ኢሳይያስ 37:1-38

  • ሕዝቅያስ በኢሳይያስ በኩል የአምላክን እርዳታ ጠየቀ (1-7)

  • ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ ዛተ (8-13)

  • የሕዝቅያስ ጸሎት (14-20)

  • ኢሳይያስ አምላክ የሰጠውን መልስ ተናገረ (21-35)

  • አንድ መልአክ 185,000 አሦራውያንን ገደለ (36-38)

37  ንጉሥ ሕዝቅያስ ይህን እንደሰማ ልብሱን ቀደደ፤ ማቅ ለብሶም ወደ ይሖዋ ቤት ገባ።+  ከዚያም የቤቱ* አስተዳዳሪ የሆነውን ኤልያቄምን፣ ጸሐፊውን ሸብናን እንዲሁም የካህናቱን ሽማግሌዎች ማቅ ለብሰው ወደ አሞጽ ልጅ ወደ ነቢዩ ኢሳይያስ+ እንዲሄዱ ላካቸው።  እነሱም እንዲህ አሉት፦ “ሕዝቅያስ እንዲህ ይላል፦ ‘ይህ ቀን የጭንቀት፣ የዘለፋና* የውርደት ቀን ነው፤ መውለጃዋ ደርሶ* ለማማጥ የሚያስችል አቅም እንዳጣች ሴት ሆነናል።+  ምናልባት አምላክህ ይሖዋ፣ ሕያው የሆነውን አምላክ እንዲያቃልል+ ጌታው የአሦር ንጉሥ የላከውን የራብሻቁን ቃል ይሰማ ይሆናል፤ ደግሞም አምላክህ ይሖዋ፣ የተናገረውን ቃል ሰምቶ ተጠያቂ ያደርገው ይሆናል። ስለዚህ በሕይወት ለተረፉት ቀሪዎች+ ጸልይ።’”+  በመሆኑም የንጉሥ ሕዝቅያስ አገልጋዮች ወደ ኢሳይያስ ሄዱ፤+  ኢሳይያስም እንዲህ አላቸው፦ “ጌታችሁን እንዲህ በሉት፦ ‘ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ “የአሦር ንጉሥ አገልጋዮች+ እኔን በመሳደብ የተናገሩትን ቃል በመስማትህ አትፍራ።+  እነሆ፣ በአእምሮው አንድ ሐሳብ አስገባለሁ፤* እሱም ወሬ ሰምቶ ወደ አገሩ ይመለሳል፤+ በገዛ አገሩም በሰይፍ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።”’”+  ራብሻቁም የአሦር ንጉሥ ለኪሶን ለቆ እንደሄደ ሲሰማ ወደ ንጉሡ ተመለሰ፤ ከሊብናም ጋር ሲዋጋ አገኘው።+  በዚህ ጊዜ ንጉሡ የኢትዮጵያው ንጉሥ ቲርሃቅ “ከአንተ ጋር ሊዋጋ ወጥቷል” የሚል ወሬ ሰምቶ ነበር። እሱም ይህን በሰማ ጊዜ ለሕዝቅያስ እንዲህ ብለው እንዲነግሩት በድጋሚ መልእክተኞች ላከ፦+ 10  “የይሁዳን ንጉሥ ሕዝቅያስን እንዲህ በሉት፦ ‘የምትታመንበት አምላክህ “ኢየሩሳሌም በአሦር ንጉሥ እጅ አትወድቅም” ብሎ አያታልህ።+ 11  እነሆ፣ የአሦር ነገሥታት ሌሎቹን አገሮች ሁሉ ፈጽመው በማጥፋት ያደረጉትን ነገር ሰምተሃል።+ ታዲያ አንተ ብቻ ከዚህ የምታመልጥ ይመስልሃል? 12  አባቶቼ ያጠፏቸውን ብሔራት አማልክታቸው ታድገዋቸዋል?