ኢሳይያስ 36:1-22

  • ሰናክሬም ይሁዳን ወረረ (1-3)

  • ራብሻቁ በይሖዋ ላይ ተሳለቀ (4-22)

36  ንጉሥ ሕዝቅያስ በነገሠ በ14ኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ+ ሰናክሬም በተመሸጉት የይሁዳ ከተሞች ሁሉ ላይ ዘምቶ ያዛቸው።+  ከዚያም የአሦር ንጉሥ፣ ራብሻቁን*+ ከብዙ ሠራዊት ጋር ከለኪሶ፣+ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ወደ ንጉሥ ሕዝቅያስ ላከው። እነሱም ወደ ልብስ አጣቢው እርሻ+ በሚወስደው አውራ ጎዳና ላይ በሚገኘው በላይኛው ኩሬ የውኃ መውረጃ ቦይ አጠገብ ቆሙ።+  ከዚያም የቤቱ* ኃላፊ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣+ ጸሐፊው ሸብና+ እንዲሁም ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ወደ እሱ መጡ።  ራብሻቁም እንዲህ አላቸው፦ “እስቲ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፦ ‘ታላቁ ንጉሥ፣ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ “ለመሆኑ እንዲህ እንድትተማመን ያደረገህ ምንድን ነው?+  ‘የጦር ስልትና ለመዋጋት የሚያስችል ኃይል አለኝ’ ትላለህ፤ ይሁንና ይህ ከንቱ ወሬ ነው። ለመሆኑ በእኔ ላይ ለማመፅ የደፈርከው በማን ተማምነህ ነው?+  እነሆ፣ ሰው ቢመረኮዘው እጁ ላይ ሊሰነቀርና ሊወጋው ከሚችለው ከዚህ ከተቀጠቀጠ ሸምበቆ፣ ከግብፅ ድጋፍ አገኛለሁ ብለህ ተማምነሃል። የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን ለሚታመኑበት ሁሉ እንዲሁ ነው።+  ‘እኛ የምንታመነው በአምላካችን በይሖዋ ነው’ የምትለኝ ከሆነ ደግሞ፣ ሕዝቅያስ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ‘መስገድ ያለባችሁ በዚህ መሠዊያ ፊት ነው’+ ብሎ የእሱን ከፍ ያሉ የማምለኪያ ቦታዎችና መሠዊያዎች አስወግዶ የለም?”’+  በል እስቲ፣ አሁን ከጌታዬ ከአሦር ንጉሥ+ ጋር ተወራረድ፦ ጋላቢዎች ማግኘት የምትችል ከሆነ 2,000 ፈረሶች እሰጥሃለሁ።  አንተ የምትታመነው በግብፅ ሠረገሎችና ፈረሰኞች ነው፤ ታዲያ ከጌታዬ አገልጋዮች መካከል ዝቅተኛ ደረጃ ያለውን አንዱን አለቃ እንኳ እንዴት መመከት ትችላለህ? 10  ለመሆኑ ይህን ምድር ለማጥፋት የመጣሁት ይሖዋ ሳይፈቅድልኝ ይመስልሃል? ይሖዋ ራሱ ‘በዚህ ምድር ላይ ዘምተህ አጥፋው’ ብሎኛል።” 11  በዚህ ጊዜ ኤልያቄም፣ ሸብና+ እና ዮአህ ራብሻቁን+ እንዲህ አሉት፦ “እባክህ፣ እኛ አገልጋዮችህ ቋንቋውን ስለምናውቅ በአረማይክ* ቋንቋ+ አናግረን፤ በቅጥሩ ላይ ያለው ሕዝብ በሚሰማው በአይሁዳውያን ቋንቋ አታነጋግረን።”+ 12  ራብሻቁ ግን እንዲህ አለ፦ “ጌታዬ ይህን ቃል እንድናገር የላከኝ ለጌታህና ለአንተ ብቻ ነው? ከእናንተ ጋር የገዛ ራሳቸውን እዳሪ ለሚበሉትና የገዛ ራሳቸውን ሽንት ለሚጠጡት በቅጥሩ ላይ ለተቀመጡት ሰዎች ጭምር አይደለም?” 13  ከዚያም ራብሻቁ ቆሞ ከፍ ባለ ድምፅ በአይሁዳውያን ቋንቋ+ እንዲህ አለ፦ “የታላቁን ንጉሥ፣ የአሦርን ንጉሥ ቃል ስሙ።+ 14  ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ ‘ሕዝቅያስ አያታላችሁ፤ እሱ ሊታደጋችሁ አይችልምና።+ 15  ደግሞም ሕዝቅያስ “ይሖዋ በእርግጥ ይታደገናል፤ ይህችም ከተማ በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” እያለ በይሖዋ እንድትታመኑ አያድርጋችሁ።+ 16  ሕዝቅያስን አትስሙት፤ የአሦር ንጉሥ እንዲህ ይላልና፦ “ከእኔ ጋር ሰላም ፍጠሩ፤ እጃችሁንም ስጡ፤* እያንዳንዳችሁም ከራሳችሁ ወይንና ከራሳችሁ በለስ ትበላላችሁ፤ ከራሳችሁም የውኃ ጉድጓድ ትጠጣላችሁ፤ 17  ይህም የሚሆነው መጥቼ የእናንተን ምድር ወደምትመስለው፣ እህልና አዲስ የወይን ጠጅ፣ ዳቦና የወይን እርሻ ወደሚገኝባት ምድር እስክወስዳችሁ ድረስ ነው።+ 18  ሕዝቅያስ ‘ይሖዋ ይታደገናል’ በማለት አያታላችሁ። ከብሔራት አማልክት መካከል ምድሩን ከአሦር ንጉሥ እጅ ያስጣለ አለ?+ 19  የሃማትና የአርጳድ+ አማልክት የት አሉ? የሰፋርዊም+ አማልክትስ የት አሉ? ሰማርያን ከእጄ ማስጣል ችለዋል?+ 20  ከእነዚህ አገሮች አማልክት ሁሉ ምድሩን ከእጄ ማስጣል የቻለ የትኛው ነው? ታዲያ ይሖዋ ኢየሩሳሌምን ከእጄ ሊያስጥላት ይችላል?”’”+ 21  እነሱ ግን ንጉሡ “ምንም መልስ አትስጡት” ብሎ አዝዞ ስለነበር ዝም አሉ፤ አንድም ቃል አልመለሱለትም።+ 22  ይሁንና የቤቱ* አስተዳዳሪ የሆነው የኬልቅያስ ልጅ ኤልያቄም፣ ጸሐፊው ሸብና+ እንዲሁም ታሪክ ጸሐፊው የአሳፍ ልጅ ዮአህ ልብሳቸውን ቀደው ወደ ሕዝቅያስ መጡ፤ ራብሻቁ ያለውንም ነገሩት።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የመጠጥ አሳላፊዎቹን አለቃ።”
ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”
ወይም “በሶርያ።”
ቃል በቃል “ከእኔ ጋር ባርኩ፤ እንዲሁም ወደ እኔ ውጡ።”
ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”