠራዊት እንደላመ ዱቄት ይሆናል፤+የጨቋኞች መንጋ ተጠርጎ እንደሚሄድ ገለባ ይሆናል።+ ይህም ሳይታሰብ፣ በቅጽበት ይፈጸማል።+   የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ትኩረቱን ወደ አንቺ በማዞርበነጎድጓድ፣ በምድር መናወጥ፣ በታላቅ ድምፅ፣በውሽንፍር፣ በአውሎ ነፋስና በሚባላ የእሳት ነበልባል ያድንሻል።”+   በዚያን ጊዜ አርዔልን የሚወጉ የብሔራት ሠራዊት ሁሉ፣+ይኸውም ጦርነት የሚከፍቱባት ሁሉ፣በእሷ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ማማዎችን የሚሠሩናጭንቀት ላይ የሚጥሏት ሁሉእንደ ሕልም፣ በሌሊትም እንደሚታይ ራእይ ይሆናሉ።   አዎ፣ የተራበ ሰው በሕልሙ ሲበላ ቆይቶሲነቃ ግን ረሃቡ እንደማይለቀው* ሁሉ፣ደግሞም የተጠማ ሰው በሕልሙ ሲጠጣ ቆይቶሲነቃ ግን ዝሎና ተጠምቶ እንደሚነሳ* ሁሉ እንዲሁ ይሆናል። በጽዮን ተራራ ላይ ጦርነት የሚከፍቱ የብሔራት ሠራዊትም ሁሉተመሳሳይ ነገር ይደርስባቸዋል።+   ክው በሉ፤ ተደነቁም፤+ዓይናችሁን ጨፍኑ፤ ዕውሮችም ሁኑ።+ በወይን ጠጅ አይሁን እንጂ ሰክረዋል፤በሚያሰክር መጠጥ አይሁን እንጂ ተንገዳግደዋል። 10  ይሖዋ ኃይለኛ የእንቅልፍ መንፈስ አፍስሶባችኋልና፤+ዓይኖቻችሁን ይኸውም ነቢያትን ጨፍኖባችኋል፤+ራሶቻችሁን ይኸውም ባለ ራእዮችን ሸፍኖባችኋል።+ 11  የሁሉ ነገር ራእይ እንደታሸገ መጽሐፍ ቃል ሆኖባችኋል።+ መጽሐፉን ማንበብ ለሚችል ሰው “እባክህ፣ ጮክ ብለህ አንብበው” ብለው ሲሰጡት “ታሽጓልና አልችልም” ይላል። 12  መጽሐፉንም ማንበብ ለማይችል ሰው “እባክህ፣ ይህን አንብበው” ብለው ሲሰጡት “ፈጽሞ ማንበብ አልችልም” ይላል። 13  ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “ይህ ሕዝብ ወደ እኔ የሚቀርበው በአፉ ብቻ ነው፤በከንፈሩም ያከብረኛል፤+ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው፤እኔንም የሚፈራው፣ ሰዎች ያስተማሩትን ትእዛዛት በማክበር ነው።+ 14  ስለዚህ እኔ በእነዚህ ሰዎች ላይ ዳግመኛ የሚያስደንቁ ነገሮች አደርጋለሁ፤+በድንቅ ላይ ድንቅ ነገር እፈጽማለሁ፤የጥበበኞቻቸውም ጥበብ ይጠፋል፤የአስተዋዮቻቸውም ማስተዋል ይሰወራል።”+ 15  ዕቅዳቸውን ከይሖዋ ለመሰወር* ከፍተኛ ጥረት ለሚያደርጉ ወዮላቸው!+ “ማን ያየናል?ማንስ ያውቅብናል?” በማለት ተግባራቸውን በጨለማ ቦታ ያከናውናሉ።+ 16  እናንተ ሰዎች፣ ነገር ታጣምማላችሁ!* ሸክላ ሠሪው እንደ ሸክላው ሊቆጠር ይገባል?+ የተሠራው ነገር ስለ ሠሪው “እሱ አልሠራኝም” ማለቱ ተገቢ ነው?+ ደግሞስ ዕቃው ሠሪውን “ማስተዋል የለውም” ይላል?+ 17  በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊባኖስ ወደ ፍራፍሬ እርሻነት ይለወጣል፤+የፍራፍሬ እርሻውም እንደ ጫካ ይቆጠራል።+ 18  በዚያ ቀን፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች የመጽሐፉን ቃል ይሰማሉ፤የዓይነ ስውራኑም ዓይኖች ከጭጋግና ከጨለማ ተላቀው ያያሉ።+ 19  የዋሆች በይሖዋ እጅግ ሐሴት ያደርጋሉ፤በሰዎች መካከል ያሉ ድሆችም በእስራኤል ቅዱስ ደስ ይላቸዋል።+ 20  ጨቋኙ ያከትምለታልና፤ጉረኛውም ያበቃለታል፤ሌሎችን ለመጉዳት አሰፍስፈው የሚጠባበቁ ሁሉ ይጠፋሉ፤+ 21  ሌሎችን በውሸት ቃል በደለኛ የሚያደርጉ፣በከተማዋ በር፣+ በተሟጋቹ* ላይ ወጥመድ የሚዘረጉናመሠረተ ቢስ በሆነ ክስ ጻድቁን ሰው ፍትሕ የሚነፍጉ ይጠፋሉ።+ 22  ስለዚህ አብርሃምን+ የተቤዠው ይሖዋ ለያዕቆብ ቤት እንዲህ ይላል፦ “ያዕቆብ ከእንግዲህ አያፍርም፤ፊቱም ከእንግዲህ አይገረጣም።*+ 23  የእጆቼ ሥራ የሆኑትን ልጆቹንበመካከሉ በሚያይበት ጊዜ፣+ስሜን ይቀድሳሉና፤አዎ፣ የያዕቆብን ቅዱስ ይቀድሳሉ፤የእስራኤልንም አምላክ ይፈራሉ።*+ 24  በመንፈስ የባዘኑ ማስተዋል ያገኛሉ፤የሚያጉረመርሙም የሚሰጣቸውን ትምህርት ይቀበላሉ።”

የግርጌ ማስታወሻ

“የአምላክ የመሠዊያ ምድጃ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል፤ ኢየሩሳሌምን የሚያመለክት ይመስላል።
ቃል በቃል “የባዕዳን።”
ወይም “ነፍሱ ባዶ እንደምትሆን።”
ወይም “ነፍሱ በጥም እንደምትቃጠል።”
ወይም “ምክራቸውን ከይሖዋ ለመሰወር።”
ወይም “እንዴት ጠማሞች ናችሁ!”
ቃል በቃል “ወቀሳ በሚሰነዝረው።”
ውርደትና ኀፍረት እንደማይደርስበት ያመለክታል።
ወይም “ለእስራኤልም አምላክ አክብሮታዊ ፍርሃት ያሳያሉ።”