+ ጎዛን፣ ካራን፣+ ረጼፍና በቴልአሳር የነበሩት የኤደን ሕዝቦች የት አሉ? 13  የሃማት ንጉሥ፣ የአርጳድ ንጉሥ፣ የሰፋርዊም+ ከተሞች ንጉሥ እንዲሁም የሄና እና የኢዋ ነገሥታት የት አሉ?’” 14  ሕዝቅያስ ደብዳቤዎቹን ከመልእክተኞቹ እጅ ተቀብሎ አነበበ። ከዚያም ወደ ይሖዋ ቤት ወጥቶ ደብዳቤዎቹን* በይሖዋ ፊት ዘረጋ።+ 15  ሕዝቅያስም ወደ ይሖዋ እንዲህ ሲል ጸለየ፦+ 16  “ከኪሩቤል በላይ* የምትቀመጥ፣ የእስራኤል አምላክ፣ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ሆይ፣+ የምድር መንግሥታት ሁሉ እውነተኛ አምላክ አንተ ብቻ ነህ። ሰማያትንና ምድርን ሠርተሃል። 17  ይሖዋ ሆይ፣ ጆሮህን አዘንብለህ ስማ!+ ይሖዋ ሆይ፣ ዓይንህን ገልጠህ እይ!+ ሰናክሬም ሕያው የሆነውን አምላክ ለማቃለል የላከውን ቃል ሁሉ ስማ።+ 18  ይሖዋ ሆይ፣ የአሦር ነገሥታት ሌሎቹን አገሮች ሁሉና የገዛ ራሳቸውን ምድር እንዳጠፉ አይካድም።+ 19  አማልክታቸውንም እሳት ውስጥ ጨምረዋል፤+ ምክንያቱም የሰው እጅ ሥራ፣ እንጨትና ድንጋይ እንጂ አማልክት አይደሉም።+ ሊያጠፏቸው የቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። 20  አሁን ግን አምላካችን ይሖዋ ሆይ፣ የምድር መንግሥታት ሁሉ፣ አንተ ብቻ እውነተኛ አምላክ እንደሆንክ ያውቁ ዘንድ ይሖዋ ሆይ፣ ከእጁ አድነን።”+ 21  ከዚያም የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ እንዲህ የሚል መልእክት ወደ ሕዝቅያስ ላከ፦ “የእስራኤል አምላክ ይሖዋ እንዲህ ይላል፦ ‘የአሦርን ንጉሥ ሰናክሬምን በተመለከተ ወደ እኔ ስለጸለይክ፣+ 22  ይሖዋ በእሱ ላይ የተናገረው ቃል ይህ ነው፦ “ድንግሊቱ የጽዮን ልጅ ትንቅሃለች፤ ደግሞም ታፌዝብሃለች። የኢየሩሳሌም ሴት ልጅ ራሷን ትነቀንቅብሃለች። 23  ያቃለልከውና+ የሰደብከው ማንን ነው? ድምፅህን ከፍ ያደረግከው፣+እብሪተኛ ዓይንህንም ያነሳኸው በማን ላይ ነው? በእስራኤል ቅዱስ ላይ እኮ ነው!+ 24  በአገልጋዮችህ በኩል ይሖዋን አቃለሃል፤+ እንዲህም ብለሃል፦‘ብዛት ባላቸው የጦር ሠረገሎቼ፣ወደ ተራሮች ከፍታ፣ርቀው ወደሚገኙትም የሊባኖስ ስፍራዎች እወጣለሁ።+ ረጃጅሞቹን አርዘ ሊባኖሶች፣ ምርጥ የሆኑትንም የጥድ ዛፎች እቆርጣለሁ። እጅግ ከፍ ወዳለው ማረፊያ ቦታ፣ በጣም ጥቅጥቅ ወዳለው ጫካ እገባለሁ። 25  ጉድጓድ ቆፍሬ ውኃ እጠጣለሁ፤የግብፅን ጅረቶች* በእግሬ ረግጬ አደርቃለሁ።’ 26  አልሰማህም? ይህ ከጥንት ዘመን ጀምሮ የተወሰነ* ነው። ከድሮ ጀምሮ ይህን አስቤአለሁ።*+ አሁን እንዲፈጸም አደርጋለሁ።+ አንተም የተመሸጉትን ከተሞች የፍርስራሽ ክምር ታደርጋለህ።+ 27  ነዋሪዎቻቸው አቅመ ቢስ ይሆናሉ፤ይሸበራሉ፤ ደግሞም ያፍራሉ። እንደ ሜዳ ተክል፣ እንደ ለምለም ሣር፣እንዲሁም የምሥራቅ ነፋስ እንዳቃጠለው በጣሪያ ላይ የበቀለ ሣር ይሆናሉ። 28  ይሁንና መቼ እንደምትቀመጥ፣ መቼ እንደምትወጣና መቼ እንደምትገባ፣እንዲሁም መቼ በእኔ ላይ እንደተቆጣህ በሚገባ አውቃለሁ፤+ 29  ምክንያቱም በእኔ ላይ የተቆጣኸው ቁጣና+ ጩኸትህ ወደ ጆሮዬ ደርሷል።+ ስለዚህ ስናጌን በአፍንጫህ፣ ልጓሜንም+ በአፍህ አስገባለሁ፤በመጣህበትም መንገድ እንድትመለስ አደርግሃለሁ።” 30  “‘ይህም ምልክት ይሆንሃል፦* በዚህ ዓመት የገቦውን እህል* ትበላላችሁ፤ በሁለተኛውም ዓመት ከዚያው ላይ የበቀለውን እህል ትበላላችሁ፤ በሦስተኛው ዓመት ግን ዘር ትዘራላችሁ፤ ታጭዳላችሁም፤ እንዲሁም ወይን ትተክላላችሁ፤ ፍሬውንም ትበላላችሁ።+ 31  ከይሁዳ ቤት ያመለጡትና በሕይወት የቀሩት ሰዎች+ ወደ ታች ሥር ይሰዳሉ፤ ወደ ላይም ያፈራሉ። 32  ከኢየሩሳሌም ቀሪዎች፣ ከጽዮን ተራራም በሕይወት የተረፉ ሰዎች ይወጣሉና።+ የሠራዊት ጌታ የይሖዋ ቅንዓት ይህን ያደርጋል።+ 33  “‘ስለዚህ ይሖዋ ስለ አሦር ንጉሥ እንዲህ ይላል፦+ “ወደዚህች ከተማ አይመጣም፤+ፍላጻም አይወረውርባትም፤ጋሻም ይዞ አይመጣባትም፤ከበባ ለማድረግም በዙሪያዋ የአፈር ቁልል አይደለድልም።”’+ 34  ‘በመጣበት መንገድ ይመለሳል፤ወደዚህች ከተማ አይገባም’ ይላል ይሖዋ። 35  ‘ስለ እኔና+ ስለ አገልጋዬ ስለ ዳዊት ስል+ይህችን ከተማ እጠብቃታለሁ፤+ ደግሞም አድናታለሁ።’” 36  የይሖዋም መልአክ ወጥቶ በአሦራውያን ሰፈር የነበሩትን 185,000 ሰዎች ገደለ። ሰዎችም በማለዳ ሲነሱ ሬሳውን አዩ።+ 37  በመሆኑም የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም ከዚያ ተነስቶ ወደ ነነዌ+ ተመለሰ፤ በዚያም ተቀመጠ።+ 38  ሰናክሬም በአምላኩ በኒስሮክ ቤት* እየሰገደ ሳለ አድራሜሌክና ሳሬጸር የተባሉት የገዛ ልጆቹ በሰይፍ መትተው ገደሉት፤+ ከዚያም ወደ አራራት+ ምድር ሸሽተው ሄዱ። ልጁም ኤሳርሃደን+ በእሱ ምትክ ነገሠ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “የቤተ መንግሥቱ።”
ወይም “የስድብና።”
ቃል በቃል “ልጁ ወደ ማህፀኑ አፍ መጥቶ።”
ቃል በቃል “እነሆ፣ መንፈስ አስገባበታለሁ።”
ቃል በቃል “ደብዳቤውን።”
“በኪሩቤል መካከል” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ወይም “የግብፅን የአባይ የመስኖ ቦዮች።”
ቃል በቃል “የተደረገ።”
ወይም “ሠርቻለሁ።”
ሰብል በሚሰበሰብበት ጊዜ ማሳው ላይ ረግፎ እንደገና የሚበቅለውን እህል ያመለክታል።
ለሕዝቅያስ የተነገረ ነው።
ወይም “ቤተ መቅደስ።”